ዋዜማ-የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አግዶት የቆየውን የማእድን ማውጣት ስራ ለማስጀመር የሚያስችል አዲስ መመሪያ አወጣ፡፡


ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተቋርጦ የነበረውን ማዕድን የማውጣት ስራ ዳግም ለማስጀመር የሚያስችል አዲስ መመሪያ የወጣ ሲሆን ከፕሬዝዳንቱ ቢሮ የወጣውና ዋዜማ የተመለከተችው ይኸው መመሪያ ከእገዳው በፊት ማለትም ከሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም በፊት ፍቃድ የያዙ የማእድን አውጪዎች ፍቃዳቸውን እንዲያድሱ፤ በማእድን አዋጅ ቁጥር 678/2002 እና በተሻሻለው ደንብ ቁጥር 32/2018 መሰረት የማእድን እና ንግድ አስተዳደር ማህበራት የሮያሊቲ ክፍያ እንዲከፍሉ እንዲሁም የከባባድ ማሽን ባለቤቶች ከማህበራቱ ጋር ውል እንዲያስሩ ያስገድዳል፡፡

ይኸው ውል በጊዜያዊ አስተዳደሩ የመሬትና ማእድን ቢሮ መጽደቅ አለበት ይላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ህጋዊ ፍቃድ ሊኖራቸው እንደሚገባ እና ግብር እንዲከፍሉም በመመሪያው ተካቷል፡፡


በፍቃድ እድሳትም ሆነ አዲስ ፍቃድ በማውጣት ሂደት ወቅት እያንዳንዱ ማእድን አውጪ የሚሰራበት ወረዳ እና ቀበሌ ጭምር ምርመራዎች እንደሚደረጉ የሚገልጸው መመሪያው፤ ከዚህ ቀደም ፍቃድ የነበራቸው ነገር ግን በህገ-ወጥ ማዕድን ማውጣት ስራ ላይ ሲሳተፉ በቆዩት አውጪዎች ላይ ምርመራ እንደሚደረግባቸውም ያስቀምጣል፡፡


በመፅደቅ ሂደት ላይ የነበሩ የማዕድንና የማምረቻ ፈቃዶች በትግራይ ማዕድን ቢሮ እስኪገመገሙ ድረስ ባለበት የሚቆይ ሲሆን፤ የማሽነሪ፣ የኬሚካል እና የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችም በመመሪያው መሰረት ፍቃድ ያገኛሉ ይላል።
የማእድን አውጪዎች ግብርና የሮያልቲ አስገዳጅ ክፍያዎችን የመክፈል፣ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወግድ፣ እና የማዕድን መሬቶችን መልሶ የማልማት ግዴታም በመመሪያው ይጣልባቸዋል።


ከዚህም በተጨማሪ የማእድንና ንግድ አስተዳደር ማህበራትን እንደ አርበኞች ማህበር ያሉ አደረጃጀቶች ያልተጓደለ የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ እንዳለባቸውና የሰነድ ጉድለት ከተገኘ ግን ማህበራቱ እንደሚሰረዙም በመመሪያው ተቀምጧል፡፡


በባህላዊ መንገድ የማእድን ቁፋሮ የሚያከናውኑ ማህበራት፤ በማሽን የታገዘ ቁፋሮ ከሚያከናውኑት አውጪዎች ጋር ውል አስረው መስራት እንደማይችሉም ይገልጻል፡፡


መመሪያው በትግራይ ክልል ወደ ማእድን ስራ ለመግባት የሚጠባበቁ የውጭ ሀገር የማዕድን አውጪ ተቋማትን በተመለከተ በልዩነት ያስቀመጠው ነገር ባይኖርም፤ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከክልሉ ማዕድን ቢሮ ፍቃድ ማግኘት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ [ዋዜማ]