Debretsion G. Mechael , Tigray regional gov deputy admin- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የትግራይ ክልል በተለይ በመቀሌ ከተማና በዙሪያዋ ለነባር ታጋዮች እና ለመንግስት ሰራተኞች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት መዝገባ መጀመሩን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ለነባር ታጋዮች ለመስጠት እየተዘጋጀ ያለው ቦታ 140 ካሬ ሜትር ሲሆን በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ክፍት ቦታዎች ለነኚሁ ነባር ታጋዮች ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከምንጮቿ አረጋግጣለች ፡፡


ለመንግስት ሰራተኛው ለመስጠት የታሰበው ቦታ 70 ካሬ ሜትር ሲሆን በአንጻራዊነት ከመሀል ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው አካባቢ ነው ተብሏል፡፡ መሬት ለመቀበል ፍላጎት ያላቸው አመልካቾች እየተመዘገቡ ሲሆን ቅድሚያ 48 ሺህ ብር በዝግ አካውንት ማስቀመጥ እንዳለባቸውም ተነግሯቸዋል፡፡ ይህ ገንዘብም አመልካቾቹ መሬቱን ከተረከቡና ግንበታ ከጀመሩ በኋላ ከደደቢት ማይክሮ ፋናንስ ተጨማሪ ብድር እንዲሰጣቸው መነሻ ይሆናል ተብሏል፡፡

የመሬት እደላው የክልሉ መንግስት በተለይ በመቀሌ ከተማ ባሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የቤት ኪራይና የመኖሪያ ቤት ዋጋን ለማረጋጋት እየወሰድኩት ያለሁት እርምጃ ነው ብሏል። ይሁንና ሕወሀት የድጋፍ መሰረቱን ለማስፋትና ሲቀርብበት የነበረውን ቅሬታ ለማርገብ የታለመ እርምጃ መሆኑን ያነጋገርናቸው የድርጅቱ አባላት ጭምር ይናገራሉ።

ከወራቶች በፊት በተመሳሳይ ለመንግስት ሰራተኞች የታደለው 70 ካሬ ሜትር ቦታ በከተማዋ 70 ካሬ በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ሰፈር እስከ መመስረት የደረሰ ነው፡፡ ነገር ግን መሬቱን የተቀበሉ አብዛኞቹ ሰዎች እጅግ በውድ ዋጋ መሬቱን መሸጣቸውን ከክልሉ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በመቀሌ በሀገሪቱ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ እንኳን ሊሸጥ በማይችልበት ዋጋ 70 ካሬ ሜትር ቦታ እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ኑሮውን በዛው በመቀሌ ከተማ ያደረገውና በመንግስት ስራ ላይ የተሰማራው ሌላው አስተያየት ሰጪ እንደሚለውም በዚህ ዋጋም የሚሸጥ መሬት ሲገኝ ቦታ ለመግዛት ያለው እሽቅድምድም በ15 አመት የከተማዋ ቆይታው አይቶት የማያውቀው እንግዳ ክስተት መሆኑን ይናገራል፡፡ በመቀሌ ከተማ አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱም ወደ አሳሳቢነት ደረጃ መድረሱንና እንደእርሱ ወርሃዊ ደሞዝተኛ ለሆኑ ነዋሪዎች ጫናው አስጨናቂ እየሆነ መምጣቱንም ነግሮናል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]