ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በከተማዋ ለተለያዩ ጉዳዮች ለሚቀርብለት የመሬት ጥያቄ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ገልጿል።
ቢሮው ለተቋሙ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ይህንኑ ውሳኔውን በማስታወቂያ አሳውቋል።
በማስታወቂያው ላይም ; “ቢሮው የልማት ጥያቄዎችን ላቀረቡ አልሚዎች ሲሰጥ የነበረውን አገልግሎት ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ ከግንቦት 12 ቀን 2013 አ.ም ጀምሮ አዲስ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል የማይቀበል መሆኑን ; እንዲሁም ከአሁን በሁዋላ የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎች የፕሮፖዛል ማመልከቻው ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ለሚመሩና ከዚህ ቀደም ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተገምግሞ ወደ ቢሮው ለተላኩት ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንም” ገልጿል።
ቀደም ብሎ በለጠፈው ሌላ ማስታወቂያ ላይ ደግሞ መሬት የሚሰጠው ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች ብቻ ሲሆን ሌሎች የሚቀርቡ የመሬት ጥያቄዎችን ወደፊት በሊዝ ጨረታ እንደሚያስተናግድ ገልጿል።
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮው የሚቀርቡለትን የመሬት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ለምን እንዳቆመ በግልጽ ያስቀመጠው ምክንያት የለም።
ዋዜማ ራዲዮ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገችው ጥረት : አገልግሎቱ እንዲቋረጥ የተወሰነው በመሬት ማቅረብ ሂደት ላይ በጥቅም ትስስር በመታገዝ ሰፊ የመሬት ቅርምት በመፈጸሙ ነው። ጉዳዩም የፌዴራል መንግስት ገብቶበት እስኪጣራም አገልግሎቱ እንዳይሰጥ ነው የተወሰነው። አገግሎቱ እንዲቋረጥ በተደረገበት ጊዜም እስከ 40 ሺህ የመሬት ጥያቄዎች ቀርበው በመታየት ላይ ነበሩ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምንጫችን ለዋዜማ ራዲዮ እንደገለጹት በመሬት አገልግሎቱ ላይ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ከመሬት ፈላጊዎች በሙስና እየተሰጠ ህገ ወጥ ድርጊት እየተፈጸመ ነው። መሬት አላግባብ እየተሰጠበት ያለውም ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደሩ በተደራጀ ቡድን ነው።
የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ውስጥ የሚሰሩት ሰራተኞች የተመረጡ ቦታዎችን ይዘው በማቆየትም በድርድር ለፈለጓቸው ሰዎች ይሰጣሉ ያሉን ምንጫችን ለዚህም ከሁለት እስከ አምስት ሚልየን ብር አንዳንዴም ከዛ በላይ ጉቦ እንደሚቀበሉ ነግረውናል።
መሬቱን በጉቦ የተቀበለ ግለሰብም መሬቱን የሚጠይቀው ለኢንቨስትመንት እንደሆነ ይግለጽ እንጂ ከሰላሳ እስከ ሀምሳ ሚልየን ብር መሬቱን የመሸጥ ሁኔታም ይታያል ብለውናል ምንጫችን። በዚህ ሂደት ውስጥም ሀሰተኛ ሰነዶች በሰፊው ጥቅም ላይ ይውላሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየትና ምላሽ እንዲሰጡን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚልኬሳ ጃገማ በተደጋጋሚ የደወልን ቢሆንም ስልክ ባለማንሳታቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም። [ዋዜማ ራዲዮ]