ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት የነዳጅ ድጎማን አስመልክቶ እከተለዋለሁ ያለውን አዲስ እርምጃ በሀምሌ ወር የሚጀምር ሲሆን ዋዜማ ራዲዮ ከሁነኛ ምንጮቿ እንደሰማችው የነዳጅ ድጎማ የማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች ከሀምሌ ወር ጀምሮ በተለያየ ደረጃ የነዳጅ ድጎማው እንዲነሳ ተደርጎ በቀጣይ አመት ሚያዝያ ወር ላይ ሙሉ ድጎማውን ለማንሳት አቅዷል።።
በሀምሌ ወር ላይ በአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ በመመስረት የነዳጅ ድጎማ ለማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች መንግስት ሲያደርገው ከነበረው ድጎማ 25 በመቶው እንደሚነሳ ሰምተናል።
በቀጣይ መስከረም 2015 ዓ.ም ላይም በዚሁ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ የማይካተቱ ተሽከርካሪዎች 50 በመቶ ድጎማ የሚነሳ ሲሆን ፣ በታህሳስ 2015 ዓ.ም ወር 75 በመቶው ድጎማ ከተነሳ በኋላ በሚያዝያ ወር ደግሞ ድጎማው ሙሉ ለሙሉ ይቆማል።
የቤት መኪናዎች ፣ ሀገር አቋራጭ የጭነት መኪናዎች በመንግስት አዲሱ የድጎማ ስርአት የማይመለከታቸው እንደሆኑ እስካሁን ታውቋል።
በሌላ በኩል የነዳጅ ድጎማ የሚመለከታቸው እንደ ባጃጅ ፣ታክሲ ፣የህዝብ ትራንስፖርት እና የከተማ አውቶብስ የመሳሰሉ ተሽከርካሪዎች ከሀምሌ ወር ጀምሮ በአዲሱ የድጎማ ስርአት የሚታዩ የሚታቀፉ ይሆናሉ።
ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ እንደሰማችው የድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች በሀምሌ ወር ሙሉ ድጎማ እየተደረገላቸው የሚቀጥሉ ሲሆን ከሶስት ወር በኋላ ያለው አለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ በመመስረት የሚደረገው ድጎማ ወደ 75 በመቶ ዝቅ የሚል ይሆናል።
ቀጥሎም በየጥቂት ወራቱ ድጎማው ወደ 50 በመቶ እና 25 በመቶ ዝቅ እያለ ድጎማው የሚነሳ ይሆናል። አዲሱ የድጎማ ስርአት የሚመከታቸው ተሽከርካሪዎችን የመመዝገብና መለያ የመስጠት ስራም ተጀምሯል።
መንግስት “የታለመለት ድጎማ” በሚል በሰየመው አዲስ ስርአት ውስጥ ከጎረቤት ሀገራት ምርቶችን የሚያመላልሱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች አልተካተቱም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የፍጆታ ምርቶች በነዚህ ተሽከርካሪዎች እንደመጓጓዛቸው እንዲሁም እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከቤንዚን በላይ ድጎማ የሚጠይቀውን ናፍጣ እንደመጠቀማቸው የምርቶች ዋጋ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም።
አሁን ባለው አለም አቀፍ ዋጋ ያለ ድጎማ ናፍጣ ቢሸጥ አንዱ ሊትር 73 ብር እንደሚሆን መንግስት ሚያዝያ 29 ቀን 2014 አ.ም የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ለማድረግ ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል። አንድ ሊትር ናፍጣ 35 ብር አካባቢ ሲሸጥ የቆየውም በዚሁ ድጎማ ምክንያት ነው።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርአት ባለመኖሩ በመጀመርያው ዙር የድጎማ ስርአት ውስጥ ማስገባት አልተቻለም ፣ በቀጣይ ሊታይ ይችላል ብለውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]