ዋዜማ- የተለያዩ አገልግሎቶች የተካተቱበት የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድን ከ17 የገቢ ምንጮች በቋሚነት ሀብት ለመሰብሰብ ታቅዷል። ለአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ገቢ ከሚሰበሰብባቸው የተለያዩ ምንጮች መካከል የባንክና ቴሌኮም አገልግሎቶች ተካተውበታል።

በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አዋጅ ቁጥር 1386/2017 መሰረት፣ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ገቢን የሚያስተዳደር ጽሕፈት ቤት እና  የገቢ ምንጭ ወሰን በሚስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ ተወስኗል። በደንቡ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ የገቢ አሰባሰብ፣ ምንጭ እና ምጣኔ የተወሰነ ሲሆን፣ ከመጪው የካቲት ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ከተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰበሰበው ሀብት የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ጽሕፈት ቤትን ለማቋቋም እና የሚሰበሰበውን የገቢ መጠን ለመወሰን የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 576/2018 በዝርዝር ተወስኗል። በደንቡ መሰረት ለአደጋ ምላሽ የሚሰበሰበው ጊቢ በ17 ምንጮች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ 15ቱ ምንጮች በአገልግሎት ሰጪዎች አማካኝነት ከሕዝብ የሚሰበሰቡ ናቸው።

ከ17 የገቢ ምንጮች መካከል ከፌደራል፣ አዲስ አበባና ድሬደዋ ዓመታዊ በጀት 0.25 በመቶ መዋጮና በግምሩክ ከተወረሱ ንብረቶት ውጪ፣ በተለያዩ አገልግሎቶች ከሕዝብ የሚሰበሰብ ነው። ከፍተኛው ገቢ  የሚሰበሰብበት የግምሩክ ኮሚሽን ከሕገ ወጥ ንግድ ከተወረሰ ንብረት ሽያጭ የሚገኝ 60 በመቶ ነው።

ገቢው ከየትኞቹ አገልግሎቶች ይሰበሰባል?

የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ የሚሰበሰብበት አግባብ በተደነገገበት ደንብ ላይ የገቢ ምንጭ ተብለው በግልጽ የተቀመጡት አብዛኛዎቹ በአገልግሎት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የገቢ ምንጩ የባንክና ፋይናንስ፣ የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የፓስፖርትና ቪዛና የንግድ ፈቃድ አገልግሎቶችን ያካተተ ነው።

የአገልግሎት አሰባሰቡ በየወሩ፣ በሩብ ዓመትና በዓመት ኹለት ጊዜ እና በአንድ ዓመት የሚሰበሰብ መሆኑን ዋዜማ የተመከተችው ደንብ ያመለከታል።

 በየወሩ ገቢ የሚሰበሰብባቸው 

  1. ​የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ለድምፅና ዳታ አየር ስዓት ዋጋ አምስት በመቶ 
  2. ​ባንኮች፣ አነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰጡት የብድር መጠን አንድ በመቶ
  3. የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከሚከፍሉት የአገልግሎት ክፍያ አምስት በመቶ
  4. የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በሚሰበስቡት የፕሪሚየም አገልግሎት አንድ በመቶ
  5. ከሀገር ውስጥ የአየር በረራ ትኬት በአንድ በረራ ትኬት 100 ብር
  6. ከፓስፖርትና ቪዛ አገልግሎት ክፍያ በየአንዳንዱ 200 ብር
  7. ከሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት አምስት በመቶ
  8. በማንኛውም ንግድ ፈቃድ ማውጣትና ማደስ አገልግሎት 200 ብር
  9. ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችን በሚያቀርቡት ሽያጭ ላይ በአንድ ሌሊት አንድ ብር
  10. ከኬሚካል አምራች ድርጅቶችና አስመጪዎች ሽያጭ ላይ 100 ብር
  11. ከሀገር ውስጥ ትንባሆና አልኮል ምርቶች ሽያጭ እና ከውጭ በሚገቡ የትንባሆና አልኮል ምርቶች ሽያጭ ላይ አምስት በመቶ
  12. ከባህር ትራንስፖርትና የሎጀስቲክስ አገልግሎት ከሚሰጠው አገልግሎት አምስት በመቶ
  13. ከሎተሪ ትኬት ሽያጭ እና የዕድል አሸናፊዎች 100 ብር  

በየሩብ ዓመት የሚሰበሰቡ

  1. ከፌዴራል መንግሥት የበጀት አስተዋጽኦ 0.25 በመቶ
  2. ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሚ አስተዳደሮች በጀት አስተዋጽኦ 0.25

በዓመት ኹለት ጊዜ የሚሰበሰብ 

  1. ከፌዴራል ግምሩክ ኮሚሽን ከሕግ ወጥ ንግድ ከተያዙ እቃዎች ከሚያገኘው ሽያጭ 60 በመቶ

በየዓመት አንድ ጊዜ የሚሰበሰብ

  1. ከማንኛውም የአክሲዮን ከሚገኝ የትርፍ ድርሻ አንድ በመቶ

ከ17 የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ምንጮች በሚሰጧቸው አገልግሎቶች አማካኝነት ገቢ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት፣ በደንቡ በተደነገገው ጊዜ ገደብ ውስጥ የሰበሰቡትን ገንዘብ የማስገባት ግዴታ ተጥሎባቸዋል። 

የአደጋ ስጋት ሥራ ምላሽ ፈንድ ገቢ ከመጪው የካቲት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ መኖሩን ዋዜማ ሰምታለች። ከተለያዩ አገልግሎቶች ገቢ መሰብሰብ የሚያስችለው ደንብ በሚኒስትሮች ምት ጸድቆ በነጋሪት ጋዜጣ የታተመው፣ ህዳር 2/2018 ዓ.ም ነበር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው አዲስ ደንብ ቁጥር 576/2018 መሰረት የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ጽሕፈት ቤት እየተደራጀ ነው ተብሏል። በቦርድ የሚመራው ጽሕፈት ቤቱ የሚሰበሰበውን ሀብት የማስተዲደር ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት ነው። [ዋዜማ]