የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር የሰጡትን መግለጫ ሰማሁት፣ አየሁት። ፖለቲካውን በፖሊስ ቋንቋ፣ የፖሊስን ጥፋት በፖለቲካ ቋንቋ ለማጽደቅ ተሞክሯል፤ እንደድሮው።
በኮሚሽነሩ መግለጫ ላይ ዝርዝር አስተያየት መስጠት ይቻል ነበር። ግን ጥቅም ያለው አልመሰለኝም። መማማር ራሱ አቅምና ፍላጎት ይጥይቃል። እዚያ አልደረስንም።
በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች አይጠየቁ ያለ ሰው የለም። አልነበረምም። ለምሳሌ፣ በቪኦኤ ላይ የቀረበው (ወደፓስተር አካባቢ መሰለኝ) የሆቴል ባለቤቶችን ያስፈራሩት፣ ንብረት ያጠፉት ድኩማን በሕግ አግባብ ተይዘው መመርመራቸው፣ ለክስ መቅረባቸው ቢነገረን ከመደገፍ በቀር አንቃወምም። ይህ ስለመሆኑ አልተነገረንም። ከጎንደር፣ ከአርባምንጭ ይመጣሉ የተባሉ የተደራጁ ሌቦች ከአዲሳባ ወጣት ጋራ ምን አገናኛቸው?
ክርክሩ ዜጎች በሕግ አግባብ ይያዙ፣ ይጠየቁ ነው። ያለፍርድ ቤት ፈቃድ የተያዙና ለቀናት የታሰሩ ዜጎችን ክብርና መልካም ስም ማጉደፍ፣ ፍርድ ቤት ያልፈረደባቸውን ሰዎች እንደ ጥፋተኛ ቆጥሮ “ጦላይ ወስጄ እቀጣለሁ፥ አስተምራለሁ” እያሉ ማሰቃየትን ሊያፍሩበት በተገባ ነበር። ጭራሽ በድርጊቱ ሲኩራሩበት ለሚመለከት “ነገሮች በተለወጡ መጠን እንደነበሩ ይቆያሉ” የሚለውን አባባል ያስታውሳል። በዚህ ጉዳይ፣ ዜጎችን ከመንገድና ከሚዝናኑበት ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በማሰርና በማሰቃየት ፖሊስ ሕግ ጥሷል። የሕግ ባለሞያዎች ፖሊስን መክሰስ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ።
ሺሻና ጫት ቤቶችን መቆጣጠር የሚለውን ጨዋታ እዚያው ብቻችሁን ስትሆኑ እየቃማችሁ ወይም እየጠጣችሁ ቀጥሉት። ሌላው ቢቀር ሰው ይታዘበናል በሉ። በሽግግር ምጥ ውስጥ ያለችን ከተማ የሚያስተዳደር መሪ፣ ደርሶ የሞራልና የስነምግባር ዘበኝነት አንገብጋቢ ስራዬ ነው ሲል ከማስገመቱም በበለጠ አገር ይጎዳል። ውስን ጉልበትና ትኩረታችሁን በሌሎች አንገብጋቢ መስኮች ላይ አውሉት።
በቀረውስ፣ የአዲስ አበባን ወጣት በጅምላ ወሮበላ፣ ዘራፊ፣ ለአገር የማይጠቅም፣ ሱሰኛ ወዘተ እያስመሰሉ ማቅረቡ አሁንም አይጠቅምም እንላለን። ጥላሸት የመቀባት፣ የማስደንገጥና የማሳቀቅ ዘመቻ ይመስላል። ዘመቻው “ቤት አልባ፣ ስራ አልባ፣ አገር አልባ፣ ሰፋሪ” ከሚለው ትርክት የቀጠለ ሊሆን እንደሚችል እንገነዘባለን። ስለዚህም፣ የመንግሥት አካላት ከዚህ መሰሉ ማጥላላት በእጅጉ እንዲጠነቀቁ እንማጸናለን። ሲሆን መስተዳድሩ ለከተማው ነዋሪዎች የአካል ብቻ ሳይሆን የፖለቲካና የስነልቦና ከለላም ሊሆንላቸው በተገባ ነበር።
የአዲስ አበባንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም የኅብረተሰብ ክፍል በጅምላ መወንጀል፣ ስሕተት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው። ሬሳ ከመቁጠር፣ የፈረሰ ሕንጻ ፎቶ ከማነጻጸር፣ የጠፋ ከተማ ከመናፈቅ በቀር የሚያተርፍልን ነገር አይኖርም። ሁላችንም ልብ እንግዛ። በተለይ ደግሞ፣ በመንግሥት ሐላፊነት ላይ ሆናችሁ የምትናገሩ ሰዎች እባካችሁ ከብዙ ንግግር ተቆጠቡ፤ ንግግራችሁ ውጤት እንደሚያስከትል ተገንዘቡ።
እንዲህም ሆኖ፣ ለውጡ ገዢ የመቀየር ሳይሆን የመሻሻል ለውጥ ሊሆን ይችላል ብዬ ተስፋ ማድረጌን አልተውኩም።