ዋዜማ ራዲዮ- በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ምክትል ሀላፊ ዶናልድ ያማማቶ የተመራ የአሜሪካ የልዑካን ቡድን ወደ ኤርትራ አቀና።
የልዑካን ቡድኑ ከስኞ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአስመራ በሚኖረው ቆይታ ከሀገሪቱ ባለስልጣናትና በአስመራ ተቀማጭ ከሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረስብ አባላት ጋር ይነጋገራል።የልዑካን ቡድኑ ተልዕኮውን በይፋ አላሳወቀም።
የጉብኝቱ ዋና ተልዕኮ በኤርትራ መንግስት ተይዘው ለእስር የተዳረጉ የአሜሪካ ኤምባሲ ስራተኞች ጉዳይ እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል።
እግረ መንገድም በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የድንበርና የፖለቲካ ችግር መፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይ የልዑካን ቡድኑ ሀሳብ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የልዑካን ቡድኑን አግኝተው ለማነጋገር ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ማረጋገጫ አልሰጡም።
በአስመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ስራተኛ የሆኑ ኤርትራውያን ሰራተኞች ያለፉትን ሶስት አመታት በእስር ላይ ናቸው። ስራተኞቹ ለአሜሪካ መንግስት መረጃ ታቀብላላችሁና ታሴራላችሁ የሚል ውንጀላ ቀርቦባቸው ነበር የታሰሩት።
ያማማቶ ኤርትራ ከጅቡቲና ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበት የድንበር ቀውስና ጦርነትን በዘላቂነት መፍታት ዋና ተልዕኳቸውሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት አስተያየት የሰጡን አሉ።
ለአሜሪካ መንግስት ምስጢር ቅርበት ያላቸው ምንጮች በበኩላቸው አሜሪካ በጅቡቲ ያላት የጦር ሰፈር አንድም በርካታ ሀገራት ተመሳሳይ የጦር ሰፈር በመክፈታቸው ሌላም የጅቡቲ መንግስት የአየር ተቆጣጣሪዎች በተደጋጋሚ ባሳዩት እንዝላልነት በተከሰቱ አደጋዎች ሳቢያ የጦር ሰፈሩን ወደ ኤርትራ የማዘዋወር ሀሳብ እየተብላላ ነው ይላሉ። ይህን አስተያየት ዋዜማ ከገለልተኛ ወገን አላጣራችም።
በቅርቡ ሁለት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች በአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ቸልተኝነት ተላትመው መውደቃቸው ይታወሳል። ጅቡቲያውያኑ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጫት አብዝተው በመቃምና በሌሎች የድስፕሊን ችግሮች በተደጋጋሚ ለተፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂ መሆናቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት ያምናሉ። የጦር ሰፈር ኪራይንም በተመለከተ ጅቡቲ ያደርገችው ጭማሪ ዋሽንግተንን እንዳላስደሰተ ይነገራል።
አሜሪካ ከአስመራ ጋር ግንኙነቷን ማደስ ከፈለገች በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ችግር መፈታት እንዳለበትም የዲፕሎማቲክ ምንጮች ያሰምሩበታል።
ዶናልድ ያማማቱ በዚሁ ሳምንት ወደ ጅቡቲና ኢትዮጵያ አቅንተው በጋራና አካባቢያዊ ጉዳዩች ለመመካከር ዕቅድ መያዛቸውን ከአሜሪካ የውጪጉዳይ መስሪያቤት የተገኘ መረጃ ያመልክታል።