ዋዜማ ራዲዮ- የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሪክ ቲለርሰን በመጪው ሳምንት ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የአፍሪቃ ሀገራትን ይጎበኛሉ።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሐሞስ ዕለት ይፋ እንዳደረገው ሚንስትሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ ጅቡቲ ቻድና ናይጀሪያን ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 4 ድረስ ይጎበኛሉ።
የአዲስ አበባ ቆይታቸው በዋነኝነት የአፍሪቃ ህብረት ኮምሽን ውስጥ የተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ተወካዮችን በማነጋገር ላይ ያተኮረ ሲሆን በተጓዳኝ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስጣናት ጋር በሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ይነጋገራሩ።
ቲለርሰን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙት በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል የዲፕሎማሲ ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመቃወም ባሻገር ለፖለቲካዊ ቀውሱ ሁሉን አቀፍ ድርድር እንዲደረግ ትፈልጋለች። የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮችም በኢትዮጵያ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ምርመራ እንዲደረግ የሚጠይቅ የህግ ረቂቅ(HR-128) አዘጋጅተው ለውሳኔ እየተጠባበቁ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ግን ለቀረቡት አማራጮች አሻፈረኝ እንዳለ ነው።
ቲለርሰን ወደ አፍሪቃ ያቀኑት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪቃውያንን የሚያንቋሽሽ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነገሩን ለማብረድና ለአፍሪቃውያን ያላቸውን ትኩረት ለመግለፅ የውጪ ጉዳይ ሚንስትራቸውን ወደ አፍሪቃ እንደሚልኩ ቃል በገቡት መሰረት ነው።
ቲለርሰን በአመዛኙ በአሜሪካ የፀረ ሽብር ትብብርና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ከአፍሪቃውያኑ መሪዎች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።