ዋዜማ ራዲዮ- “ግማሽ ቢሊዮን ብር ባዲሳባ ምን ይገዛል?” ብሎ የጠየቀ ቡራቡሬ ምላሽ ያገኛል፡፡
ግማሽ ቢሊየን ብር ቃሊቲ ብረታብረት ፋብሪካን ባለበት ሁኔታ ይገዛል፡፡ ቦሌ አካባቢ ጅምር ባለ 10 ፎቅ ሕንጻን ይገዛል፡፡ ወይም ደግሞ አሜሪካን ግቢ 1380 ካሬ እዳሪ መሬትን ይገዛል፡፡
ላለፉት ተከታታይ ዓመታት የሊዝ ግብይት ዉጤት ጯኺ ዜና ሳይሆን የቀረበት ጊዜ እምብዛምም ነው፡፡ ሰበር ዜና የሚያደርገው ታዲያ ለኪስ ቦታዎች የሚቀርበው ዋጋ መጠን የጤና ስለማይመስል ነው፡፡ ኒውዮርክ ማንሀተን፣ ፈረንሳይ ፓሪስ፣ ቻይና ጓንዙ የአዲሳባን ያህል አፈራቸው አልከበረም፡፡ ስለምን የአዲሳባ አፈር አለቅጥ ከበረ?
አሜሪካን ግቢም እንደ ማንሀተን
ከአንድ ወር በፊት የተካሄደው የ24ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ዉጤት በመሬት ዙርያ አያሌ ጥያቄዎችን ለኩሷል፡፡ ዉጤቱ ለዲስአበቤዎች የኛ የሚሏት ከተማ የነርሱ እንዳልሆነች በለሆሳስ ነግሯቸዋል፡፡ የማኅረሰብ አጥኚዎችን ወደፊት “በመሐል አዲሳባ ንብረት አለኝ የሚል አማካይ ድሀ” ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል ወደሚል ድምዳሜ አድርሷቸዋል፡፡ከጥቂት ዓመታት በፊት መሐል አዲሳባ ንብረት ይዞ አማካይ ገቢ ያለው ዜጋ ኾኖ መኖር ይቻል ነበር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን እንጃ፡፡
ይህን ትንቢት ማመን የተሳነው 24ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ አጽንኦት ሰጥቶ ይመልከት፡፡ በእርግጥም 24ኛው ዙር በመሬት ግብይት ታሪክ ማርሽ ቀያሪው ነበር፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ፣ ወረዳ አንድ፣ ልዩ ስሙ አሜሪካን ግቢ፣ ከአንዋር መስጊድ ማዶ የቀረቡ ስድስት ቦታዎች ከ2005ቱ የሊዝ አዋጅ ወዲህ ከቀረቡ ዋጋዎች ሁሉ የላቀውን ዋጋ አስመዝግበዋል፡፡ የስድስቱን ቦታዎች የስፋት ጨመቅ ቁልቁል ደምረን በቀረበላቸው ድምር ዋጋ ብናበዛው አስፈሪ “እኩል ይሆናልን” እናገኛለን፡፡
የስድስቱ ቦታዎች የካሬ ድምር 5231 ስኩዌር ካሬ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ቦታ በድምሩ የተሰጠው ዋጋ ግን ለየትየሌሌ የቀረበ ነው፡፡ ለጥሪም የሚያስፈራ፣ ለአፍም የሚከብድ፣ ለስሌት መኪናም ፈተና፡፡ 5ሺ ከምናምን ካሬው የተገዛበት ገንዘብ ድምር 1, 322,784,681.00 (አንድ ቢሊየን ሦስት መቶ ሀያ ሁለት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሰማንያ አራት ሺ ስድስት መቶ ሰማንያ አንድ ብር) ይደርሳል፡፡ ይህ ባለ 10 ዲጂት ገንዘብ በ30 ዓመታት ወደ መስተዳደሩ ካዝና የሚገባ ሲሆን የወለድ ምጣኔ ሲታከልበት አሐዙ ከሦስት እጥፍ በላይ ይፋፋል፡፡
ይፋፋል ስንል ምን ማለት ነው? በየዓመቱ ድርብ ድርብርብ ወለድ እላዩ ላይ ይከመርበታል ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከሌሎች ክልሎች በተለየ በሕግ ያልተደገፈ የድርብ ወለድ (Compound Interest) አሠራርን ትከተላለች፡፡ ይህም በመኾኑ አምስት ሺህ ካሬ የተሸመተበት ዋጋ ከነድርብር ወለዱ ወደ 3 ቢሊዮን ይመነደጋል፡፡ ይህ ለ6 የአሜሪካ ግቢ የሊዝ ቦታዎች በተለያዩ ግለሰቦች የተሰጠ ዋጋ በቀላል ስሌት ወደ አስፈሪ አሐዝነት ሲቀየር ማየት ወደ አእምሮ በርከት ያሉ ጥያቄዎች እንዲራመዱ ምክንያት ይሆናል፡፡ አሀዙ በመሬት ጉዳይ አሁን መሬት ላይ ያለውን እውነታ አጥርተን እንድናይ የሚያስችል ሳይሆን አይቀርም፡፡
ለመሆኑ ይህ ለ5ሺ ካሬ የተከፈለ ጥሪት በዚህ ብጣሽ ካሬ መሬት ላይ ባይውልና ወደ ሌላ ልማት ይሸጋገር ቢባል ምን ሊሠራበት ይችላል ብሎ መጠየቅ ማስተዋል ነው፡፡ የሐዋሳ የኢንዱስትሪ መንደርን አንድ አምስተኛ ወጪ ይሸፍናል፤ ወይም ደግሞ በመጠኑ ከሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በአምስት እጅ የሚያንስ ሌላ ኢንዱስትሪ መንደር ባንዱ ከተማ ይገነባል፡፡ ወይም ደግሞ ሰሜን መዘጋጃና መገናኛ ደርሶ አልገጥም ያለውን ቀለበት መንገድ በከፊል ያስጨርሳል፡፡ አልያም ሁለት ባለ 30 ፎቅ ሕንጻዎችን አጽም ያቆማል፡፡ ለዋና መሥሪያ ቤትነት በቁፋሮ ላይ ያሉ እንደዘመን፣ እንደ ንብ ወይም እንደ ሕብረት ያሉ ሁለት ባንኮችን ግንባታ በከፊል ያስጨርሳል፡፡ የቻይና ኮንስትራክሽን በአዲስ አበባ እየገነባው ያለውን አደይ አበባ ስታዲየም ግማሽ ወጪን ይሸፍናል፡፡ ብሩ ለአዲስ ኩባንያ መቋቋሚያ ይዋል ብንል ደግሞ አንድ አዲስ ባንክና አንድ አዲስ የኢንሹራንስ ኩባንያን ማቋቋም ያስችል ነበር፡፡ ታዲያ እንዴት ይህን ተአምር መስራት የሚችል ገንዘብ በቁራሽ መሬት ላይ ሊዉል ቻለ?
ይህ የሆነው አንድም ተጫራቾቹን አሰባስቦ በተመሳሳይ የቢዝነስ ታንኳ የሚያሳፍር ካፒቴን ባለመኖሩ ነው፡፡ አንድም በተሳሳተ የመሬት ፖሊስ ምክንያት ዜጎች አእምሮ ላይ የተፈጠረ እብደትና ሽብር በመኖሩ ነው፡፡ አንድም ከባህላዊ ንግድ የወጣ፣ ከራሱ አርቆ ማሰብ የሚችል ባለራዕይ፣ ፈጣሪ፣ ምጡቅ ባለሐብት ባለመፈጠሩ ነው፡፡ አንድም…
የሊዝ ዋጋ በመርካቶ ለምን ያብዳል?
የመርካቶ ነገር የጠቅላላው የሊዝ ዋጋ ንረት መገለጫ ሊደረግ ይገባልም አይገባምም ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ “You know…መርካቶ is መርካቶ፣ Merkato is an exception that proves the rule” ይላል ዋዜማ ያናገረችው በጣና ገበያ አቢሲኒያ ባንክ ቅርንጫፍ የሚሠራ ወጣት የምጣኔ ሐብት ባለሞያ፡፡ የርሱ የሙግት ነጥብ መሠረት የነጋዴዎቻችን ለእውቀት ፀሐይ አለመጋለጥ ነው፡፡ ትርክቱ በግርድፉ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
የጨረታው ተወዳዳሪዎች ብዙዎቹ እድሜ ዘመናቸውን በመርካቶ የነገዱ ናቸው፡፡ የአንድ ካሬን ዋጋ ምንነት በመርካቶ ሲሆን አብጠርጥረው ያውቀዋታል? ለምሳሌ ሚስማር ተራ ለአዲስ ግንባታ ከዓመታት በፊት ሲፈርስ በጊዚያዊነት የተሸነሸኑ የኮንቴይነር ሱቆች እስከ 60ሺህ ብር ተከራይተዋል፡፡ የነዚህ ሽንሽን ሱቆች ስፋት 10 ካሬ እንኳ አይሞላም እኮ፡፡ ለመንጠራራት ደጅ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ራጉኤል አካባቢም ብትሄድም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለሞባይል ቤት ተሸንሽነው የተከራዩ 30 ካሬ ሱቆች በየ3 ወሩ 400ሺህ ብር ድረስ ያስገባሉ፡፡ ቁልፋቸው 150ሺህ ድረስ ይሸጣል፡፡ መርካቶ ዉስጥ በአንድ እግር ቆሞ ለመቸርቸር ቦታ ማግኘት አያት ወይም ላፍቶ አንድ ሺህ ካሬ መሬት ከማግኘት የተሻለ ነው፡፡
በመርካቶና አካቢባዋ የሊዝ ዋጋ አለቅጥ መናር አንዱ ሚስጥሩም ይኸው ነው፡፡ ነጋዴዎች በርከት ብለው ይደራጃሉ፡፡ አክሲዮን መስርተው ከመሐላቸው ኮሚቴ ይመርጣሉ፡፡ ለምሳሌ በ24ኛው ዙር በዉድ ካሸነፉት ዉስጥ ብዙዎቹ ለዚሁ ዉድድር ሲሉ በፍጥነት የተደራጁ አዳዲስ አክሲዮኖች ናቸው፡፡ አንድ አክሲዮን ዉስጥ እስከ ሦስት መቶ ነጋዴዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ወጪዉን ስለሚጋሩት አይከብዳቸውም፡፡ ሊዝ በ30 ዓመታት የሚከፈል የወደፊት እዳ ነው፡፡ መርካቶዎች ደግሞ እንደምታውቀው እዳ አይፈሩም፡፡ የኖሩበት ነው፡፡ ሠርተን እንከፍላለን ነው የሚሉት፡፡ መሬቱንም እንደዚያ ነው የሚያስቡት፡፡
መግለጫ ሀ፣ በ24ኛ ዙር በአሜሪካን ግቢ የቀረቡ ቦታዎችና የተሰጣቸው ዋጋ በካሬ
መርካቶ ከድህነት ወለል ወደ ብልጽግና ማማ ያበቃቻቸው ባህላዊ ነጋዴዎች ከመርካቶ ሳጥን ዉጭ ማሳብና ማስላት ብዙም አይሆንላቸውም፡፡ “They cannot think business out of the Merkato box, Finished!!” ለነርሱ የብልጽግና መንገድ ከቻይና 20ፊት ኮንቴይነር አምጥቶ መርካቶ መቸርቸር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ዉጭ ያለ ቢዝነስ ሁሉ አስፈሪ ቁማር ነው፡፡ ለምሳሌ ከገቢ ንግድና ችርቻሮ ወደ አምራች ዘርፍ (ማኑፋክቸሪንግ) ግቡ ቢባሉ መንግሥት ንብረታቸውን በአዋጅ የዘረፋቸው ነው የሚመስላቸው፡፡ 80 ሚሊዮን ብር አካውንቱ ዉስጥ ይዞ አሁንም 50 ሉክ ደብተር የሚቸረችር ነጋዴ አውቃለሁ፡፡ እኛ ባንክ አክሲዮን ቢገዛ ምንም ሳይሰራ በዓመት 31 በመቶ ድርሻ ያገኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለዚህ ሰውዬ 5 ሚሊዮን አምጣና ልማት ባንክ 25 ሚሊዮን ለኢንደስትሪ ያበድርሀል ብትለው ተረት ተረት ነው የሚመስለው፡፡ መርካቶዎች የመክበራቸው ምንጭ መርካቶና መርካቶ በመሆኗ ለነርሱ የብልጽግና አልፋና ኦሜጋም መርካቶ ብቻ ናት፡፡ ነገርኩህ እኮ! የስሌት ማሽን አስገቡ ሲባሉ ራሳቸውን የሚስቱት ለምን ይመስልሀል? ከለመዱት ንግድና አሰራር ዝንፍ ማለት ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ለመርካቶ አፈር ገንዘባቸውን ቢበትኑ ምኑ ይገርማል? ሲል ሀሳቡን ያሳርጋል፡፡
የምጣኔ ባለሞያውን ትርክት የሚያስረግጡ ክስተቶች አልጠፉም፡፡
ለምሳሌ በ11ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ዝዋይ ኢነተርናሸሽናል ቦንብ ተራ አካባቢ ለካሬ 305,000ሺህ በመስጠት አሸነፈ፡፡ ዉጤቱ አገር ጉድ አሰኘ፡፡ የሚገርመው ከፊሎቹ ባለአክሲዮኖች ይህ ዋጋ መሰጠቱን የሰሙት ከጋዜጦች መኾኑ ነው፡፡ ዋጋውን የወሰኑት ጥቂት ባለአክሲዮች ከማኔጅመንቱ ጋር በመሆን ነበር፡፡ ዉሳኔያቸው ግብታዊና በጥድፊያ የተሞላ እንደነበር የሚያሳየው በባለአክሲዮኖቹ መሐል ዉጤቱን ተከትሎ የተፈጠረው ዉዝግብ ነው፡፡ የዉዝግቡ መነሻ ግን ለምን እንዲህ አይነት ዉድ ዋጋ ለዚህች ቁራሽ መሬት ቀረበ ከሚለው ይልቅ፣ ወይም ድግሞ የአዋጪነት ጥያቄን ከማንሳት ይልቅ “ለምን መንግሥት ዐይን ዉስጥ ታስገቡናላችሁ?” ወደሚለው የሚያመዝን ነበር፡፡
ለ449 ካሬ 137 ሚሊዮን ብር ለመከስከስ ፈቅዶ የነበረው ዝዋይ ኢንተርናሽናልም ጉዳዩ የሕዝብ እንደራሴዎች መነጋገሪያ እስከመሆን መድረሱ ምቾት አልሰጠውም ነበር፡፡ በወቅቱ ዝዋይ አካውንቱ ዉስጥ የነበረው የብር መጠንም ከ5 ሚሊዮን የበለጠም እንዳልነበረ ስናውቅ ይበልጥ እንገረማለን፡፡
“ብሩን ማዋጣት እንኳ አያቅታቸውም ነበር፡፡ አልሳምን የመሰሉ ቢሊየነሮች ያሉበት አክሲዮን እኮ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ ያሳሰባቸው ስማቸው ሕዝብና መንግሥት ጆሮ መግባቱ ነበር፣ ግብር እንጠየቃለን፣ ኦዲተር ይላክብናል፣ የሚል ጭንቀት ተፈጥሮባቸው እንደነበር ትዝ ይላኛል፡፡” ይላል ይኸው የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኛ፡፡
ሊዝ የሕገወጥ ገንዘብ ማጠቢያ ማሽን?
በአንድ ሳምንት አንድ ድንገተኛ ሚሊየነር በሚፈጠርባት በአሁኗ ኢትዮጵያ የሕዝብ አገልጋዩና ነጋዴው፣ ሹመኛውና ልጆቹ፣ ፖለቲከኛውና ሸሪኮቹ በሽርክና የሚነግዱበት ሕቡእ ዓለም ተፈጥሯል፡፡ ነግቶ ሲመሽ ከምንምነት ወደ ሚሊየነርነት ሽግግር የሚያደርጉ ሰዎች ገንዘባቸውን ከባንክ ቤት ይልቅ በጆንያ ይዞ መዞር የሚቀናቸው ናቸው፡፡ ጆንያ ይዞ መዞር ብዙም ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡ አዲስ ቪላ መግዛትም የሰው ዐይን ዉስጥ የሚከት ነው፡፡ አቋራጩ መንገድ በተጋነነ ዋጋም ቢሆን ራቅ ባለ ዘመድ ስም ሌጣ መሬት በሊዝ ማሸነፍ ነው፡፡
ሊዝ በባህሪው አየር ላይ የንብረት ባቤት የሚያደርግ ነው፡፡ ለግንባታና ለእዳ መክፈያ የእፎይታ ጊዜን የሚሰጥ የ99 ዓመት የመሬት ኪራይ ነው፡፡ የግዢዉን 20 በመቶ ወይም 10 በመቶ ክፍያ በመፈጸም ብቻ ንብረትን በስም ይዞ መቆየት ያስችላል፡፡ ወደ ግንባታ ለመግባት በአማካይ ከ9 እስከ 12 ወራት ይፈጃል፡፡ ስለዚህ ቋሚ ንብረትና ተንቀሳቃሽ ገንዘብን ይዞ ለመቆየት ሁነኛ አማራጭ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ በፀረ ሙስና ቢደረስበት እንኳን ሊወሰድ የሚችለው የሊዝ ቅድመ ክፍያው ነው፡፡
አንዳንድ የሊዝ ጨረታ ዉጤቶች መሠረታዊ አመክንዮ የሚተነተናቸው ያልሆኑትም ለዚሁ ይመስላል፡፡ በፍጹም ትክክል የማይመስሉ ዋጋዎች በየዙሩ ይሰማሉ፡፡ ማዘጋጃ ቤት ዉጤት ለመስማት የተቀመጠ ተጫራች ሁሉ ያልጎመጉማል፡፡ ለምሳሌ ከፊል ግንባታ የተካሄደበት ባለ 500 ካሬ መሬት በ3 ሚሊዮን ብር እንደልብ በሚሸጥበት ሰፈር ተመሳሳይ ደረጃ ያለው ባዶ ቦታ በ7ሚሊዮን ብር ድምር የሊዝ ዋጋ ማሸነፍ እንዴት አድርጎ ስሜት ይሰጣል? ነገሩ የብር ማጠቢያ ማሽን እስካልሆነ ድረስ ማለቴ ነው፡፡
በአንድ ክፍለ ከተማ፣ በተመሳሳይ ወረዳ፣ በተመሳሳይ የመሬት ደረጃ፣ ተመሳሳይ መሠረተ ልማት ያለው ቦታ የተራራቀ ዋጋ ለምን ይቀርብበታል? ብለን ብንጠይቅ መልስ አናገኝም፡፡ ተመሳሳይ ስፋት ያላቸው፣ አንዳንድ ጊዜም ኩታ ገጠም የኾኑ መንትዬ ቦታዎች ለሊዝ ገበያ ሲወጡ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ዋጋ ሲቀርብባቸው ነገሩ የጤና ነው ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡
ከሆኑ ዙሮች በፊት በሲኤምሲ ኩታ ገጠም የኾኑ ቦታዎች ላይ ለአንዱ በካሬ 12ሺህ ብር ሲቀርብ ለሌላኛው 28ሺህ ብር ቀረበ፡፡ ሁለቱም ወሰዱት ለምን? በዉድ የተገዛው መሬት ዉስጥ ጣሊያን ወርቅ እንደቀበረበት መረጃ እስከሌለ ድረስ ግዢው ትክክል ስለመሆኑ የሚያስረዳ ተአምር ማግኘት አይቻልም፡፡
“የአዲሳባ መሬት ሊያልቅ ነው!”
54ሺ ሄክታር የምትሰፋዋ አዲስ አበባ መለጠጥ የምትችለውን ያህል ሄዳ ጨርሳለች፡፡ ኾኖም ሰማይዋ ክፍት ነው፡፡ ኾኖም 80 ከመቶ የሚሆነው መሐል ሰፈሯ ፈርሶ የሚገነባ ነው፡፡ የከተማ ቦታዎች ወደ ሊዝ ስሪት እንዲካተቱ በአዋጅ ከተደነገገበት ጊዜ ጀምሮ ለሊዝ ጨረታ የቀረቡ ቦታዎች ከስፋቷ ከመቶ አንድ እጅ አይሆኑም፡፡ የስከዛሬው ቢደመር ከአንድ ሚሊዮን ስኩዌር ሜትር ካሬ በላይ ለጨረታ አልቀረበም፡፡ ኾኖም በየጊዜው ዜጎች ለቁራሽ መሬት እየሰጡ ያሉት ቁልል ዋጋ በሌሎች ላይ ፍርሃትን ፈጥሯል፡፡ መሬቱ ሁሉ ተሸጦ እያለቀ ነው የሚል ስጋት ነግሷል፡፡ ነገሩ የስቴዲየም ሰልፍን ይመስላል፡፡ ከረዥም ሰልፍ ኋላ የተሰለፈ ኳስ ወዳጅ ስቴዲየሙ የሞላ ይመስለዋል፡፡ ትኬት በእጥፍ ዋጋ ክፍሎ ለመግባት ይደፍራል፣ ዉስጥ ሲገባ ግን ኦና ስቴዲየም ይጠብቀዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ተጫራቾች በዚህ መንፈስ እንደሚጫረቱ መገመት የሚከብድ አይደለም፡፡ መሬቱ ምን ያመጣል? ስንት ያወጣል? ምን ይሰራበታል፣ ለየትኛው ልማት በየትኛው ቦታ፣ ለምን ያህል ዘመን? ሊዉል ይችላል? ለመሬት በሚከፈለው ጥሪት ሌሎች የቢዝነስ አማራጮች ላይ ቢውል ምን ይፈጠራል? የሚል ስሌት ዉስጥ የሚገባው ነዋሪ ብዙ አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አማካኝነት የተሠራ አንድ ቆየት ያለ ጥናት እንደሚያስረዳው ተጫራቾች ለአዲስ አበባ መሬት የሚሰጠውን ዋጋ የሚተምኑት በአመዛኙ በሌሎች የዋጋ አሰጣጥ ላይ ተደግፈው ነው፡፡ ይህም ማለት ለአንድ ቦታ የሚሰጡት ዋጋ የሚወሰነው ሌሎች ተጫራቾች ቀደም ባለው ዙር ለተመሳሳይ መሬት በሰጡት ዋጋ ላይ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተቆለለ የጠጠር ክምር ላይ እያንዳንዱ ተጫራች ሌላ ጠጠር እየወረወረ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ የሊዝ ዋጋ እየናረ እንጂ እየሰከነ ያልሄደው አንድም በዚሁ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
ከ7 ዓመታት በፊት ከፍተኛው የሊዝ ዋጋ 2ሺ ብር ነበር፡፡በአራት ዓመታት ዉስጥ 26ሺ ደረሰ፡፡ ከዓመት በኋላ 32ሺህ ብር፣ ከዚያም 65ሺ ብር እያለ 11ኛው ዙር ላይ ከ3መቶ ሺ ብር ከፍ ያለ ዋጋ መጠራት ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው የተሰኘ የእንግሊዝኛ መጽሔት በነሐሴ 2006 በሠራው አንድ ዘገባ የአዲስ አበባ ሊዝ ዋጋ በየዓመቱ የ529 በመቶ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገሰግስ አስነብቦ ነበር፡፡
የ2ኛ ከተማ እጦት
አዲስ አበባ መሄጃ ባጣ ሕዝብ ተሰንጋለች፡፡ የነዋሪዎቿና የቤቶቿ ቁጥር በሚሊዮን ተኩል ልዩነት ያሳያል፡፡ ከተማዋ ከትንንሽ ከተሞች በሚፈልስ ሕዝብ ተወጥራለች፡፡ ሸክሟን የሚያቃልልላት 2ኛ ከተማ ተርባለች፡፡ ይህ በአዲስ አበባ መሬት እጅግ ዉዱ ንብረት እንዲሆን ጥርጊያ መንገድ አበጅቷል፡፡ የመሬት ዋጋ በማያቋርጥ ሆኔታ የሚያሻቅብ ሀብት ነው፡፡ ይህ የልብ ልብ የሚሰጣቸው ባለብሮች ባላቸው ጥሪት ሁሉ መሬት መግዛትን ይመርጣሉ፡፡ የሚገርመው የገጠር ሀብታሞች፣ ጥሬ ብር የቋጠሩ ገበሬዎችና የወፍጮ ቤት ባለቤቶች ጭምር ሊዝ በሚወጣበት ወር ተንደርድረው ወደ አዲስ አበባ መትመማቸው ነው፡፡
የመሬት ዋጋ መቆለል ከከተማዋ አግድም እድገትና ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ የተተበተበ ችጋር ጋር የሚተሳሰር ነው፡፡ ቀደም ባሉ መንግሥታት የተገነቡ ቤቶች 17ሺ የኪራይ ቤቶች ናቸው፡፡ 170ሺ የቀበሌ ቤቶች በአዋጅ 47/67 በዉርስ የተገኙ ናቸው፡፡ የሕዝብ ቁጥር ግን በአያሌው እያሻቀበ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ መሬት የሀብትና የደኅንነት ብቸኛው መገለጫ ሆኗል፡፡ በአሁኗ አዲስ አበባ መሬት ያለው ሰው ሙሉ ሰው ተደርጎ ይታሰባል፡፡
በተረጋጋ ሁኔታ ለመኖር የሚያስችል መጠለያን በኪራይ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የኪራይ ቤቶች ዉስጥ የተጠለለ ነዋሪ በአንጻራዊነት የተረጋጋ ሕይወት መምራት ይችል ነበር፡፡ አሁን ኪራይ ቤቶች ሳይቀሩ ለመንግሥት ሹመኞች ይፈለጋሉ እየተባለ ዘለግ ላሉ ዓመታት የኖሩ ተከራዮች እንኳ በስጋት እየከሱ ነው፡፡ ቀበሌ ቤቶች በልማት አፋፍ ላይ ያሉ የገደል አፋፍ መጠለያዎች ሆነዋል፡፡ ከግለሰብ ቤት መከራየት ሰቀቀኑ የትየለሌ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የቤት ባለቤት መሆን በንጉሡ ዘመን ከመሳፍንትነቱ ወገን የመሆን ያህል የሚያስመካ ሆኗል፡፡ ይህ ሁኔታ የትኛንም ዋጋ ከፍሎ የኔ የሚሉት መሬት በመዲናዋ ለማግኘት የሚደረገውን ሩጫ እንዲከር አድርጎታል፡፡
የቁጥ ቁጥ አቅርቦት
አዲስ አበባን በሥራ አስኪያጅነት የመሩትና በኋላም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር የኾኑት የቀድሞው ሹም አቶ መኩሪያ ኃይሌ ባንድ ወቅት የመሥሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ለሕዝብ እንደራሴዎች ሲያቀርቡ የሊዝ ዋጋ መናር ምክንያት በጥያቄ መልክ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ የሊዝ ዋጋ መናር መንግሥታቸውን የምር እንደሚያሳስበው ከገለጹ በኋላ ባለሐብቶች ገንዘባቸውን መሬት ላይ ሳይሆን ልማት ላይ እንዲያዉሉት ነው ፍላጎታችን ሲሉ አብራርተው ነበር፡፡ እርሳቸው በወቅቱ ችግሩን ሊያያዙት የሞከሩት መሬት በብዛት ለጨረታ ካለመቅረቡ ጋር ነበር፡፡
ለመሆኑ የሊዝ መሬት አቅርቦት ማነስና መብዛት ታሪኩን ይለውጠዋል? ብለን ብንጠይቅ ግን መልሳችን ግማሽ አውንታዊ፣ ግማሽ አሉታዊ ይሆናል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ሊዝ ዘገየ ከተባለ በየስድስት ሳምንቱ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ ወጥቷል፡፡ በአንድ ጊዜ በአማካይ 70 ያህል ቦታዎች ለጨረታ ይቀርባሉ፡፡ በአንድ ዙር ወደ ሁለት መቶ አምሳ ቦታዎች የቀረቡበት ጊዜም ነበር፡፡ ኾኖም በዚያ ዙር ዋጋ ተረጋግቶ ነበር ለማለት የሚያስደፍሩ ምልክቶች ታይተዋል ብሎ መደምደም የሚያስችል ዉጤት አልተመዘገበም፡፡
እርግጥ ነው በአንድ ክፍለ ከተማ በጣት የሚቆጠሩ ቦታዎች ብቻ ለጨረታ በቀረቡበት ሁኔታ በርከት ያሉ ተጫራቾች ለዉስን ቦታዎች ስለሚፎካከሩ ጠጠር ያሉ ዉጤቶች እንዲመዘገቡ እድል ሲፈጥር ታይቷል፡፡ ይህ በንፋስ ስልክ ሳርቤት ገብሬል እና በልደታ ኮንዶሚንየም አካባቢ ባለፉት ተከታታይ የጨረታ ዙሮች በወጡ ጥቂት ቦታዎች ላይ በጉልህ ተንጸባርቋል፡፡ ኾኖም ዋጋዎቹ የናሩት ብዙ መሬት በአንድ ጊዜ በገፍ ስላልቀረበ ብቻ ነው የሚለው ሚዛን የሚደፋ ምክንያት አልሆነም፡፡ መንግሥት ግን ሁሌም ለሊዝ መናር ምክንያት የሚያቀርበው በቂ መሬት በተከታታይ ለሊዝ አለማቅረቡን ነው፡፡ ይህ ጠቅላላውን መስል ለማየት አለመድፈር ነው፡፡ የአዲስ አበባ የመሬት ማዕዘን ባለ አንድ ንጣፍ አይደለም፡፡ ምስለ ብዙ ነው፡፡
እርግጥ ነው የብዙ ቦታዎች በተመሳሳይ ዙር ለጨረታ መቅረብ ተጫራቾች አማራጮች እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ በአንድ መሬት ላይ የሚቀርቡ ተጫራቾችን ቁጥር እንደሚወስን ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሾልከው በአጋጣሚ በትንሽ ብር ቦታ ማሸነፍ የቻሉ ሰዎች እንዳሉ ከ10ኛ ዙር በፊት የነበሩ ዉጤቶች ይመሰክራሉ፡፡ ይህ ግን ሁልጊዜ የሚያጋጥም ሳይሆን የሎተሪ ያህል የሚከሰት ከሺ አንድ ገጠመኝ ነው፡፡
መግለጫ ለ፣ በሦስት ዙሮች ከፍተኛ ቦታዎች ለሊዝ ገበያ ያቀረቡ ክፍለ ከተሞችና የቦታዎቹ ብዛት
ዉድ ነው? ወይስ አያዋጣም?
ዉድ ስንት ነው? የሚል ጥያቄ ብናነሳስ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ ነገር ግን ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ መሬት የሚሰጠው ዋጋ ዉድ ነው ስንልስ ምን ማለታችን ነው? አያዋጣም እያልን ነው? አይገባውም እያልን ነው? ወይስ ሌላ ያልታየ አማራጭ አለ ማለታችን ነው?
ዋጋን ዉድ ነው አይደለም ለማለት የንጽጽር መስመር ማስመር ይኖርብናል፡፡ አዲስ አበባ መነጻጸር ያለበት ደግሞ ከሌሎች መሬትን በተመሳሳይ የሊዝ ስሪት ከሚያስተዳድሩ የዓለም ከተሞች ጋር ሳይሆን በአገሪቱ ካለው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እውነቶች ነው፡፡ ሰው ይነስም ይብዛ ምክንያታዊ እንሰሳ ነው፡፡ ማንም ቢኾን የሠረቀውን ካልሆነ የሠራበትን እንዲሁ አይበትንም፡፡ ሰዎች ለሊዝ “ዉድ” ዋጋን የሚሰጡት ለመሬቱ የሚገባው ያ ዋጋ እንደሆነ በመረዳታቸው ቢሆንስ? አዋጪነቱን አስልተው ቢኾንስ?
ይህን የሚያጠናክርልን ቀደም ባሉ ዙሮች ዉድ በተባለ ዋጋ መሬት የገዙ ሰዎች አሁን ምን ላይ እንዳሉ ስንረዳ ብቻ ነው፡፡
ቦሌ ሚሊየንየም ጀርባ፣ ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ፣ ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ጉድ ያስባሉ ዋጋዎች ቀርበው የጋዜጣ ዜና ኾነው ነበር፡፡ አሁን እነዚያ ዋጋዎች ጉድ አያስብሉም፡፡ እንዲያውም በትንሽነታቸው ለማመን የሚቸግሩ ናቸው፡፡ እንዲያውም አሸናፊዉን እንደሎቶሪ እድለኛ የሚያስቆጥሩ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ሲታዩ ነው ታዲያ የገበያ አዋጪነታቸው ወለል ብሎ የሚታየው፡፡ በዚያን ወቅት የተጋነነ ዋጋ አቅርበው ያሸነፉ ባለሐብቶች መሬቱ ላይ ጅምር ግንባታ አካሄደው መሸጥ ቢያሰኛቸው እንኳ አሁን የሚያስመካ ትርፍ ይዘው መዉጣት ይችላሉ፡፡ መሬት ላይ አነስተኛ እሴት ብቻ በመጨመር የሚገኘው ትርፍ ተምቦል ያለ ነው፡፡
ይህ ሲታይ ታዲያ አስካሁን ዉድ ብለን የቆለልነው ካብ ሁሉ የምቧይ ካብ ይሆንብናል፡፡ በስካሁኑ ትንታኔያችን አንድ መሠረታዊ መረዳትን ሳንስት አልቀረንም፡፡ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ መረዳት፡፡