FILE
  • ፓርላማው አስቸኳይ ሰብሰባ ተጠርቷል


ዋዜማ- የአለም የገንዘብ ድርጅት ስራ አስፈፃሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ 3.4 ቢሊየን ዶላር ብድር አፀደቀ።

ላለፉት አምስት ዓመታት ሲጓተት የነበረው ይህ ብድር የተፈቀደው ለሶስት አመታት ያህል በመንግስትና በአበዳሪዎች መካከል ዘለግ ያለ ድርድር ከተደረገ በኋላ ነው። አሁን ከተፈቀደው በአራት አመት የሚለቀቅ 3.4 ቢሊየን ዶላር ውስጥ አንድ ቢሊየን ዶላሩን ለኢትዮጵያ በአፋጣኝ ይተላለፋል።

ብድሩ፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃግብር ለመደገፍ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን ለማስወገድ፣ የውጭ ዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እና አካታች፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራና ለከፍተኛ ዕድገት መሠረት ለመጣል እንደሚውል ድርጅቱ ገልጧል። ድርጅቱ ብድሩን መልቀቁ፣ ሌሎች የአገሪቱ የልማት አጋሮችና አበዳሪዎች ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ በር ይከፍታል ተብሏል።

ዋሽንግተን ላይ ዛሬ ከቀትር በኋላ የተሰየመው የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF)ካፀደቀው ብድር በተጨማሪ ሌሎች የልማት አጋር አበዳሪዎች ይፋ የሚያደርጉት የብድር ስምምነት እንደሚኖር በመድረኩ ላይ ተነግሯል።

የአለም የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረገውን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግስት 10.7 ቢሊየን ዶላር ያህል ብድር ከተለያዩ የልማት አጋሮች ቃል እንደተገባለት ሲያስታውቅ ሰንብቷል።


ይህን አለማቀፍ ብድር ለማግኘት የተለያዩ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎችን ስታደርግ ስንብታለች፣ በተለይ ኢትዮጵያ የብር የምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን የሚያስችል አዲስ ፖሊስ ተግባራዊ ተደርጓል።

ፖሊሲው ተግባራዊ መደረግ በጀመረበት የመጀመሪያው ቀን የብር የምንዛሪ ተመን 30 በመቶ ዝቅ ብሏል።
መንግስት ይህን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ፈተናዎችን ያስከትላል በሚል የበረታ ትችት እየቀረበበት ነው።

በነገው ዕለት ማክሰኞ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን በተመሳሳይ ለኢትዮጵያ ዳጎስ ያለ የብድር ድጋፍ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመንግስት በኩል የሚንስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ምክክር ለማድረግ አራት ኪሎ ቀጠሮ ይዟል።
በእረፍት ላይ ያሉ የፓርላማ አባላትም ለአስቸኳይ ስብሰባ እረፍት አቋርጠው ስብሰባ እንዲቀመጡ ተጠርተዋል። የብድር ስምምነቶችን ያፀድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ]