FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር 500,000 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በ2012 ዓ.ም በመስተዳድሩ የቤቶች ኤጄንሲ እና ከቤት አልሚዎች ጋር ለመስራት እና ለተጠቃሚዎች ለማዳረስ የያዘውን እቅድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የዚህ እቅድ አካል የሆነው የ20 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በከተማ መስተዳድሩ ምከትል ከንቲባ ታከለ ኡማ አማካኝነት ጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡

የቤት ፍላጎትን ለሟሟለት የታሰቡት አማራጮች ላይ ብዙዎች ቢስማሙም በቁጥሮቹ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ከግንባታ ሳይቶች ፣ ከመሰረተ ልማት ፣ ከመስተዳድሩ ቅቡልነት ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በሚገነቡበት ሳይቶች በረጅም ጊዜ ሊገጥሙት ከሚችሉት የመሰረተ ልማት ችግሮች፣ ከከተማ ልማት እና ፕላን እንዲሁም ከማቴሪያል አቅርቦት እንጻር ከባለሙያዎች እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጥያቄዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተነሱ ነው፡፡

በተለይም በከተማው ውስጥ ለግንባታ የተመረጡት ቦታዎች መካከል ለከተማ አቀፍ አገልግሎት እንዲውሉ ለረጅም አመታት ተጠብቀው ጊዜአቸውን ጠብቀው ለመገንባት የቆዩት ቦታዎችን ለዚህ አገልግሎት ማዋሉ የሚያስከትለው ትልቅ ፈተና እና የወደፊት ችግሮች በደንብ የታሰበበባቸው አይመስልም የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡

ከለገሀር ሼመንደፈር ህንፃ በስተግራ ለዋና የትራንስፖርት መናኸሪያነት የታቀደው ቦታ ለምሳሌ ለከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማዕከል እንዲሆን የታቀደ፤ የተለያዩ የከተማ አቀፍ ብቻ ሳይሆኑ አገር አቀፍ የትራንስፖርት መጓጓዣዎች ሊያስተናግድ እና ሊያሳልጥ የሚችል፤ በቀን በመቶ ሺዎችን የሚያስተናገድ እንዲሆን የታሰበ ቦታ ነው፡፡

ይህ ለከተማው የወደፊት እድገት በታሪክም ሆነ በከተማ ፕላኒንግ ወሳኝ የሆነ ቦታ ከዚህ ሰፊ እንቅስቃሴ ጋር ተዛማጅ የሆኑ የአገልግሎት መስጫ ልማቶችን አቀናጅቶ የሚለማ ቦታ እንዲሆን እንደታቀደ እና ለዓመታት የተሰሩ ፣ እየተሰሩ እና ለወደፊቱ የሚሰሩ የትራንስፓርት ሥርዓት ዋና ቦታ እንደሆነ ይገልጻሉ ፡፡

በንፅፅር ትንሽ ቁጥር ላላቸው መኖርያ ቤቶች የከተማዋን ዋነኛ የትራንስፓርት መናኸሪያን አሳልፎ መስጠት ከፕላኒንግ ፣ ከትራንስፓርት እና ከከተማ ቦታ አጠቃቀም አንፃር ትክክል አይደለም ብለው የሚከራከሩ ባለሙያዎች ከእዚህ በፊት የተሰሩ የዚህ መሰል ስህተቶችን በከፍተኛ ደረጃ እና ለማረም በሚከብድ መልኩ መድገም እንደሆነ እና የፓለቲካ ጉዳትም ሊያመጣ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ሌላው የአድዋ መናፈሻ ተብሎ ታቅዶ ለብዙ ዓመታት የተቀመጠ ቦታ ነው፡፡ የቦታው መልካ ምድርም ሆነ ያለው ረግረጋማ ባሕርይ ለመናፈሻነት ምቹ የሚያደርገው ሲሆን፣ ላለፉት አስርተ አመታት ተጠብቆ የቆየን ቦታ ለሌላ አገልግሎት ማዋል መናፈሻ ለጠማው ከተማ እና ነዋሪ ላይ ለወደፊቱ የጤና እና የማህበረሰብ ችግሮችን መፍጠር ነው የሚሉም አሉ። እንደዚህ ለዘመናት ተጠብቆ የቆየን፣ ስመ-ጥር መናፈሻ ሆኖ መልማት የሚችል ቦታን ለሌላ አገልግሎት ማዋሉ ተገቢ ነው ብለው አያምኑም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የከተማው አስተዳደር እና ነዋሪው ለከተማው የሚገባውን የአረንጓዴ ሽፍን እና የመናፈሻ ስፍራዎች ተደራሽነት እንዲጨምሩ ከፍተኛ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ይህን የከተማው ሌላ ማስተንፈሻ መሆን የሚገባው እና የሚችልን ታሪካዊ ዳራው ከፍተኛ የሆነን ቦታ ወደ መኖሪያነት መቀየር ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ ።

የምህድስና ባለሙያዎች ደግሞ የአድዋ ፓርክ ለብዙ አመታት አፈር የተደፋበት ቦታ፣ ረግረግ እና የአካባቢው አፈር ጥቁር መረሬ መሆኑ የግንባት ዋጋው ከፍተኛ ስለሚያደርገው ሌሎች አማራጮች እንዲታይ ሲመክሩ፣ የግድ መሆን ካለበት ግን ለነዋሪዎች ደህንነት ዲዛይኑ ላይ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ።

ለፓርክ እና ለሌሎች ለማህበረሰብ የጋራ አገልግሎት የተከለሉ፤ ከተማ አቀፍ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ ቦታዎች ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚውሉ ይልቅ በተገቢው ባለሙያ ተጠንተው ለታለመላቸው አገልግሎት ቢውሉ የበለጠ ዘላቂ የማህበረሰባዊ እና ኤኮኖሚያው ጠቀሜታ እንዳላቸው የሚናገሩ ባለሙያዎች ከተማው ጊዜው ሳይረፍድ ሌሎች አማራጮች እንዲያይ ይመክራሉ፡፡

የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ወጪያቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ሲሆን ግንባታው በዘጠኝ ክ/ከተማዎች የሚከናወን እና በግንባታ ስራውም ከ1740 በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት በማሳተፍ ከ52 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድልን የሚያገኙ ይሆናል ሲል መስተዳደሩ አሳውቆዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በ20/80ና በ40/60 የቤት ልማት መርሀግብር የሚከናወኑ እና የግንባታ መርሀ ግብሩ በቅርቡ ይፋ ከተደረገውና 500 ሺህ ቤቶች ከሚገነቡበት የቤቶች ግንባታ እቅድ ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ መሆኑ በመስተዳደሩ ተነግሮዋል ።

በከተማ አስተዳደሩ በእቅድነት ከተያዙት እነዚህ ቤቶች ውስጥም 120ሺህ ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ ወጪ የሚገነቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ከ 300ሺህ በላይ የሚሆኑት መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ከግል ባለሀብቶች ጋር በጋራ እንደሚገነቡ ተገልፆዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ ቀጣይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና ከግል ባለሀብቶች ጋር በትብብር የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች ግንባታዎቻችው በቀጣይ ቀናት በይፋ የሚጀመሩ ናቸው ተብሎዋል።

በቅርብ ቀናት ግንባታቸው ለሚጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚውል 69 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን እና ለግንባታ ከተዘጋጁ ቦታዎች ውስጥ በመሀል ከተማ ውስጥ ለረጅም አመታት ያለአግልግሎት ተይዘው የነበሩና ከተማ አስተዳደሩ ወደ መሬት ባንክ ገቢ ካደረጋቸው ቦታዎች መካከል እንደሚገኙበት ተገልፆዋል፡፡