ዋዜማ ራዲዮ- ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረው የአዳም ረታ ዳጎስ ያለ ልቦለድ በሚቀጥለው ሳምንት ገበያ ላይ ይውላል። “የስንብት ቀለማት” የተሰኘው የአዳም አዲሱ መጽሐፍ ቀድሞ እንደተነገረለት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ገጾች አሉት።
መጽሐፉ በስምንት ምዕራፎች እና በ46 ንዑስ ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። ፍቅር፣ ፖለቲካ፣ የሀገር ጉዳዮች የተካተቱበት መጽሐፉ ዋነኛ መቼቱን ያደረግው በአዲስ አበባዎቹ ሳሪስ እና ንፉስ ስልክ ሰፈሮች ነው።
“ሳሪስ ውስጥ የተደረጉ እያንዳንዱ ለውጦች የታሪኩ አካሎች ናቸው” ይላል የመጽሐፉ አሳታሚ አቤል ሰይፈ። ” አዳም ሰፈርን እንደ ገጽ ባህሪ ተጠቅሟል።”
በዚህ መፅሀፉ አዳም ከሰፈር ሌላ ውሻን በገጸ-ባህሪነት አካቷል።
በመጽሐፉ የመጨረሻ 20 ገጾች ስለ “የስንብት ቀለማት” ዳሰሳቸውን ያሰፈሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ-ፅሁፍ መምህር ቴዎድሮስ ገብሬ አዳም ረታ በሀገራችን የአጻጻፍ ዘዬ ባልተለመደ መልኩ በቀደሙት ስራዎቹ “መንገድን” በአሁኑ ደግሞ “ሰፈርን” እንደ ገጸ ባህሪ መጠቀሙ ለየት እንደሚያደርገው ጽፈዋል። አዳም በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ አዲስ ልማድ ማምጣቱንም የመፅሀፉን ረቂቅ ያነበቡ አድንቀዋል።
ደራሲው ከዚህ በፊት አተኩሮ ከሚፅፍበት የደርግ ዘመን በወጣ መልኩ በአዲሱ መጽሐፉ ለአሁኑ ጊዜ ሰፊውን ቦታ ሰጥቷል። በምልሰት ከሚወሳው የወታደራዊው አገዛዝ እና በወቅቱ በደርግ እና ኢህአፓ የፖለቲካ ጎራ ተሰልፈው ከነበሩት የ “ያ ትውልድ” የተወሰኑ ገጸ-ባህሪያት ውጭ የዘመኑ ወጣቶች የመጽሐፉ ሞተር ሆነው ተስለዋል።
አዳም በሌሎቹ ድርሰቶቹ እንዳደረገው በዚህኛው ስራውም በእውን የሚታወቁ አርቲስቶችን በገጸ-ባህሪያትነት ተጠቅሟል። ከታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ ተመሳሳይ ሚና በመጽሐፉ እንደተሰጠው ረቂቁን ያነበቡ ይናገራሉ።
በረቂቅ ደረጃ እያለ ተደጋጋሚ የአርትኦት ስራ እንደተደረገለት የተነገረለት “የስንብት ቀለማት” በመጽሐፍ ለመውጣት ስድስት አመታትን ወስዷል። አጀማመሩ ላይ “ከሰማይ የወረደ ፍርፍር” በተሰኘው የአዳም የአጭር ልቦለዶች መድብል ውስጥ ለመደመር የተዘጋጀ ከ35 እስከ 40 ገጽ የሚፈጅ ተረክ የነበረው “የስንብት ቀለማት” እየሰፋ ሄዶ 960 ገጽ የፈጀ መጽሐፍ እንደወጣው የኃላ ታሪኩን የሚያውቁ ያስረዳሉ።
“አዳም እንደዚህ የለፋበት ስራ የለም” ይላል ለአዳም ቅርብ የሆነ የዋዜማ ምንጭ ረጅም ጊዜ ስለወሰደው መጽሐፍ ሲናገር። “አዳም ቡና እየጠጣ፣ ጫጫታ ሳይረብሸው የሚጽፍ ነው። ይሄኛውን ግን ትኩረት ሰጥቶ የሰራው ነው።”
“ሌሎቹ ስራዎቹን ‘አስቸግረውኛል’ ሲል ሰምቼ አላውቅም። ይህኛው ግን እርሱ ራሱ ‘በጣም አስለፍቶኛል’ ይላል።”
አዳም በድርሰቱ ውስጥ በሚጨምራቸው የግርጌ ማስታወሻዎች (footnotes)፣ “ግራፊክሶች” እና በተለየ ቀለም በሚጻፉ ቃላት ምክንያት የየመጽሐፍቱ አርትኦትና ቅንብር ጊዜ እንዲወስድ ምክንያት ይሆናል። በአዲሱ መጽሐፉም ተመሳሳይ የአጻጻፍ ዘዬ ተከትሏል።
እነዚህን ጥንቃቄ የሚጠይቁ የአዳም ልዩ ዘዬዎችን በኃላፊነት ተረክቦ የቅንብር እና ህትመት ክትትል ስራውን እያከናወነ የሚገኘው የደራሲውን ቀደምት መጽሐፍት ለንባብ ያበቃው “ማህሌት አሳታሚ”፣ በአዲሱ ስሙ “ሀሳብ አሳታሚ” ነው።
በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ገበያ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው “የስንብት ቀለማት” የገጾቹ ህትመት መጠናቀቁን አሳታሚው ይገልጻል።የመጽሐፉን የህትመት ስራ እየሰራ የሚገኘው ሮሆቦት ማተሚያ ቤት በአሁኑ ወቅት የሽፋን ገጽ ህትመት ላይ መድረሱንም ይናገራል።
መጽሐፉ “B5” በሚባለው መጠን የሚታተም በመሆኑ እና የገጽ ብዛቱም ከፍ ያለ በመሆኑ የማተሚያ ዋጋውን እንዳናረው አቤል ያስረዳል። በዚህም ምክንያት የመጽሐፉ የኮፒ ብዛት ላይ እና የመሸጫ ዋጋ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን ያብራራል።
“የስንብት ቀለማት” የመጀመሪያ እትም በሌሎቹ የአዳም መጽሐፍት እንደተለመደው ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ በሚደርስ ብዛት ሳይሆን በአምስት ሺህ ኮፒ ብቻ ለገበያ ይቀርባል። የህትመት አጠቃላይ ክፍያው ብቻ አንድ ሚሊዮን ብር እንደፈጀ የተነገረለት አዲሱ መጽሐፍ ዋጋውም ቆንጠጥ የሚያደርግ ሆኗል። በገበያ ዋጋ አንዱ መጽሐፍ 350 ብር ይጠየቅበታል።