ዋዜማ ራዲዮ- የስልጣን ጊዜው ተጠናቆ ለአንድ አመት ተጨማሪ ጊዜ በስልጣን ላይ የቆየውን የኣአዲስ አበባ መስተዳድር አሁንም ለተጨማሪ ጊዜ በስልጣን እንዲቆይ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከመስተዳድሩ የውስጥ ምንጮች ስምታለች።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ካለፈው የከተማና የአካባቢ ምርጫ በሁዋላ የስራ ዘመኑ ተጠናቆ ፣ በ2010 አ.ም በወቅቱ በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ አልተቻለም በሚል የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ለአንድ አመት እንዲራዘም ተደርጓል። ይህ የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክሮበትም ጭምር ነው።
እንደዚሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አንቀጽ 14 ላይ ማሻሻያ በማድረግ የከተማው ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት ውጭ መሾም እንዲችል ተፈቅዷል።በቀድሞ አሰራር የከተማው ከንቲባም ምክትል ከንቲባም የከተማው ምክር ቤት አባል መሆን ይጠበቅበት ነበር።
የተሻሻለው የከተማው ቻርተር ታከለ ኡማን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። አሁን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት የተሰጠው የአንድ አመት ማራዘሚያ ተጠናቋል።እስካሁንም ከመንግስት በኩል የምክር ቤት ምርጫ ይደረጋል ወይስ አሁንም የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ይራዘምለታል በሚለው ላይ በይፋ የተባለ ነገር የለም። የምክር ቤቱ የስራ ዘመን የማይራዘም ከሆነ ታከለ ኡማ ምክትል ከንቲባ ሆነው መቀጠል የሚያስችላቸው ህጋዊ መሰረት አይኖራቸውም። ምክንያቱም የተሻሻለው ቻርተር ምክትል ከንቲባ ከምክር ቤት ውጭ እንዲሾም ፈቀደ እንጂ የምክር ቤቱን የመሾምና ሹመቱን የማጽደቅ ስልጣንን አልነጠቀም። ስለዚህ ታከለ ኡማ የምክር ቤቱ ስልጣን ካልተራዘመ በስራ ላይ ሊቆዩ አይችሉም።
ዋዜማ ራዲዮ ከምንጯ መስማት እንደቻለችው ; የአዲስ አበባን ምክር ቤት የስራ ዘመን በድጋሜ ለማራዘም በመንግስት በኩል ታስቧል። ለምን ያህል ጊዜና በምን የህግ ይዘት የሚለውን ግን አደናጋሪና ውስብስብ የህግ ጉዳዮችን አስነስቷል።
የህግ ትርጓሜን ክፍተትን በመጠቀም አሁን በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር “ህጋዊነቱ እላከተመም” በሚል የመከራከሪያ መስተዳድሩን በስራ ላይ እንዲቆይ ለማድረግም ምክክሮች መደረጋቸውን ተረድተናል።
የህግ ክፍተትን ተጠቅሞ መስተዳድሩን ህጋዊ አድርጎ ማቆየት አስቸጋሪ መሆኑን ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ባለሙያዎች መኖራቸውና ጉዳዩ ላይ ተከታታይ ምክክሮች ተደረገው እንደነበር ተሰምቷል።
የምክር ቤቱ የስራ ዘመን የማይራዘም ከሆነ ምርጫ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ ስለማይታሰብ የከተማዋ እድል በባለአደራ አስተዳደር መቀጠል ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው የነገሩንም አሉ።
የከተማው ምክር ቤትን የስራ ዘመንን በድጋሜ በህግ ማራዘም ግን ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ምንጮቻችን አፅንዖት ስጥተው ነግረውናል። ይህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ለእረፍት ከተበተነበት ለአስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ሊያስፈልግ ይችላል።