ዋዜማ ራዲዮ-በኢትዮጵያ በስፋት የሚታየውን የስብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ ተከትሎ የአሜሪካ ኮንግረስ HR128 የተባለውን የህግ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ አፀደቀው።
ኮንግረሱ ማክስኞ ባደረገው ስብሰባው ድምፅ መስጠት ሳያስፈልግ የውሳኔ ሀሳቡን አፅድቆታል።
በውሳኔ ሀሳቡ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ፣ ተጠያቂዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ አፋኝ ህጎች እንዲሻሩ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ያሳስባል።
ከሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት አካታች የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠርም የውሳኔ ሀሳቡ ይጠይቃል።
ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የልማት ዕርዳታና የፀጥታ ትብብር ድጋፍ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ይህንንም የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በኢትዮጵያ በግድያና መብት ጥሰት መሳተፋቸው የተረጋገጠ ባለስልጣናት ላይም የጉዞ ዕግድና የንብረት/የገንዘብ እቀባ እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፏል።
ኮንግረሱ የውሳኔ ሀሳቡን ከማፅደቁ አንድ ቀን አስቀድሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሀን ለኮንግረሱ አባላት በፃፉት ደብዳቤ ኮንግረሱ ውሳኔውን እንዳያፀድቅ አሳስበው ውሳኔው ከፀደቀ የሁለቱ ሀገሮችን ግንኙነት ይጎዳል፣ ውጤታማም አይሆንም ብለዋል።
ሀገራችን በአዲስ የፖለቲካ ተሀድሶ ላይ በመሆኗ እየተደረገ ያለው የፖለቲካ ማሻሻያ ውጤት ጊዜ ተሰጥቶ ሊታይ ይገባል ብለዋል አምባሳደሩ።