ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ በአራት ክፍለ ከተሞች የሚገኙና ከ2003 ዓ.ም ወዲህ በሕገወጥ መንገድ እንደተገነቡ የሚታመኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለማፍረስ የአቶ ድሪባ ኩማ ካቢኔ በምስጢር ዉሳኔ ማሳለፉ ተሰማ፡፡
ይህ ዉሳኔ የተላለፈው የአዲስ አበባ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት ከመጀመሩ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ነው፡፡
ከከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ጽሕፈት ቤት ወደ አራት ከፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ባሳለፍነው ሳምንት እንደተላከ የተነገረ አንድ ማኅተም አልባ ደብዳቤ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ቀበቷቸውን እንዲያጠብቁ ይመክራል፡፡ ሁሉም የወረዳና የክፍለ ከተማ መዋቅሮች ሕገወጦችን ለመታገል በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው፣ ለዚሁ ተግባር ሲባል የሚቋቋመው ልዩ ግብረኃይል ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለመስጠት እንዳያመነቱ ያሳስባል፡፡
ሕገወጥነትን ማስቆም ለነገ ተብሎ የሚያድር ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያትተው ይህ ደብዳቤ ለአቃቂ ቃሊቲ፣ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ለቦሌ፣ ለኮልፌ ቀራንዮና ለየካ ክፍለ ከተሞች የከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ጽሕፈት ቤቶች የተላከ ነው፡፡
ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ ተደርጎ እንደተላከ የተገለጸ ሌላ ባለ 4 ገጽ ቅጽ ደግሞ ወደፊት የሚፈርሱ ቤቶችን የተመለከቱ መረጃዎች የሚሞሉበት ፎርም እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቅጹ በዋናነት የቤቱን አባወራ ሙሉ ስም፣ የቤተሰብ ቁጥር፣ ቤቱ የተገነባበት ዓመተ ምህረት፣ ቤቱ የተገነባበት ቁሳቁስ፣ በቤቱ ዉስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ብዛት፣ የቤቱ አጥር ርዝመትና ዓይነት የሚጠይቅ መዘርዝር ተካቶበታል፡፡ ይህ ቅጽ የሚደርሳቸው ቤቶች በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ዉስጥ የመፍረስ እጣ የሚገጥማቸው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ቅጹን በየቤቱ እየዞሩ የሚያስሞሉ የወረዳ ደንብ አስከባሪዎች ልዩ የፖሊስ ጥበቃ እንደማይለያቸው ቃል የተገባላቸው ሲኾን የኮማንድ ፖስት የሰንሰለት ዕዝ ከፖሊስ አቅም በላይ የኾነ ማንኛውም ኹኔታ ለመቆጣጠር ዝግጁ መኾኑ ተነግሯቸዋል፡፡
አርብና ቅዳሜ ምሽት በአንዳንድ ወረዳዎች ጉዳዩን አስመልክቶ የስምሪት መርሐግብር በሚሰጥበት ወቅት ደንብ አስከባሪዎች ከሰፋሪዎች ለሚሰነዘርባቸው ያልተጠበቀ ጥቃት ዋስትናችን ምንድነው ሲሉ ከዚህ ቀደም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ አንድ ሥራ አስፈጻሚ ላይ የደረሰን ክፉ አጋጣሚ እንደዋቢ በማንሳት ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ በተሰጠ ምላሽ ደንብ አስከባሪዎች ለጊዜው መረጃ በመሰብሰብ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ተነግሯቸዋል፤ መረጃ ለምን ሰበሰባችሁ ብሎ የሚተናኮል ነዋሪ ይኖራል ተብሎ ስለማይጠበቅ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የወረዳ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤቶች ወደፊት በሚፈርሱ አካባቢዎች ረብሻ ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ወጣቶችን ስምና ጠቅላላ ሁኔታ ቀድመው ሪፖርት እንዲያደርጉ ተነግሯቸዋል፡፡ ይህ የቅድመ ዝግጅት ሰፊ ንቅናቄ ዓላማ ነዋሪዎችን አግባብቶ ሕገወጥ ግንባታቸውን ራሳቸው በመልካም ፍቃዳቸው ቤቶቻቸውን እንዲያፈርሱ ወይም ደግሞ ለአፍራሽ ግብረኃይሉ ቀና ትብብር እንዲያደርጉ ማግባባት ነው፡፡
ይህን የማግባባት ሥራ ለማሳለጥም በሚፈርሱ ሰፈሮች ነዋሪ የነበሩና ምንም ዓይነት መውደቂያ አይኖራቸውም ተብለው የሚገመቱ፣ መስተዳደሩ “የድሀ ድሀ” ብሎ የሚጠራቸው ነዋሪዎች በስምና በቁጥር ከተለዩ በኋላ የቀበሌ ቤት እስኪገኝላቸው ድረስ በአካባቢው ጊዝያዊ መጠለያ እንዲዘጋጅላቸው ይኸው ደብዳቤ ምክረ ሐሳቡን ያስቀምጣል፡፡
ያም ኾኖ አሁን በችኮላ ወደ ማፍረስ ሥራ የመግባት ፍላጎት በመስተዳደሩ ዘንድ እምብዛምም እንደሌለና ከዚያ ይልቅ በመጪዎቹ ሳምንታት ቅጹ በሚያዘው መሠረት የነዋሪዎችን መረጃ የመሰብሰብ ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ የመንግሥት ጽኑ ፍላጎት እንደሆነ በወረዳ ዉስጥ በምክትል የጽሕፈት ቤት ኃላፊነት የሚሠሩ ግለሰብ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ “አሁን በመጪዎቹ ዓመታት በመልሶ ማልማት የሚፈርሱ ቦታዎች ላይኖሩ ይችላሉ፤ ከዚያ ይልቅ ማስፋፊያ ቦታዎች ላይ ያለን ሕገ ወጥ ግንባታ መልክ ማስያዝ ነው የተፈለገው የሚመስለኝ” ሲሉ ጥርጣሬ ያልተለየው አስተያየታቸውን ያክላሉ፡፡
በበርካታ የአዲስ አበባ ወረዳዎች ሰሞኑን በተነገረ ማስታወቂያ ቤታቸውን ከ97 ወዲህ የገነቡ ማናቸውም ነዋሪዎች አለን የሚሉትን ማስረጃ በመያዝ በየወረዳቸው ቀርበው እንዲያሳዉቁ ያዛል፡፡ ይህ ማስታወቂያ በወረዳና ክፍለ ከተማ መዋቅሮች ዉስጥ በሚሰሩ የመሬትና ተያያዥ ጉዳይ ባለሞያዎች ዘንድ ግርታና ጥርጣሬን መፍጠሩ አልቀረም፡፡
በአንድ በኩል ከማዕከል በተላከ ደብዳቤ እንዲፈርሱ የሚፈለጉ ቤቶች ከ2003 ዓ. ም ወዲህ የተገነቡ ቤቶች ብቻ መኾናቸውን ሲጠቁም በሌላ በኩል ወረዳዎች ከ97 ወዲህ የተገነባን ማንኛውንም ግንባታ ለመመዝገብ መፈለጋቸው ምናልባት ከ1997 እስከ 2003 የተገነቡና የአየር ካርታ ላይ የሚታዩ ቤቶችን ወደ ሕጋዊነት የማሸጋገር ጭላንጭል ተስፋ ይኖር ይሆናል የሚል እሳቤን በአንዳንድ የመሬት ልማት ባለሞያዎች ዘንድ ሳይፈጥር አልቀረም፡፡
መንግሥት ባለፉት ዓመታት ከ1988 እስከ 1997 የተገነቡ ሕገወጥ ቤቶች በአየር ካርታ ላይ እስከታዩ ድረስ ወደ ሕጋዊነት በማሸጋገር ላይ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ከ97 እስከ 2003 የተሠሩ ተመሳሳይ ቤቶችንም ወደ ሕጋዊነት ለማሸጋገር መመርያ ከወጣ በኋላ ባልታወቀ ምክንያት መመርያው በመመርያ መሻሩ አይዘነጋም፡፡
የኢህአዴግ መንግሥት ምናልባት በከተማ አካባቢ በከፍተኛ ፍጥነት ያሽቆለቀለውን የሕዝብ ቅቡልነቱን ከፍ ለማድረግ እስከ 2003 ድረስ የተገነቡ ቤቶች ወደ ሊዝ ሥርዓት በማስገባት ሕጋዊ እንዲኾኑ የሚያስችል ያልተጠበቀ ዉሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ከሰሞኑ እየበረከተ መጥቷል፡፡
ሕገ ወጥ ግንባታዎችን በማፍረስ ረገድ መስተዳደሩ ቁርጠኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ቢሰማም ፖለቲካዊ ኪሳራ ያመጣብኛል ብሎ በሚያምንበት ወቅት ግን ይህን ድርጊቱን ጋብ ለማድረግ ሲሞክር በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡
ባለፈው ዓመት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ስማቸው ኮንቱማ፣ ቀርሳና ማንጎ በተባሉ አካባቢዎች በነበረ ደም አፋሳሽ የማፍረስ ሂደት 11ሺህ ቤቶች በግብረኃይል እንዲፈርሱ ከተደረገ በኋላ ድርጊቱ ብዙም ሳይገፋበት ቆይቷል፡፡ ይኸውም በአገሪቱ በተለይም ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ዉስጥ በተፈጠረ ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ሁኔታዎች መልካቸውን እንዳይለዉጡ በሚል የማፍረስ መርሐግብር እንዲታጠፍ በመደረጉ ነበር፡፡ እንደማሳያ የሚጠቀሰው በዚያው ሰሞን ለመፍረስ በእቅድ ተይዘው የነበሩ በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ የሚገኙ ተጨማሪ ቦታዎችም እንዳይፈርሱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ልዩ መመርያ መውረዱ ነው፡፡
ከንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ሐና ማርያም ሰፈሮች ቀደም ብሎ በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ ማዶ ወረገኑ በሚባል ሰፈር ከ2ሺህ የሚልቁ ቤቶች እንዲፈርሱ መደረጉም አይዘነጋም፡፡ ይህም ሂደት ከፍተኛ የሕዝብ ጩኸትና ተቃውሞ ከማስከተሉም በላይ በርካቶችን ለእስር ዳርጎ ነበር፡፡
ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ ታዛቢዎች ሕገ ወጥ ግንባታ አሁንም በበርካታ የከተማዋ የማስፋፊያ አካባቢዎች በጠራራ ፀሐይ እየተካሄደ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ በቦሌና በንፋስ ስልክ በርካታ ወረዳዎች አምና በፈረሱ የማንጎና ኮንቱማ ሰፈሮች ላይ ጭምር አዳዲስ ሰፋሪዎች የጨረቃ ቤት እየገነቡባቸው እንደሚገኝ ከስፍራው በየጊዜው የሚደርሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
መስተዳደሩ የፈረሱ ቦታዎችን በፍጥነት ወደ ልማት በማስተላለፉ ሂደት ዉስንነት ስለሚታይበትና ሕገወጥ የሚባሉ ቤቶች ከመገንባታቸው በፊት ለመከላከል አለመቻሉ ወይም አለመፍቀዱ ከፈረሱ ዓመት እንኳ ባልሞላቸው ቦታዎች ድጋሚ ሕገወጥ ግንባታ እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ይህ እንዲከሰት ከሚያደርጉ ተጨማሪ ምክንያቶች አንዱ ከገጠር ወደ ከተማ ድኅነትን ሽሽት የሚደረግ የማያባራ ትኩስ ስደት እንደሆነ የሚናገሩ ብዙ ናቸው፡፡
በመዲናዋ የቤት ኪራይ ዋጋ ከምንጊዜም በላይ በአስደንጋጭ ኹኔታ እየናረ መምጣቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የመሬት ወረራ ላይ ለመሳተፍ እንዲገደዱ እንዳደረጋቸው የሚያምኑም ጥቂት አይደሉም፡፡
በአሁን ጊዜ በመዲናዋ ቤት መሥሪያ መሬት የሚገኝበት ብቸኛው አግባብ የሊዝ ጨረታ መኾኑ ሌላው ለወረራው አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከተማዋ የሊዝ ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ላለው ነዋሪ ቀርቶ መካከለኛ ገቢ ላላቸውም የሚቀመስ አለመሆኑ ደግሞ በከተማዋ አዲስ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል፡፡
አሁን የመፍረስ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ የተነገረላቸው በኮልፌ ቀራንዮ በርካታ ወረዳዎች፣ በለቡና ጃሞ አካባቢ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድና ሁለት፣ በየካ ወረዳ 13፣ እና በቦሌና አቃቂ ቃሊቲ በርካታ የማስፋፊያ ሰፈሮች የሚገኙ ቤቶች ናቸው፡፡
በዚህ አዲስ የማፍረስ እቅድ መስተዳደሩ ከገፋበት በነዚህ አራት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ዉስጥ ለዓመታት የኖሩ ቁጥራቸው ቢያንስ 30ሺ የሚጠጉ ቤቶች የመፍረስ እጣ ሊገጥማቸው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡ የማፍረስ ዕቅዱ ከ97 እስከ 2003 የተገነቡ ቤቶችን የሚጨምር ከኾነ ደግሞ ይህ አሐዝ በሦስት እጥፍ ሊያድግ ይችላል፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳደር ምክር ቤት የ4ኛ ዓመት፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባሳለፍነው አርብ ከሰዓት በኋላ ሲያጠናቅቅ በመሐል ከተማ የሚገኙ ዜጎችን በመልሶ ማልማት ስም በከፍተኛ ቁጥርና ስፋት የማፈናቀሉ ተግባር ለጊዜው ጋብ እንዲል የሚያዝ ያልተጠበቀ ዉሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ይህ ዉሳኔ ለአንዳንድ ፖለቲካዊ ተንታኞች ኢህአዴግ እድሜውን ለማራዘም በሚል የዋጠው መራራ ኪኒን ተደርጎ ተወስዷል፡፡