ዋዜማ ራዲዮ- የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማን በትግራይ ቀውስና በሌሎች ክፍለ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ሰኞ ዕለት ወደ ምስራቅ አፍሪካ አምርተዋል።
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተሰየሙት ልዩ መልዕክተኛው ፊልትማን የትግራይን ጦርነት ጨምሮ በሕዳሴው ግድብ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብ ዙሪያ መፍትሄ የማፈላለግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል።
በአንድ ሳምንት ቆይታቸው ሱዳንን፣ ግብጽን፣ ኤርትራን እና ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ። ከየሀገራቱ ባለስልጣናት ጋር የመነጋገር መርሀ ግብር እንዳላቸውም ከአሜሪካ የወጪ ጉዳይ መስሪያቤት የገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ልዑኩ በትግራዩ ቀውስ ዙሪያ ግጭት ቆሞ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ፣ ድርድር እስከማስጀመር የሚደርስ ሀሳብ እንዳላቸው በስፋት እየተነገረ ነው። በአዲስ አበባ ከአፍሪቃ ኅብረትና ከመንግስታቱ ድርጅት ሀላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ተነግሯል።
በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ክበብ፣ ፊልትማን የጠ/ሚ ዐቢይን አስተዳደር አጥብቀው የሚተቹና የሚቃወሙ ተደርገው ይቆጠራሉ። በቅርብ ያንጸባረቁዋቸውን አንዳንድ አቋሞች በመጥቀስም ዲፕሎማቱ ገለልተኛ መፍትሔ አፈላላጊ ሊሆኑ አይችሉም የሚል ጠንካራ ስሜት መኖሩን የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ። በዚህም የተነሣ ፊልትማን ሞቅ ያለ አቀባበል እንደማይጠብቃቸው ከወዲሁ ተገምቷል።
ጄፍሪ ፊልትማን አንጋፋ ዲፕሎማት ሲሆኑ የመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካና የፀጥታ አማካሪ በመሆን ስርተዋል። በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለይም በሶሪያና ሊባኖስ ጦርነት ቆሞ ሰለም እንዲመጣ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ዋና ልዑክ በመሆን አገልግለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]