ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ የአስሩ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ከተሸኘው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን ማፍረስ በሚቻልበት ሁኔታ ዙርያ እየመከሩ ነው፡፡ ከንቲባ ድሪባ በሚመሩት በዚህ ዝግ ስብሰባ ላይ ከቀረቡ አከራካሪ ነጥቦች አንዱ በአዲስ አበባ አራት ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ሰፋፊ ሕገ ወጥ ግንባታዎች የማፍረስ ዘመቻ መቼ ማካሄድ አለብን የሚለው ነው፡፡
በዚህ ዝግ ስብሰባ ከአስሩ የሥራ አስፈጻሚዎች በተጨማሪ የየክፍለ ከተሞቹ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ እንዲገኙ ተደርጓል፡፡
ከወራት በፊት በተደረጉ ተመሳሳይ የመስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች የተገኙባቸው ስብሰባዎች በ2009 አዲስ የማፍረስ መርሐ ግብር እንደማይኖርና ከዚያ ይልቅ የፈረሱ ቦታዎችን ለባለሐብቶች የማስተላለፍና የማልማት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በስፋት ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህ አቋም ተይዞ የነበረው አገሪቱ አጋጥሟት ከነበሩ ሕዝባዊ አመጾች ጋር በተያያዘ ነዋሪዎችን ለማረጋጋት እንደነበር ይገመታል፡፡
አሁን የአዲስ አበባ መስተዳደር የአቅጣጫ ለውጥ ለማድረግ እየመከረ እንደሚገኝ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ የሚሰሩ አንድ ኃላፊ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ይኸውም የማፍረስ ዘመቻን ላልተወሰነ ጊዜ ከማዘግየት ይልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ ቀደም ብሎ ቢካሄድ ለቁጥጥር አመቺ መኾኑ በአንዳንድ ሹማምንት ዘንድ በመታመኑ ነው፡፡
ኾኖም በርሳቸው የግል አመለካከት የማፍረስ ተግባሩን መስተዳደሩ ልጀመር ቢል እንኳ የደኅንነት መዋቅሩ ይህ እንዲሆን ይፈቅዳል የሚል ግምት የላቸውም፡፡ “በኔ እምነት በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ዉስጥ አዲስ አበባ ላይ ቤት ማፍረስ የሚታሰብ አይሆንም፡፡”
የካ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ዉስጥ በድምሩ ከ40ሺ የሚልቁ ሕገወጥ ግንባታዎች እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በግብረ ኃይል እንዲፈርሱ ቀን ተቆርጦላቸው የነበሩ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ጀሞ ሁለት አካባቢ በተለምዶ ሱቄ ሰፈር፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቀርሳና ኩንተማ ሰፈሮችን የሚጎራበቱ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በኮልፌ ቀራንዮ በተለምዶ ስልጤ ሰፈር አካባቢ ይጠቀሳሉ፡፡ ኾኖም የማፍረስ ሂደቱ በድንገት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ከመስተዳደሩ መመሪያ ተላልፎ ነበር፡፡
ከዚያ በኋላም አቧሬ ሚስፎርድ ሰፈር፣ ቦሌ አድዋ ፓርክ ዉስጥ የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች፣ አምባሳደር ፖስታ ቤት ጀርባ ጥቂት የንግድ ቤቶችና መኖርያዎች በአጭር ጊዜ ዉስጥ እንደሚፈርሱ እቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ይህም እቅድ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የክፍለ ከተማ የመሬት ማደስ ባለሞያዎች እንደሚገምቱት የማፍረስ ዘመቻው እንዲዘገይ የተደረገው በአገሪቱ አብዛኛዎቹ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች አለመረጋጋት መከሰቱን ተከትሎ ቤት የማፍረሱ ተግባር ቢቀጥል በዋና ከተማዋ ትኩስ እምቢተኝነት ሊቀሰቀስ ይችላል ከሚል ስጋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡
ምናልባት አሁን እየተደረገ ባለው ምክክር የ10 ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች ከ2003 ወዲህ የተገነቡ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን የማፍረስ ተግባር እንዲቀጥል ከወሰኑ በመጀመርያው ዙር ወደ ተግባር የሚገባባቸው በእነዚሁ አራት ክፍለ ከተሞች የተዘረዘሩ ወረዳዎች እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ከአዲስ አበባ መስተዳደር የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት የቀረበ አንድ ሪፖርት እንደሚያትተው በ2008 ዓ. ም ብቻ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የሚገኙና ሕገ ወጥ ናቸው የተባሉ 11ሺ 691 ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡ በሃና ማርያም ሰፈር ደግሞ ተጨማሪ 1ሺ 860 ቤቶች እንዲፈርሱ ሆነዋል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ ዓመት ዉስጥ 4ሺ ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ በዚህ ሂደት በአንድ ዓመት ዉስጥ በከተማዋ የተፈናቀለው ቤተሰብ ቁጥር ከ30ሺ እንደሚልቅ ይገመታል፡፡
የመስተዳደሩ የደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር አሳዬ አምባዬ ከሦስት ወራት በፊት ለመንግሥት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሕገ ወጥ ግንባታንና የመሬት ወረራን የመከላከል ሥራው በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለው ነበር፡፡
መስተዳደሩ የመሬት ወረራ የሚፈጽሙ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ከክፍለ አገር የሚመጡ ዜጎችና በአጭር ጊዜ መክበር የሚፈልጉ የመሬት ደላሎች ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ አብዛኛዎቹ ሕገ ወጥ መሬት ወራሪዎች ቁራሽ መሬት ከአርሷደር በካሬ ሜትር እየገዙ አጥረው የሚይዙ ባለሀብቶች እንጂ ቤት አልባ ነዋሪዎች ዋነኛ መሬት ወራሪ እንዳልሆኑ የመስተዳደሩ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ይከራከራሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ስማቸው ማንጎ፣ ቀርሳና ኩንተማ በተባሉ ሠፈሮች ሕገ ወጥ የተባሉ ነዋሪዎችን ለማጽዳት በተደረገ ሙከራ የወረዳውን ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት ስለመጥፋቱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎም እንዲሁ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ስሙ ወረገኑ በተባለ ሰፈር ሕገወጥ የተባሉ ቤቶችን በግብረኃይል ለማፍረስ የተወሰደው እርምጃ ደም አፋሳሽ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በደንብ ማስከበር ግብረኃይል በተለያዩ የከተማዋ ሰፈሮች በአስቸኳይ እንዲፈርሱ የሚደረጉ ቦታዎች ለዓመታት እንደታጠሩ ይቀመጣሉ፡፡ በቅርቡ ለመስተዳደሩ ኃላፊዎች የቀረበ አንድ ጥናት በከተማዋ 750 ቦታዎች ታጥረው ለዓመታት ተቀምጠዋል፡፡ እንደምሳሌ ከቀሩቡት ዉስጥ በሜድሮክ ታጥረው የተያዙ ቦታዎች በአማካይ ለ15 ዓመታት ታጥረው ያለምንም ግንባታ ተይዘዋል፡፡
በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በኃይል እንዲፈርሱ ከተደረጉ ሰፈሮች ዉስጥ አንዳቸውም ከመታጠር ዉጭ ወደ ልማት አልገቡም፡፡