በሀገሪቱ የተባባሰውን የፀጥታና የመረጋጋት ችግር ተከትሎ መንግስት በተበታተነ መልክ የሚንቀሳቀሱ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማቱን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየተንቀሳቀሰ ነው። “የደህንነትና የፖሊስ ተቋማት አሁን ባሉበት ሁኔታ መቀጠል ለሀገሪቱ ዘላቂ ህልውና አደጋን ይጋብዛል” ያለው የመንግስት የደህንነት ካውንስል ባቀረበው ሀሳብ መሰረት በሶስት ደረጃ የተከፈለ የማሻሻያ ዕቅድ ተግባራዊ ይደረጋል። የዚህ እንቅስቃሴ አንድ ክፍል የሆነውና የፌደራል ፖሊስን ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲሆን የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
በእርግጥ የአዋጁ አብይ አላማ ምንድነው? የፌደራሉ ፖሊስ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚንስትሩ መሆኑ ወትሮም በህወሀት የበላይነት በሚዘወረው የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ምን ለውጥ ያመጣል? ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮችን አነጋግራለች። አንተነህ ኪዳኔ ያዘጋጀውን ዘገባ እነሆ
[ዘገባውን በድምፅ እዚህ ማድመጥ ይችላሉ/ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]
አወዛጋቢ እና አከራካሪ ህጎች ማውጣት የማይታክተው የኢትዮጵያ ፓርላማ በዚህ ሳምንት የብዙዎችን ቅንድብ ከፍ ያስደረገ ሌላ የህግ ረቂቅ ለቤቱ አቅርቦ ነበር፡፡ የህግ ረቂቁ በፌደራልና አርብቶ አደር ሚኒስቴር ስር የነበሩትን የፌደራል ፖሊስ ና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽኖችን ከሚንስቴሩ እንዲወጡ የሚያደርግ ነው። ህጉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጠሪነት ደግሞ የፍትህ ሚኒስትርን ሥልጣንና ተግባር ወደወረሰው እና ራሱን ችሎ ወደሚቋቋመው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይዛወራል፡፡
በሌሎች ህጎች የማጸደቅ ሂደት እንደተለመደው በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስቀድሞ ውይይት ያልተደረገበት የህግ ረቂቅ ከወዲሁ ጥያቄዎችን ከየአቅጣጫው አስነስቷል፡፡ ረቂቁ ለዝርዝር ዕይታ ለፓርላማው ህግና ፍትህ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንደተመራ ቢገለጽም መቶ በመቶ በገዢው ፓርቲ ከተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት ስር ነቀል ለውጥ የማይጠብቁ ወገኖች ከፖለቲካ እና ከህግ አወጣጥ አንጻር በየፈርጁ ይበልቱት ይዘዋል፡፡ ትችታቸው የበረታው እና ትከረታቸውም የጨመረው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ ላይ ነው፡፡
የፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት ለምን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሰጥ እንደተፈለገ በህግ ረቂቁ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን “በወንጀል መከላከል፣ የአገር ውስጥ ደህንነትን በማስከበር፣ የሽብር ወንጀልን በመከላከል እና በሌሎች በርካታ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነትን እየተወጣ” መሆኑን የሚጠቅሰው ማብራሪያው ይህን ተቋም “ለአንድ አስፈጻሚ ተቋም ብቻ ተጠሪ አድርጎ መቀጠል የአሠራር ክፍተት እንዳይፈጥር” በሚል ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን መደረጉን ያትታል፡፡
በ1995 ዓ.ም ወደ ቀድሞው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከመዛወሩ በፊት የፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት ለፍትህ ሚኒስቴር ነበር፡፡ የዚያን ጊዜው የተጠሪነት ሽግሽጉ የተደረገው የፌደራል ጉዳዮች በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ የመወሰን ስልጣንና ተግባራት በአዋጅ ከተሰጡት በኋላ ነበር፡፡
“ፌደራል ፖሊስ መጀመሪያም ቢሆን ወደ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሄደው የፌደራል መንግስት የጸጥታ ክንፍ (arm) እንዲሆን በማሰብ ነበር” ይላል ቀድሞ የህግ አስተማሪ አሁን ደግሞ ጠበቃና አማካሪ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኝ ባለሙያ ለዋዜማ ሲናገር፡፡ “በፍትህ ሚኒስቴር ስር እያለ ከገደቡ እንዳያልፍ እና ከመጠን ያለፈ ኃይል እንዳይጠቀም የመያዝ ነገር ነበር፡፡ ፍትህ ሚኒስትር እንደ ፌደራል ጉዳዮች በፖለቲካ ሰዎች ሳይሆን በህግ ባለሙያዎች ነበር የሚመራው” ሲል ከዝውውሩ ጀርባ ስለነበረው ዋና ምክንያት ያስረዳል፡፡
ፌደራል ጉዳዮች በክልሎች ጣልቃ የሚገባው በውስን ጉዳዮች (exceptions) መሆኑን የሚያሰምርበት የህግ ባለሙያው የፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት ከፍትህ ሚኒስቴር በወቅቱ በዚህ ምክንያት መነጠቁ አግባብ እንዳልነበር ይከራከራል፡፡ ውሳኔውም ፖለቲካው እንደነበር አስረግጦ ይናገራል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እና የጸጥታ ጉዳይ አጥኚዎችም የዚያን ጊዜውም ሆነ የአሁኑ ውሳኔ ፖለቲካዊ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡ የኢህአዴግ መንግስት የፖሊስ የጸጥታ ኃይሉን አንዴ በማዕከላዊ መንግስት ስር ሌላ ጊዜ ደግሞ ዲሴንትራላይዝ በማድረግ ሲወላውል መቆየቱን ያስረዳሉ፡፡
ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በሽግግር ዘመን ወቅት በመጀመሪያ ህግ ከወጣላቸው ተቋማት አንዱ የፖሊስ ኃይል አንዱ ነበር፡፡ በ1934 ዓ.ም በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ከጸደቀው የፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ በመቀጠል ተያያዥነት ያላቸው ህጎች የወጡት ንጉሱ ከስልጣን ከመውረዳቸው አንድ አመት አስቀድሞ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ሳይነካ የቀጠለው ፖሊስን የሚገዛ ህግ በ1983፣ በ1992 እና በ1995 ዓ.ም ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ አሁን በረቂቅነት ደረጃ ያለው አራተኛ ማሻሻያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የፖሊስ ኃይል የሚታየው እንደ አንድ የሰራዊቱ አካል እንደነበር በፖሊስ ላይ ጥናት ያደረገ ተመራማሪ ይናገራል፡፡ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ይህን ለመቀየር የፖሊስ ኃይሉን በሶስት መርሆዎች ላይ ተመስርቶ ለማሻሻል (ሪፎርም) እንደሞከረ ያስረዳል፡፡ የመጀመሪያው ያልተማከለ ማድረግ (decentralization)፣ ሁለተኛው የወታደራዊ ባህሪ እንዳይላበስ ማድረግ (demilitarization) ሲሆን የመጨረሻው ለፖለቲካ ያልወገነ (apolitical) ተቋም ማድረግ ነበር፡፡
ገዢው ፓርቲ በተወሰነ ደረጃ ሶስቱንም ለማሳካት ቢውተረተርም በ1993 ዓ.ም እና በ1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተከሰቱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ምክንያት ወደ ኋላ መመለሱን ያስረዳል፡፡ በሌሎች ሀገሮች እንደሚተገበረው ፖሊስ በወንጀል መከላከል እና በአግልግሎት ሰጪነት ብቻ እንዲወሰን ተወጥኖ የነበረ ቢሆንም መንግስት “በቁርጥ ቀን የሚከላከልከለት ኃይል በመፈለጉ” የተቋም ግንባታው መጨናገፉን ይገልጻል፡፡ በተለይ የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በነበሩ ሁነቶች የአዲስ አበባ እና የክልል ፖሊሶች ያሳዩት “ለዘብተኝነት” መንግስት ጉዳዩን መልሶ “በጥብቅ እንዲያስብበት” እንዳደረገው ያብራራል፡፡
ከምርጫ 97 ሁለት ዓመት ቀድሞ ተጠሪነቱ ወደ ፌደራል ጉዳዮች የዞረው የፌደራል ፖሊስ ከምርጫው በኋላ የፌደራል መንግስቱ ሁነኛ ተቋም እየሆነ መጥቶ ነበር፡፡ ጡንቻው ፈረጠመ ሲባል ዘግየት ብለው በወጡ የገቢዎች እና የጉምሩክ እንደዚሁም የጸረ-ሙስና ህጎች ወንጀልን የመመርመር ስልጣኑ ተሸራረፈ፡፡
ሆኖም በሀገሪቱ ከዩኒቨርስቲ ተቃውሞ እስከ ብሔር ግጭት ያሉ ማናቸውም ችግሮች ሲፈጠሩ ወደ የቦታዎቹ በእሳት አጥፊነት የሚላክ ኃይል የመሆኑ እውነታ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋ እና እየገዘፈ እንጂ እየደበዘዘ አልመጣም፡፡ ከህዳሴው ግድብ እስከ ዮኒቨርስቲዎች፣ ከኤምባሲ እስከ “ፓርቲ” የሬድዮ ጣቢያ ጥበቃ ከግዙፍ እስከ ጥቃቅን “ተፈላጊ” ተቋማት ጥበቃ የሚያደርገው ፌደራል ፖሊስ ነው፡፡ ኮንትሮባንድን ከመከላከል እስከ ድንበር ቁጥጥር ያሉ ስራዎችን ሲተገብርም ይስተዋላል፡፡
እንደ ዋዜማ ምንጮች ከሆነ በአሁኑ ወቅት የፌደራል ፖሊስ አባላት ፈጥኖ ደራሽን ጨምሮ ወደ 60 ሺህ ገደማ ደርሰዋል፡፡ የፖሊስ ኮሚሽኑ የአባላት ቁጥሩ በበዙ፣ ስራው እና ሃላፊነቱ በገዘፉ መጠን በማን ስር ሆኖ ተግባራቱን እንደሚፈጽም ግራ ሲያጋባ ቆይቷል፡፡
“የፌደራል ፖሊስ ባለፉት 15 ዓመታት ስር የሰደደ የማንነት ቀውስ የተንጸባረቀበት ተቋም ነው” ይላል በፖሊስ ላይ ጥናት ያደረገው ተመራማሪ፡፡ “ተጠሪነቱ ለፌደራል ጉዳዮች ነው ይባል እንጂ ለይስሙላ ነው፡፡ ከፌደራል ጉዳዮች ጋር ካለው ግንኙነት ይልቅ ከሌሎች የደህንነት ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ ነው፡፡”
የተመራማሪውን አባባል በጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያማክሩ ባለሙያ ይጋሩታል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ለፌደራል ጉዳዮች ተጠሪ እንዲሆን የተደረገው ከስራ አስፈጻሚው ቅርንጫፎች በአንዱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አማካኝነት ዓመታዊ ሪፖርት ተቀብሎ በጀት ለመመደብ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
“የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የፌደራል ፖሊስን ለመቆጣጠር ምንም ስልጣን አልነበረውም” ይላሉ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪው፡፡ “የፌደራል ፖሊስ ቀጥተኛ ተጠሪነቱ [ለደህንነት ሹሙ] ጌታቸው አሰፋ ነው፡፡”
የደህንነት ተቋሙ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ያለውን መስመሩን ያልለየ ግንኙነት የባለሙያዎቹን አስተያየት ይደግፋል፡፡ ሽብርን ለማዋጋት በሚል በሁለቱ መስሪያ ቤቶች የተቋቋመው የጋራ ግብረ ኃይል እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት በሚመራው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሁለቱ ተቋማት መሪዎች ያላቸው ተሳትፎ በምሳሌነት ይነሳሉ፡፡ አሁን በኃላፊነት ደረጃ የሚገኙት ኮሚሽነር አሰፋ አብዮ እና ከእርሳቸው በፊት የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ ሁለቱም ከክልል የጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊነት ተነስተው በቦታው ላይ መሾማቸው ሌላው አመላካች ነው።
የጸጥታ ባለሙያው “ጸሐይ የሞቀው እውነት” የሚሉት የፌደራል ፖሊስ የዲቪዥን ኃላፊዎች ኮሚሽነራቸውን ተሻግረው ለደህንነት ሹሙ በቀጥታ ሪፖርት የማድረግ አሰራርም ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡
የፌደራል ፖሊስ እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት ካለው “ለምን ወደፊት በጥናት ላይ ተመስርቶ እስኪወሰን ድረስ” በሚል ተጠሪነቱ “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደረገ?” ለሚለው ጥያቄ ሶስቱም ባለሙያዎች ተቀራራቢ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በኦሮሚያ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች በጸጥታ ሃይሉ በኩል የታየው “ያለመቀናጀት”፣ “ያለማናበብ” እና “ያለመታዘዝ” ሁነቶች ለውሳኔው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ የህግ ረቂቁ ማብራሪያ ላይም “አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር” የሚል ሀረግ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
“በኦሮሚያ ጉዳይ አስገራሚ የሆነ ያለመቀናጀት ችግር በጸጥታ ኃይሉ በኩል ታይቷል” ይላሉ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪው፡፡ “የትዕዛዝ ሰንሰለቱ እንዴት እንደሆነ አይታወቅም፡፡”
የህግ ጠበቃ እና አማካሪውም “የቅንጅት ጉዳይ” ከህጉ ረቂቁ ጀርባ እንዳለ ይስማማሉ፡፡ መንግስት የደህንነት እና የፖሊስ ኃይሉን አቀናጅቶ ለመምራት እና ከአንድ ማዕከል ትዕዛዝ እንዲቀበሉ ለማድረግ በማሰብ ህጉ እንዲረቀቅ እንዳደረገ ያስረዳሉ፡፡ የህጉ ረቂቁ በዚህ ወቅት መውጣት “መንግስት ያለበትን የጸጥታ ስጋት በግልጽ ያሳያል” ሲሉም ያክላሉ፡፡
“መንግስት የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ያልረጋ መሆኑ አስፈርቶታል” ይላሉ፡፡ “ለዚህም የጸጥታውን ክንፍ እያጠናከረ ይመስላል፡፡”
የወቅቱ የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ የህግ ረቂቁን ለማውጣት ምክንያት እንደሆነ አንዱ ማሳያው የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ መንፈቅ እንኳ ሳይሞላው እንዲሻሻል ማድረጉ ነው። የመንግስት መስሪያ ቤቶችን እንደገና ያዋቀረው አዋጅ በመስከረም ወር መጨረሻ ሲወጣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል ለረጅም ጊዜ ጥናት ተደርጎበት እንደሆነሲወጣ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ጥናቱን መመልከታቸውን የሚገልፁት የህግ አማካሪው የፌደራል ፖሊስም ሆነ አሁን የተሻሻሉት ሌሎች ተቋማት ያን ጊዜ በጥናቱ አለመካተታቸውን ያስታውሳሉ። “አሁን ለምን አስፈለገ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
“ይህ ከፍ ያለ የህጎች በሽታ ያሳያል” ሲሉ “በይድረስ ይድረስ” የተሰራ የሚሉትን የህግ ረቂቅ አወጣጥ ይተቻሉ። “ህግ ሲወጣ በቋሚነት ነው መውጣት ያለበት። በየቀኑ የሚሻሻል ህግ ተዓማኒነቱን ያጣል” ይላሉ።
የህግ አማካሪውን ያስደመማቸው እውነታ አሁን በረቂቅ ደረጃ ያለው ህግም ቢሆን የፌደራል ፖሊስን ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጠው እና ነባሩን አዋጅ የሚያሻሽለው “በጊዜያዊነት” መሆኑ ነው። “በጊዜያዊነት ህግ እንዴት ይሻሻላል?” ሲሉ ገረሜታቸውን በጥያቄ መልክ ያስቀመጣሉ። በህግ ረቂቁ ላይ የተጠቀሰው “ጥናት እስኪደረግ” የሚለው ገለጻም አልተዋጠላቸውም። “ጥናቱን ለማድረግ አሁን ምን አስቸገረ?” ይላሉ።
የፌደራል ፖሊስ በመሰጠቱ “በጊዜያዊነት” በአደራ መልክ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተላልፎ መሰጠቱ የሚፈጥረው የመዋለል ስሜት ከግምት ውስጥ አልገባም ባይ ናቸው የህግ አማካሪው። አንድ ተቋም ለሌላ መስሪያ ቤት ተጠሪ እንዲሆን ሲደረግ የፋይናንስም ሆነ የፖለቲካ ተፅዕኖዎች አሉት። የተቋሙ አደረጃጀት፣ ፖሊሲ የማስፈጸም ሁኔታ እና ውሳኔ የሚቀበልበት ሂደት የሚቃኘው የጠሪነት ስልጣን ባለው መስሪያ ቤት አካሄድ ነው።የማሳጣት
የፖሊስ እና ሌሎች ተቋማት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰጠት አባዜ በሌሎች ተቋማት እንደነገሩ እንኳን ያለውን በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት የመፈተሽ ሂደት የማስቀረት አዝማሚያ እንደሆነ የህግ አማካሪው ያስረዳሉ።አካሄዱ ተቋማቱ አሰራራቸው ግልፅነት የጎደለው እንዲሆን ያደርገዋል ሲሉም ይከራከራሉ።
“ተቋማት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስር ሲሆኑ ተጠያቂነት ይጠፋል። መፈራት ይጀምራሉ” ይላሉ የህግ አማካሪው። “ይህ አይነት አካሄድ ጥብቅ ቁጥጥርን ለማምለጥ የሚደረግ ነው።”
ባለሙያዎቹ ከየዘርፋቸው አንጻር የፌደራል ፖሊስን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስር መውደቅ ቢተቹም በአንድ ነገር ግን ሁሉም እርግጠኛ ናቸው— ማሻሻያው መሰረታዊ የሆነ ለውጥ እንደማያመጣ ።