ዋዜማ- የአዲስ አበባ አስተዳድር በከተማዋ የሚደረጉ ማናቸውንም የቋሚ ንብረት ባለቤትነት ዝውውር ከሕዳር 29 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ ማገዱን ማስታወቁን ዋዜማ ተመልክታለች።
በመስተዳድሩ የከንቲባ ፅህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ዘርፍ ሐላፊ ቢንያም ምክሩ ለሁሉም የከተማዋ አስተዳድር መዋቅሮች በላኩት ማሳሳቢያ ከሕዳር 29 ቀን 2015 ጀምሮ ማንኛውም የቋሚ ንብረት ዝውውር በጊዚያዊነት እንዲታገድ አሳስቧል።
እገዳው ያሰፈለገው በከተማዋ እየተስፋፋ የመጣውን ሕገወጥነት ለመከላከል መሆኑን ደብዳቤው ያትታል።
በዚህ ሳምንት አጋማሽ የአዲስ አበባ መስተዳድር ሙስናን ለመከላከልና በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል ከመንግስት መዋቅር የተውጣጡ አምስት አባላት ያሉት ግብረ ሀይል ማቋቋሙን ይፋ አድርጎ ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ባንድራ ይሰቀላል በሚሉና ይህን በሚቃወሙ ተማሪዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ጉዳት መድረሱንና ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 97 ያህል ሰዎችን ይዞ ማስሩን አስታውቋል።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመንግስት መገናኛ ብዙሀን በሰጡት ቃለመጠይቅ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የተፈጠረው ግጭት አስተዳድሩ በሙስና ዘመቻ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ለማደናቀፍ በሙስና የተዘፈቁ አካላት እጅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በፀረሙስና ዘመቻው እርምጃ ይወሰድብናል ብለው የሰጉ እንዲሁም በሙስና መቀጠል የሚፈልጉ አካላት ሁከት በማስነሳት የመንግስትን ትኩረት ለማስቀየር እያሴሩ ነው ሲሉ አዳነች ከሰዋል። ከንቲባዋ ሙሰኛ ያሏቸውን አካላት በስም አልጠቀሱም።
በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ላይ በተፈጠረው ሁከት የውጪ ኃይሎችና የምዕራባውያንም እጅ አለበት ብለዋል አዳነች ።
የፌደራሉ መንግስት አዲስ የፀረ ሙስና ዘመቻ መጀመሩንና ሁሉም የክልልና ከተማ መስተዳድሮች እስከ ወረዳ የሚዘልቅ የፀረ ሙስና ግብረ ኃይል እንዲያቋቁሙ ትዕዛዝ ማውረዱ ይታወቃል። [ዋዜማ]