(ዋዜማ ራዲዮ) ሕዝብን ከመሬቱ ለሚያፈናቅሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ የነበረው የዓለም ባንክ ሲቀርብበት የነበረውን ስሞታና ነቀፌታ ይመልሳል የተባለ አዲስ ተግባራዊ ርምጃ መውሰድ መጀመሩ ከሰሞኑ ይፋ ሆኗል፡፡
ሕዝቡን ከቀዬውና ከመንደሩ በመንቀል፣ የግዳጅ ሠፈራና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማሉ” የሚል ክስ ተደጋግሞ የሚቀርብባቸው እንደ ኢሕአዴግ ያሉ መንግስታት ይህን የዓለም ባንክን እርምጃ በቀላሉ ላይቀበሉት እንደሚችሉ የሚገልጹ ታዛቢዎችም ይህ የዓለማችን ግዙፍ አበዳሪ ተቋም ከረፈደም ቢሆን የአቋም ለውጥ ማምጣቱ መልካም መኾኑን በመጥቀስ ተስፋቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል… ባንኩ በፋይናንስ የሚደግፈው ፕሮጀክት… ሕዝብን ከመሬቱና ቀዬው ያለፈቃዱ በማፈናቀል ጉልህ አብነት ይሆናል።
ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መዝገቡ ሀይሉ ያቀርበዋል
የዓለም ባንክ እንደ ግድብ፣ መንገድና የኃይል ማመንጫ ለመሳሰሉ የልማት ፕሮጀክቶች ብድርና ዕርዳታ የሚያቀርብ ሲኾን ከሰፈራ ጋር ትስስር ያላቸውንም ፕሮጀክቶች የሚያግዝ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአበዳሪ ተቋሙ የሚረዳቸው ከሠፈራ ጋር የተገናኙ ፕሮጀክቶች መጠን እየበዛ መምጣቱም ይነገራል፡፡ ከሠፈራ ጋር ትስስር ያላቸው በባንኩ የሚደገፉ የፕሮጀክቶች መጠን እ አ አ በ1993 ዓ.ም ስምንት በመቶ የነበረ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ወደ ሃያ ዘጠኝ ከመቶ ከፍ ማለቱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2004 እስከ 2013 ዓ/ም ባሉት ዓመታት ውስጥ ከነዚህ በዓለም ባንክ ከሚደገፉ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ ለአካላዊና ኡኮኖሚያዊ ተፈናቃይነት የተዳረገው ሕዝብ ብዛት 3.4 ሚሊየን መድረሱም ተጠቁሟል፡፡ በጥናት የተደገፈና በሕዝብ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሠፈራ ጠቀሚነቱ የጎላ የመሆኑን ያሕል፣ በመንግስታት አስገዳጅነት የሚካሄድ ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግጋት ክልክል ከመሆኑ ባሻገር ቀውሱም ቀላል አይሆንም፡፡ ይሕን መሰረት በማድረግ ነበር የሠብዓዊ መብት ተቋማት የዓለም ባንክ ዜጎቻቸውን በኃይል ከመሬቱ ለሚያፈናቅሉ መንግሥታት የሚለግሰውን ገንዘብ እንዲቆጣጠር አልያም እንዲያግድ ተቃውሞና ትችታቸውን ሲያሰሙ የቆዩት፡፡
የዓለም አቀፉን ተቋም ፈንድ ካዝናቸው እያስገቡ በግዳጅ ሠፈራ ፕሮግራማቸው የመብት ረገጣ ከሚፈጸምባቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ያስረዱ የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች ለበርካታ ዓመታት በጋምቤላ ክልልና በሰሜን ኦሞ በኢሕዴግ መንግስት ተፈጽሟል ያሉትን ግፍና መከራ ጥናት በማድረግ ያዘጋጁትን ሪፖርት፣ በተጎጂዎች ምስክርነት አስደግፈው በማቅረብ ይፋ አድርገውታል፡፡ ከነዚህም መሐል እንደ “ዘ ጋርዲያን” ያሉ ጋዜጦች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ኮንሰርቲየም፣ ሠርቫይቫል ኢንተርናሽናል፣ ኢንክሉሲቭ ዲቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
የዓለም ባንክ በጋምቤላ ክልል የሚያካሂደው “የመሰረታዊ አገልግሎቶች ጥበቃ” (“ፕሮቴክሽን ኦፍ ቤዚክ ሰርቪስስ”-) የተሰኘ ፕሮግራም የሚሰጠው ገንዘብ በኢሕአዴግ በሚፈጸመው የግዳጅ ሠፈራ ለበርካታ የአካባቢው ተወላጆች መፈናቀል፣ መታሰር፣ መሰደድ፣ ብሎም መገደል ሠበብ እንደሆነ የሚያስረዱ የመብት ተሟጋቾችና የምርመራ ተቋማት ፤ ባንኩ ለበርካታ ዓመታት የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ጭምር በመጣስ ሲያቀርቡለት የነበረውን ማመልከቻ ተመልክቶ መፍትሔ አለመስጠቱን ተችተዋል፡፡እነኝህን የመብት ጥሰቶች አስመልክቶ አስረጂ ደብዳቤና ደጋፊ ማስረጃዎች የተላኩለትየዓለም ባንክ በጊዜው ተግባራዊ ውሳኔ ባያሳልፍም፣ በወቅቱ ወደ ጋምቤላ ክልል አጣሪዎቹን ልኮ ያገኘው ተጨማሪ መረጃ ለሰሞኑ ውሳኔ መንደርደሪያ ሳይሆነው እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
በፈረንጆች አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች በጋምቤላ ስለፈጸሙት ጥቃት ለባንኩ መረጃ መላኩንና የባንኩ አጣሪ ቡድንም በጃንዋሪ 2013 ዓ.ም ሥፍራው ድረስ ተወካዮቹን ልኮ ሪፖርት መሰብሰቡን የገለጸው ዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኝነት ኮንሰርቲየም አጣሪው ቡድን ያገኘውን መረጃ ለቦርዱ ወዲያውኑ ማቅረቡን፣ ቦርዱ ግን የደረሰበትን ድምዳሜ “ሳጥን ውስጥ ቆልፎበት” ከርሞ የዛሬ ዓመት ይፋ እንዳደረገው አጋልጧል፡፡ በዚህ ይፋዊ ሪፖርትም ቢሆን የዓለም ባንክ የኢሕአዴግ መንግስት ፈጽሟቸዋል የተባሉት የመብት ረገጣዎች ከተለቀቀው ፈንድ ጋር ትስስር የለውም የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ ነው የተነገረው፡፡
የዓለም ባንክ ከምርጫ 97 በኋላ በገዢው ፓርቲ የተፈጸመውን የመብት ጥሰት ተከትሎ ዕርዳታውን አቋርጦ እንደነበር የሚታወቅ ሲኾን የኢትዮጵያ መንግስት ድሕነትን በመቀነስ እንዲሁም ድርቅና ረሃብን በማስወገዱ ረገድ አሳይቷል በተባለው “ስኬት” ምክንያት ከ1998 ዓ.ም አንስቶ ይህንኑ “መሰረታዊ አገልግሎት ጥበቃ” (ፒቢኤስ) ፈንድን እንዳስቀጠለ ገልጿል፡፡ ከዚሁ የአንድ ዓመት ማዕቀብ በኋላ ዕገዳውን ሲያነሳ በ“ፒቢኤስ” ፕሮግራሙ አማካኝነት 225 ሚሊየን ዶላር ለግሷል፡፡ እኤአ በሜይ 2009 ዓም ደግሞ 540 ሚሊየን ዶላር ጨምሯል፡፡ ከዚያ ወቅት አንስቶ ኢሕአዴግ የዓለም ባንክ ኃላፊዎችን ሳያማክር የሠፈራ ፕሮግራሙን መጀመሩን የገለጹ ምንጮች በጃንዋሪ 2011 የባንኩ ኃላፊዎች ባቀረቡት ጥያቄ ምክንያት ማብራሪያ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፌደራልም ሆነ የክልል ባለሥልጣናት ሠፈራው በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው ሲናገሩ የሚደመጡት፡፡ ይሕም ለሕዝቡ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ወፍጮ፣ ትምሕርት ቤት የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች በተሟላበት፣ የምግብ ዋስትናውም ሊረጋገጥ በሚችል መልኩ መከናወኑንም ያስረዳሉ፡፡ በመንግስት ተከናወነ ያሉትን የግዳጅ ሠፈራ በመቃወማቸው ለጥቃት መጋለጣቸውን፣ ከኢሕአዴግ መንግስት ወታደሮች ጥይት ማምለጣቸውን የገለጹ በኬንያና ደቡብ ሱዳን ስደተኞች ካምፕ የተጠለሉ የአካባቢው ተወላጆች ግን የመንግስት ወታደሮች በተወላጆቹ ላይ የፈጸሙት ግፍ አሰቃቂና በተገቢው ሁኔታ ያልተገለጸ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መንግስት ያለ ሕዝቡ ፈቃድና ይሁንታ ባካሄደው በዚህ የግዳጅ ሠፈራ፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው መሬት መፈናቀላቸውን የሚያስረዱ ምንጮች ሠፈራውን የተቃወሙ ነዋሪዎች በተለይ የአኙዋክ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙንና በዚህም ጦስ የተገደሉም እንዳሉ ዘርዝረዋል፡፡ ገዢው ፓርቲ የታጠቁ ወታደሮችን በማሰማራት ድብዳባ መፈጸሙን፣ ሰዎች ወታደራዊ ካምፕ ተወስደው ቶርቸር እንደተፈጸመባቸው ከጥቃቱ ያመለጡም በጎረቤት ሃገራት ስደተኛ ካምፖች እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ በተለይ በአኙዋኮች ላይ ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በቅርበት መከታተሉን የጠቆመው “ኢንክሉሲቭ ዲቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል” በመንግስት ተፈጽሟል ያለውን ድርጊት “በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ጥፋት” ሲል ኮንኖታል፡፡
ከኃይል እርምጃው ባሻገር ገንዘቡ ከታቀደው ዓላማ ውጪ እንደሚውልና በሙስና እንደሚባክን የሚያስረዳ ምስጢርም ይፋ ኾኗል፡፡ የመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ሳይቀር ከዚሁ የዓለም ባንክ ፈንድ እንደሚከፈል ተነግሯል ፡፡ ሁለት የኢሕአዴግ የቀድሞ ባለሥልጣናት ለምርመራ ጋዜጠኞቹ ኮንሰርቲየም በሰጡት መረጃ ከዓለም ባንክ ከተለቀቀው 2 ቢሊየን ዶላር ውስጥ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲዞር መደረጉን ተናግረዋል ፡፡ ለምርመራ ጋዜጠኛ ቡድኑ ቀደም ባለው ጊዜ ቃላቸውን ከሰጡት መሐል የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ኦሞት ኦቦንግ ከተላከው ፈንድ ውስጥ በሳቸው በራሳቸው ትዕዛዝ 10 ሚሊየን ብር ወደ ሌላ ወዳልተጠቀሰ አገልግሎት መዛወሩን ያጋለጡ ሲሆን፤ በእሳቸው የአመራር ዘመን ትምሕርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ኦቶው ኒይግዎ የዓለም ባንክ ፈንድ በሌላ ጉዳይ ላይ እንዲውል መደረጉን ማረጋገጫም ሠጥተዋል፡፡
ከወራት በፊት ለ“ኢንተርናሽናል ኮንሶርቲየም ኦፍ ኢንቨስቲጌቲቭ ጆርናሊስትስ” የምርመራ ጋዜጠኝነት ቡድን በአስተርጓሚነት ይሰራ የነበረው ፓስተር ኦሞት አጉዋ ከሌሎች ሁለት የክልሉ ተወላጆች ጋር በመንግስት ኃይሎች ታስሮ በአሸባሪነት መከሰሱ ገዢው ፓርቲ ምስጢሩን ለማፈን የተጓዘበትን ርቀት ያሳያል ያሉም አልጠፉም፡፡
የዓለም ባንክ ለበርካታ ዓመታት በልማት ሠበብ የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግላቸው መንግስታት የሚፈጽሙትን የመብት ረገጣና ማፈናቀል ከግምት ሊያስገባ ቀርቶ የራሱን መተዳደሪያና ደንብ እንኳ ለማክበር ዳተኛ እንደነበር የሚገልጹ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የአሁኑ ውሳኔው ቁጥጥርና ክትትል ካልተለየው ተስፋ እንዳለው ነው የሚገልጹት፤ ውሳኔው መልካም ነገር ይዞ መምጣት አለመምጣቱ ደግሞ በጊዜ ሂደት የሚታይ ይኾናል፡፡