ሰኔ፣ 2008

ተጻፈ፣

በሙሔ ሐዘን ጨርቆስ

እንዴት ናችሁ የዋዜማ ታዳሚዎች?

ከትናንትና ወዲያ ጋሽ አበራ ሞላ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጋር ቆሞ ሲያስነጥስ አየሁት፡፡ እነዚህ ሰዎች ቆሻሻ የትም እየደፉ አሳበዱት፡፡ ቁመቱ ከምን ጊዜውም ረዝሞ ታየኝ፡፡ በሹራብ ላይ ቡናማ ጃኬት ደርቧል፡፡ ከአንገቱ ላይ ቡናማ ስካርፍ ጠምጥሟል፡፡ እኔ እያየሁት ብቻ ሦስት ጊዜ አስነጠሰ፡፡ ሲያስነጥስ ድምጹ ከአፍንጫው ሳይሆን ከክራሩ እንደወጣ ሁሉ ተመስጬ አዳመጥኩት። በአካባቢው የከተማ ባቡራችን አስገምጋሚ ድምጽ ባይኖር ሲያስነጥስ ግዮን ሆቴል ማዶ የሚሰማ መሰለኝ፡፡ ‹‹እንጥሼ….ሼ ከተፍ….››። ከግራ ኪሱ መሐረብ አውጥቶ አፍንጫውን አጸዳድቶ መሐረቡን ወደ ኪሱ ሲመልስ እንደ ልዩ ትእይንት አየሁት፡፡ ጠጋ ብዬ ሳየው ጉንፋን እንደያዘው አስተዋልኩ፡፡ ኃይለኛ ጉንፋን፡፡ አሳዘነኝ፡፡

እኔ ራሴ ሳርስ የሚያስንቅ ጉንፋን ደፍቆኝ ገና መነሳቴ ነው፡፡ አንድ ሳምንት ቤት አዋለኝ፡፡ በዚህ እንደ ጀሐነም እሳት በሚፋጅ ኑሮ ‹‹ጉንፋን ቤት አዋለኝ›› ማለቴ እንደሚያስቀይማችሁ አውቃለሁ፡፡ ግን ምን ላድርግ፡፡ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ አሁን እየተሻለኝ ነው፡፡

Merkato 2ዉድ የአገር ሰው ጦማር ታዳሚዎች!

በችግሩ እየተሰቃየን ያለነው እኔና ጋሽ አበራ ሞላ ብቻ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ፈጣሪ ምስክሬ ነው…በዚህ ሰሞን አብዛኛውን አዲሳቤ ጉንፋን እያንደፋደፈው ይገኛል፡፡ እንደለመደው የብርቱካን ጭማቂ አፍልቶ እንዳይጠጣ ሌላ ራስ ምታት መቀስቀስ ይኾናል።  ብርቱካን ኪሎው ስንት እንደገባ ሰምታችኋል? 38 ብር፡፡ መጠናቸው የጥምቀት ሎሚ የሚያካክሉ ናቸው ለዚያውም፡፡ ክፉ ጊዜ!

ለጉንፋን መበራከት ተጠያቂው ማነው ካላችሁኝ ገዢው ፓርቲ ነው መልሴ፤ የራሱንም ሆነ የአካባቢን ንጽሕና አይጠብቅማ፡፡ ለብርቱካን መጠን መቀነስ ተጠያቂው ማን ነው ካላችሁኝ፤ አሁንም ገዢው ፓርቲ ነው መልሴ፡፡ መርቲን ለአላሙዲ ሸጠብና!  ሼህ አላሙዲ ለብርቱካን መወደድ ብቻ ሳይሆን ለአዲስ አበባ ሕዝብ በጉንፋን መሰቃየት ዋናው ተጠያቂ ናቸው እላለሁ፡፡ ዘሄግ ወስጄ ብገትራቸው ደስ ባለኝ፡፡ ለምን በሉኝ! እዚህም እዚያም የግንባታ ድስት ጥደው ፈጁና፡፡ ለመኾኑ እሳቸው ያላጠሩት ሰፈር አለ እንዴ? ሜክሲኮ፣ካዛንቺስ፣ ፒያሳ፣ብሔራዊ፣ ሳርቤት…፡፡ ደግሞኮ አንዱም አይሠራ፡፡ ፒያሳን ለ 18 ዓመት አጥረው ዙርያውን ገላጣ የሕዝብ ሽንት ቤት አደረጉት፡፡ ከአጥሩ የሚወጣው ሽታ እንኳን እኛን ተራ ዜጎቹን ቀርቶ ማዘጋጃው ቤት ያሉትን ከንቲባ አላሰራ እያላቸው ነው፡፡ እሳቸው ግን የሼሁ ብድር አለባቸው መሰለኝ አይቀሟቸውም፡፡

ሸራተን ፖሊስ ጋራዥን አምስት ዓመት ሙሉ አጥረው የሌባ መደበቂያ አደረጉት፡፡ የፍልዉኃን  መስኪድ ማዶ በቆርቆሮ አጥረው የደሀው ‹‹የተፈጥሮ ጥሪ›› ማነጣጠሪያ ማዕከል አደረጉት፡፡ ካዛንቺስ ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጎን ያጠሩትም ቦታ ኩሬ በመስራቱ የከተማዋ የወባ ማከፋፈያ ማዕከል ሆኗል፡፡

Around Churchill Road sidewalk PHOTO-Wazema
Around Churchill Road sidewalk PHOTO-Wazema

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

እመኑኝ ጉንፋን መጥፎ በሽታ ነው፡፡ በዋናነት የሚያጠቃው ደግሞ ደሀውን ከተሜ  ነው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ጓደኞቼ በሙሉ ጉንፋን ታመዋል፡፡ ዛሬ ጠዋት ታክሲ ዉስጥ በአንድ ጊዜ አምስት ተሳፋሪዎች በተመሳሳይ ደቂቃ ሲያስሉ አይቻለሁ፡፡ እንዲያውም ሾፌሩ ወራጅ የተባለ መስሎት ጥግ ይዞ ቆመና እሱም በመስኮቱ ብቅ ብሎ ያፍንጫውን ሸክም አቃለለ ፡፡

ተራ አስከባሪዎች ይስላሉ፣ ወያሎች ‹‹መልስ›› በተባሉ ቁጥር በየመሐሉ ያስነጥሳሉ፡፡ አንገታቸውን በመስኮት አስግገው በጉንፋን ባጎረና ድምጻቸው ይጣራሉ፡፡

ፖስታ ቤት ጋር ሲወርዱ አደገኛ ጠረን የሚያመነጩ አምስት ክፍታፍ ገንዳዎች አፋቸውን ከፍተው ይቀበልዎታል፡፡ ክርፋታቸው ሽታ ብቻ ሳይኾን ምጽም አውጥቶ የሚጮህ ይመስላል፡፡ ከዘውዲቱ ሆስፒታል ወደ ፖስታ ቤት የምታስወጣዋን ቀጭን አስፋልት ወንድ የሆነ አይሻገራትም፡፡ ታዲያ ፖስታ ቤት አካባቢ ብቻ አይደለም የከረፋው፤ ቄራም፣ ሳሪስም፣ ጎፋም ላፍቶም አቦም፣ መሻለኪያም፣ ጠመንጃ ያዥም ያው ናቸው፡፡ የአዲሳባ ሰፈሮች ሁሉ ይሸታሉ፡፡ ቀድሞ ውድ ሽቶ በተቀቡ ዘመናይ ወይዛዝር ይታወድ የነበረው የቦሌ መድኃኒዓለም አካባቢ እንኳ ራሱን መጠበቅ አቅቶት መዝረክረክ ጀምሯል፡፡ ከተማዋ ውስጥ ጽዱ ቦታ ያለው ቤተ መንግሥትና ሸራተን ግቢ ዉስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ለስላቁ ማክራሪያ የሚኾነው ጉድ ደግሞ  ይህኛው ነው ‹‹የአዲስ አበባ ጽዱና አረንጓዴ ጽሕፈት ቤት›› የሚባለው መሥሪያ ቤት ራሱ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳው ከተነሳለት 3 ሳምንት አልፎታል ብለውኛል የመስሪያ ቤቱ ባልደረቦች፡፡

አንባቢዎቼ ሆይ!

የሸገር ጉንፋኑ ለማን በጀ ብትሉኝ ለጀብሎ እላችኋለሁ፡፡ ጀብሎ ነጋዴ ባለ 12 ብሩን ጥቅል ሶፍት ቆራርጦ ለሦስት ዙር መናፈጫ የሚበቃ ዝርዝር ሶፍት ይሰራበታል፡፡ ከዚያም አንድ ጥቅል ሶፍት በአንድ ብር ይቸረችራል፡፡ ሶፍቱን የሚሸጡት ደግሞ የጎዳና ልጆች ናቸው፡፡ ወይም ደግሞ በከባድ ድህነት ዉስጥ ብዙ ልጅ የወለዱ ደፋር የአዲሳባ እናቶች፡፡ ልጆቻቸውን ሶፍት እያሸከሙ በየትራፊክ መብራቱ ያሰማሯቸዋል፡፡ እነርሱ ግን እንደ ክፉ ትራፊክ ፖሊስ አንድ ጥግ ይዘው የገበያውን ሁኔታ በሩቁ ይከታተላሉ፡፡ የሚገርመው ሁሉም ዝርዝር ሶፍት የሚሸጡ የጎዳና ልጆች ንፍጣም መሆናቸው ነው፡፡ ንፍጣቸውን አንድ ጊዜ ወደ ዉስጥ በኃይል ይስቡትና ‹‹እናቱ እስቲ ሶፍት ግዢኝ›› ይላሉ፡፡ አዲሳባ ገዢዎቿን ብቻ ሳይሆን ዜጎቿን እየመሰለች ነው፡፡

ክቡራትና ክቡራን!

ለምን ይህ ሁሉ ዜጋ በተመሳሳይ ጊዜ ለጉንፋን እንደተጋለጠ ለጊዜው የተባለ ነገር የለም፡፡ ሁሉን አዋቂ (Omnipotent) እና ሁሉን ተንታኝ (Omnianalyst) የሆኑት ኤፍ ኤሞቻችን ግን ነገሩ ከብራዚል ወለዱ ዚካ ቫይረስ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር ያለ መስሏቸውም እንደኾነ እንጃ  ሰሞኑን ከአዲሳባው ጉንፋን ይልቅ አብዝተው ስለ ሪዮ ኦሎምፒክ እየተንጰረጰሩ ነው፡፡ ብሥራት ‹‹ኤፍ ኤም›› በበኩሉ ጉንፋን ለባርሴሎናው ንጉሥ ሜሲም የማይመለስ አደገኛ ቫይረስ እንደሆነ በመግለጽ ሕዝቡ አብዝቶ ከማማረር እንዲቆጠብ እየመከረ ነው፡፡

ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማወጋችሁ ቁምነገር ቢኖር ከተማችን አዲስ አበባ በቆሻሻ ክምር እየተዋጠች ስለመሆኑ ነው፡፡

###

እቴጌዋ ፊንፊኔን ‹‹አዲስ አበባ›› ብለው ስም ያወጡላት ቀን ምኞታቸውን የሚጻረር ሰይጣን ፍለውሀ ዉስጥ መሽጎ ነበር የሚል አፈ ታሪክ ተጽፎ ከሆነ ንገሩኝ፡፡ ካልተጻፈ ግን እኔው እጽፈዋለሁ፡፡ ሸገር የስሟን ተቃራኒ ለመሆን ባለፉት 130 ዓመታት ብዙ ደክማለች፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ድካሟ ፍሬ እያፈራላት ነው፡፡ እንደዘንድሮ ግን ተሳክቶላት አያውቅም፡፡

የሞጃ ዝርዝር በማውጣት የምናውቀው ፎርብስ መጽሔት የዓለም ከተሞችን በቆሻሻነት አወዳድሮ ለአዲስ አበባ የሚገባትን ሜዳሊያ በቅርቡ ሸልሟታል፡፡ አልሰማችሁ ከሆነ እንጃ እንጂ ከተማችን የአዘርባጃኗን ‹‹ባኩ›› እና የባንግላዲሸዋን ዳካን አስቀድማ በመግባት የዓለም 6ኛዋ እድፋም ከተማ ተብላለች። ይሄኔኮ ከንቲባ ድሪባ ይህን ጉድ አልሰሙ ይኾናል።

እኔን የገረመኝ ግጥምጥሞሹ ነው፡፡ የፎርብስ የደረጃ ሰንጠረዥ በወጣ በሳምንቱ የአዲስ አበባን ቆሻሻ የሚያነሱ መኪኖች አድማ መቱ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ረጲ ቆሼ መዘጋቱን ተከትሎ አዲሱ ቆሻሻ መጣያ ከአዲስ አበባ ርቆ በመገኘቱ ክፍያ እንዲሻሻልላቸው ያነሱት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ ነው፡፡

###

Merkatoዉድ የጦማሬ ታዳሚዎች!

ዝም ብዬ ነገር ከማበዛ መሬት ላይ ያለውን እውነት ብተርክላችሁ ይበልጥ ያለንበትን ሁኔታ ትረዳላችሁ ብዬ አሰብኩ፡፡

የቆሻሻ ክምሮች የአቡነ ጴጥሮስንም ሆነ የድል ሀውልት ለመጋረድ ፉክክር የገጠሙ መስለዋል ፡፡ ለምሳሌ አንድ ለናቱ በሆነው የቸርችል ጎዳና ‹‹ሐሮን ታወር›› ፊት ለፊት የጎዳና ልጆች መኪና የሚያጥቡበት ስፍራ አለ፡፡ አጠገቡ ሕብረት ኢንሹራንስ በአቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ አጋፋሪነት በ300 ሚሊዮን ብር ያስገነባው ባለ 15 ፎቅ ዋና ጽሕፈት ቤት በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ከርሱ ጎን እውቁ የነርቭ ስፔሻሊስት ዶክተር ጉታ ላለፉት አስር ዓመታት አንድ አንድ ጡብ እንደ ነርቭ በጥንቃቄ እያስቀመጡ ያስገነቡት ባለ 13 ፎቅ ሕንጻ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ኩሩ የቸርችል ጎዳና አካፋይ ታዲያ መቶ ሀምሳ ጆንያ የበሰበሰ ቆሻሻ ተከምሮ ይታያል፡፡ ክምሩ ባለፉት ሁለት ወራት ያለማቋረጥ ወደላይ እየተቆለለ አምስት መቶ ደርሷል፡፡ በቅርቡ በቁመት የማዘጋጃ ቤቱን ሰዓት እንደሚጋርድ እወራረዳለሁ፡፡ ታዲያ ይሄ ምኑ ይገርማል ትሉኝ ይሆናል፡፡ ቆሻሻው ለምን ያህል ጊዜ ሳይነሳ እዚያ ስፍራ እንደቆየ ስነግራችሁ ብቻ ነው ነገሬ የሚገባችሁ፡፡ ለ68 ቀናት፡፡ አሁንም አለ፡፡ ኤልኒኖ ያወናበደው ዝናብና ፀሐይ ቆሻሻው ላይ ተፈራርቆበት በአካባቢው የፈጠረው ጠረን አፍንጫን እንደ ጉንጅ ከነስሩ መንግሎ መንቀል የሚያስችል ነው፡፡ ሰዎች ከዚያ ስፍራ የሚያልፉት በሩጫ ነው፡፡ በመቶ ሜትር ሩጫ፡፡ ‹‹ስፕሪንት›› እያደረጉ፡፡

ባምቢስ ወረድ ብሎ ‹‹ሰሜ ባላገሩ ድልድይ›› መዞርያ አካባቢ ጋሽ አበራ ሞላ ከአመታት በፊት የሚያምር ግቢና ካፌ አድርጎት የነበረ ገላጣ ስፍራ አለ፡፡ ዛሬ ታዲያ ይስ ስፍራ አንድ ሺ አንድ መቶ የቆሻሻ ጆንያ ተደፍቶበት በአካባቢው እንኳን ሰው መኪናም ቢኾን ቀስ ብሎ መሄድ አይችልም፡፡ ስለሺ ደምሴ ወዶ አይደለም ረዝሞ የጎበጠው፡፡ ቢያስቀይሙት እንጂ…፡፡

መስቀል ፍላወር አዲሱ አደባባይ ጎን በግ ተራ የሚባለው ቦታ ያለው የቆሻሻ ገንዳ እላዩ ላይ የተደፋበት ቆሻሻ ከመብዛቱ የተነሳ ገንዳው ተሰውሯል፡፡ ሳሪስ ከአቦ ማዞርያ ወደ ቡልቡላ የሚወስደው መንገድ ላይ፣ ፒያሳ አትክልት ተራና አካባቢው፣ አያት አዲስ መንደርና አካባቢው፣ አዲሱ ገበያ ታክሲ መጨረሻ…ሁሉም ያው ናቸው፡፡

Ambassador area PHOTO -Wazema
Ambassador area PHOTO -Wazema

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

መንግሥት ባመነው 3 ሚሊዮን ሕዝብ ሸገር ላይ ይኖራል፡፡ እኔ በቆጠርኩት 6 ሚሊዮን እንሞላለን፡፡ መንግሥት በሚለው 550 ቶን ደረቅ ቆሻሻ አዲሳበቤ በየቀኑ ያመርታል፡፡ እኔ ባነበብኩት 3 ሚሊዮን ቶን ቆሻሻ በዓመት ይጣላል፡፡ ከዚህ ዉስጥ 76 ከመቶ ደረቅ ቆሻሻ ከመኖርያ ቤቶች የሚወጣ ነው፡፡ 18 በመቶዉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያመርቱት ነው፡፡ 6 በመቶው ከጎዳና ላይ የሚጠረግ ነው፡፡ ከዚህ የቆሻሻ ምርት መንግሥት መልቀም የሚችለው 76 በመቶው ብቻ ነው፡፡ በተቀረው መቶኛ የአዲስ አበባ ሕዝብ በጉንፋን ፍዳውን ያያል፡፡

መንግሥት በሁለት መንገድ ቆሻሻ ያነሳል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ወጣቶች ከየቤቱ በጆንያ እየከተቱ የሚሰበስቡት ቆሻሻ በጋሪ እየተገፋ፣ ጋሪው ከሌለም በትከሻ ታዝሎ ወደ ቆሻሻ ገንዳ ይደርሳል፡፡ አንድ በሉ፡፡ መስተዳደሩ ደግሞ የገንዳ ቆሻሻዎችን በመኪና ጭኖ ሰንዳፋ ያደርሳቸዋል፡፡ ይህ ሂደት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለአንድ ቀን እንኳ ዝንፍ ካለ አዲሳባ መሽተት ትጀምራለች፡፡ አሁን የሆነውም ይህ ነው፡፡

መስተዳደሩ የአዲስ አበባን ሕዝብ በ549 የቆሻሻ ዞኖች ከፍሎታል፡፡ እያንዳንዱ ዞን በአማካይ አንድ ሺ አባወራ ይኖርበታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ 568 የጽዳት ማኅበራት ተሰማርተዋል፡፡ 4ሺ የቆሻሻ ለቃሚ ደመወዝ ይሰፈርለታል፡፡ በያንዳንዱ ማኅበር በአማካይ 10 ጎረምሶች የኢህአዴግ አባልነት ካርድ ይዘው ቆሻሻ ይገፋሉ፡፡ ፓርቲው ስብሰባ ሲጠራቸው የቆሻሻ ጆንያቸውን የትም ጥለው ይሰበሰባሉ፡፡ ኑሮ ነውና በነርሱ ማን ይፈርዳል?

ቆሻሻን ባይነት ባይነቱ የመለየት ሥራ ለመስራት መስተዳደሩ አቅሙም እውቀቱም ስለሌለው ይህ የሚሰራው በባህላዊ ዘዴ ነው፡፡ ይኸውም ቤተሰብ ጎማ፣ ጠርሙስ የዉሃ ላስቲኮችና የአገልግሎት ዘመናቸው ያበቁ የቤት ቁሳቁሶችን ለቆራሌው ይሸጣል፡፡ ቆራሌው ምናለሽ ተራ ወስዶ ይቸበችበዋል፡፡ ምናለሽ ተራ ጎማውን ለቤቲ ሶልሬብልስ፣ ብረቱን ለአቢሲኒያ ስቲልና ለሜቴክ ይሸጣል፡፡ በሌላ ቋንቋ ኢትዮጰያ ዉስጥ ለጊዜው ‹‹ሪሳይክሊንግ›› እየተሰራ ያለው  በዚህ መንገድ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መስተዳደሩ ለአቅመ ሪሳይክሊን ስላልበቃ ለጊዜው ቆሻሻን መሰብሰብ፣ ማጓጓዝና መድፋት ላይ ብቻ አትኩሮ እየሰራ ይገኛል፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ ላይ ያነበብኩት ዜና ትዝ አለኝ፡፡ አይስላንድ በከፍተኛ የቆሻሻ እጥረት ተመታች ይላል ርዕሱ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ምርቶቻቸው የሚፈበረኩትት ቆሻሻ ሪሳይክል እየተደረገ በመሆኑ ነው፡፡ድንገት ሪሳይክል የሚደረግ ቆሻሻ ጠፋ፡፡ ዜናው እንዳተተው ችግሩን ለመቅረፍ አይስላንድ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ ከስክሳ ከስዊድን ቆሻሻ ገዛቻት፡፡

ዉድ የአገር ቤት ጦማር ታዳሚዎች!

ክቡራትና ክቡራን!

ደቡብ ምዕራብ አዲስ አበባ የሚገኘው የረጲው የቆሻሻ መድፊያ ወይም በተለምዶ አጠራሩ ቆሼ  የአዲስ አበባን እድፍ ሲቀበል ግማሽ ምዕተ አመት ሊሞላው አንድ ዓመት ቀረው፡፡

ረጲ ከመሐል ፒያሳ 13 ኪሎሜትር ብቻ ስትርቅ የቆሻሻ መጣያው ሜዳ 25 ሄክታር ስፋት አለው፡፡ ቆሼ እንደተቀረው ዓለም ምንም አይነት የቆሻሻ ማሰባጠር፣ ማበስበስ፣ መለየት፣ መበተን፣ መዘወር የመሰሉ ዉስብስብ ሂደቶችን የማይፈልግ ነው፡፡ በአጭሩ ከሁሉም አቅጣጫ የተሰበሰበ ቆሻሻ በመኪና ተጭኖ ይደፋል፡፡ የተደፋው ቆሻሻ ኑሮ በደፋቻቸው ዜጎች ይበረበራል፡፡ ያልተጋጠ አጥንት፣ ብዙ ያልበሰበሰ ማንጎ፣ ቅቤ የበዛበት ክትፎ ተለቅሞ ይበላል፡፡ ከዚያ ዶዘር መጥቶ የቆሻሻውን ክምር ንዶ ይበትነዋል፡፡ ይህ ነው የቆሼ የ49 ዓመት ታሪክ በአጭሩ፡፡1500 የሚሆኑ ዜጎች ኑሯቸው የተመሰረተው በቆሼ ላይ ስለነበር ወደ ሰንዳፋ የተደረገው ሽግግር ብዙዎችን አስለቅሷል፡፡

ዉድ ተጦማሪዎቼ!

ቆሼን ከተቀረው ዓለም የቆሻሻ ማከማቻዎች ምን ልዩ ያደርገዋል ካላችሁ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በሉ፡፡

1ኛ. ዙርያውን በመኖርያ ቤቶች የተከበበ መሆኑ፣

2ኛ. ብዙ የቆሼ አካባቢ ነዋሪዎች በሚጥል በሽታ የሚሰቃዩ ቢኾንም የችግሩን መንስዔ ግድ ሰጥቶት የተመራመረ የጤና ተቋም አለመኖሩ፣

3ኛ› ቆሻሻው ከተከመረ በኋላ እላዩ ላይ አፈር አለመደፋቱ፣

4ኛ. ጠረን ተከላካይ ንጥረ ነገር አለመረጨቱ፣

5ኛ. በታሪኩ አንድም ጊዜ በአጥር ለመከለል አለመሞከሩ፣ ናቸው፡፡

ከዓመት በፊት ቆሼ ተዘጋ፡፡ ቆሼ ተዘግቶ ብቻ አላበቃም፡፡ 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የኃይል ማመንጫ እየተገነባበት ነው ተባለ፡፡ ጥሩ! ያርግልን፡፡ ያርግላቸው፡፡ እኔ ግን ይሄን መብራት እንኳን ከቆሻሻ አመንጭተውት ከተከዜ የመነጨውም እየጠፋብን ነው ስል ስጋቴን ገለጽኩ፡፡ የሰማኝ የለም፡፡ ደግሞ ከቆሻሻ ያመነጨ አንድም የአፍሪካ አገር ባለመኖሩ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን የመጀመርያው ያደርጋታል ይሉናል፡፡ በምንስ ቢሆን እኛ መቼ ሁለተኛ ሆነን እናውቅና!  ሯጮቻችን ራሳቸው ሁለተኛ ላለመሆን ዉድድር አቋርጠው መዉጣት ጀምረው የለም እንዴ?

ይህ ቆሼን የኃይል ቋት ለማድረግ የተጀመረው ሥራ 75 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡ 2.6 ቢሊየን ብር የፈጀ ገንዘብ ፈሶበታል፡፡ ግንባታው በ2006 ጥቅምት ወር ነው የተጀመረው፡፡ የተወሰነውን የቆሻሻ መድፊያ ክፍል አረንጓዴ ፓርክ ለማድረግም ሥራዎች እየተሰሩ ነው ይሉናል፡፡ የኛ ምላሽ ግን እስኪ አረንጓዴውን ተዉትና መጀመርያ በየጎዳናው የተዝረከረከውን  ቆሻሻ አንሱልን የሚል ነው፡፡ ‹‹ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ›› እንዲል ዶክተር መረራ፡፡

ሰንዳፋ ናት ቀጣይዋ ረጲ፡፡ እዚያ ደግሞ 31 ሚሊዮን ዩሮ የሚፈጅ የቆሻሻ ማከማቻ ተገንብቷል ነው ያሉን፡፡ ከዚህ ዉስጥ 20 ሚሊዮኑን እንደፈረደብን ከፈረንሳይ መንግስት ነው የተበደርነው፡፡ ብድራችን ከቆሻሻው ክምር አልበዛም ጎበዝ!

አሁን የኔ ስጋት ምንድነው? በቆሻሻ ወለድ በሽታ ታመን እንዳንሞት፡፡ ይኸው ስንት ዘመን የኃይል ማመንጫ ግድብ ስንገነባ ስንገነባ ስንገነባ…ከጨለማ ተላቀን አናውቅ፡፡ ይኸው ስንት ዘመን…፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹የቆሻሻ ማከማቻ እየገነባን ነው ታገሱን›› ብለው ልጆቻችንን በቆሻሻ ወለድ በሽታ እንዳይጨርሷቸው ነው ስጋቴ፡፡

በቅርቡ ባነበብኩትና ፎረም ፎር ኤንቫይሮመንት ባጠናው አንድ ጥናት የከተማዋ 30 በመቶ ነዋሪ በጎዳና ላይ የሚጸዳዳ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ ባነበብኩት ሌላ ዜና ላይ ደግሞ የአዲስ አበባ መስተዳደር የቆሻሻ ገንዳ እጥረት እንጂ የቆሻሻ አንሺዎች እጥረት እንዳላጋጠመው በራሱ ሚዲያ ተናግሯል፡፡ እንግዲህ ይታያችሁ! በሌላው ዓለም አስፋልትን እንደ ሳሎን በኦሞ ወልውለው የሚያጥቡ መኪናዎች ሲሰማራ እኛ የቆሻሻ ገንዳ እንኳን የለንም፡፡

ኸረ ለመሆኑ ይሄ ከዉሀ ቢል ጋራ የምንከፍለው 2 ፐርሰንት ክፍያ የት ነው የሚገባው? ለስብሰባቸው የታሸገ ውኃ እየገዙበት ይሆን እንዴ? ለምን የታሸገ ዉኃ ከሚገዙ ገንዳ አይገዙም?

ዉድ የጦማሬ ታጋሽ አንባቢዎች!

በጽናት ስላነበባችሁኝ እመርቃችኋለሁ፡፡ እግዜአብሔር ኢትዮጵያን ከ ‹‹አተት›› ይጠብቃት፡፡ ለምን በሉኝ፡፡

(ይህንን ጦማር እየጻፍኩ የማሳረጊያ ምዕራፍ ላይ ስደርስ ብሔራዊው ቴሌቪዥን በ2 ሰዓት የምሽት ዜና እወጃው ‹‹አተት›› አዲስ አበባ ዉስጥ መከሰቱን አሳውቆ ሕብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና እንዲጠብቅ አሳስቧል) የምሬን ነው፡፡

እደግመዋለሁ!

እግዜአብሔር ኢትዮጵያን ከ‹‹አተት›› ይጠብቅ! አሜን!