ዋዜማ- በትግራይና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተካረረ አለመግባባት መፈጠሩንና በራሳቸው በትግራይ ፖለቲካዊና  ወታደራዊ ቡድኖች መካከል የበረታ ክፍፍል መከሰቱን ተከትሎ ሕወሓት አዲስ ወታደራዊ አደረጃጀትንና የፖለቲካ አስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ ተገንዝባለች።

ከተደረጉት አዳዲስ አደረጃጀቶች መካከል የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች (TDF) የተደራጁበት የዕዝ ሰንሰለት ይገኝበታል። አዲሱ አወቃቀር ሕወሓት በማናቸውም መንገድ በክልሉ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ እንዲሆን የሚያስችለው መሆኑንም ምንጮቻችን ነግረውናል። ዝርዝሩን አንብቡት 

በሰሜኑ የኢትዮጲያ ክፍል የሰነበተ የጦርነት ስጋት አለ። ይህንኑ የጦርነት ዳመና ተከትሎ በርካታ መዋቅራዊ ለውጦችን እያደረገ እንደሆነ የሚነገርለት የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች (TDF)፤ በተለይም ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የታችኛውን እርከን ያማከለ መዋቅራዊ ለውጥ፤ የከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ሽግሽግ እና የሰራዊት ድልድል ስራዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ ይህ ሽግሽግ ሰራዊቱን ከፖለቲካዊ ሽኩቻ አውጥቶ ወደ አንድ ማዕከላዊ ዕዝ ወይም ‹‹ሴንትራል ኮማንድ›› ለማምጣት ያለመ ቢሆንም፤ በውስጡ ግን አሁንም ከፍተኛ ውጥረትና የአሰላለፍ ለውጦችን እያስተናገደ ስለመሆኑ ዋዜማ ከሰራዊቱ የአሁን እና የቀድሞ አባላት ሰምታለች፡፡

የትግራይ ኃይል በ2013 ዓ.ም በፌደራሉ መንግስት እና በህወሃት መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የተመሰረተ ሲሆን፤ ከመደበኛ ሰራዊትነት ይልቅ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ፤ ማለትም የትግራይ ተወላጅ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ከጦርነቱ በፊት የነበረው የክልሉ ልዩ ሃይል እና የፖሊስ አባላት፤ ሚሊሻዎችን እንዲሁም ተማሪዎች እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሰልጣኝ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን ያቀፈ ነው፡፡ በዚሁ ወታደራዊ ሃይል ውስጥ፤ በተለይም ህወሃት የደርግን ስርአት ለመጣል ባደረገው የ 17 አመታት ትግል ወቅት ተሳትፎ የነበራቸው የትግራይ ተወላጅ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሰራዊቱ ‹‹የጀርባ አጥንት›› ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡ 

የአርሚዎች ስምሪት እና ስልታዊ ቦታዎች

ሰራዊቱ 4 ግንባሮች እና በቁጥር የሚታወቁ 12 ክፍለ ጦሮች አሉት፡፡ ምንም እንኳን ወታደራዊ ሚስጥርን ለመጠበቅ ሲባል ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይደረግም፤ በቁጥር የሚታወቁት አርሚዎች 12ቱ ናቸው፡፡
 
የሰሜን ግንባር በስሩ መቀመጫውን ዓዲግራት ያደረገው አርሚ 15፣ በክልሉ ምስራቃዊ ዞን ሰፍሮ የሚገኘው አርሚ 10፣ በኢሮብ፣ አድዋ፣ አክሱም እና ባድመ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱት አርሚ 11, 13 እና 17 የያዘ ነው፡፡

የደቡብ ግንባር በስሩ በማይጨው እና መኾኒ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው አርሚ 20 ልዩ ስሙ ‹‹አንበሳ›› እንዲሁም በኮረም እና አላማጣ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱት አርሚ 21 እና 23ን የያዘ ነው፡፡


የምዕራብ ግንባርም ባለፈው አመት መጨረሻ የተቃውሞ ድምጽ ያሰማው እና በጸለምት፣ ሁመራ እና ማይጸብሪ ድንበር አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውን አርሚ 31 በስሩ ይዟል፡፡ በወልቃይት እና ሱዳን ድንበር መተላለፊያዎች የሚንቀሳቀሱት አርሚ 33 እና 35ም በዚሁ ግንባር ስር ናቸው፡፡
 
አርሚ 91 ወይም ሜካናይዝድ ተብሎ የሚጠራው ከባድ መሳሪያዎችን የታጠቀው ክፍለ ጦርም በጀነራል ገብረመድህን (ድንኩል) ሲመራ የቆየ ሲሆን በመቀለ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ኩሓ›› አካባቢ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
አርሚ 09 ወይም ኮማንዶ ክፍለ ጦርም በመዲናዋ መቐለ ቁልፍ ስፍራዎችን የሚጠብቅ ሃይል ነው፡፡  

አርሚ 70 በመባል የሚጠራውና በጦርነቱ ወቅት ከሰራዊቱ ተገንጥሎ በሱዳን የቀረው ሃይል  በሱዳን ድንበር ‹‹በሐምዳይት›› በኩል የሚገኝ ተንቀሳቃሽ ኃይል ነው። ይህ ሃይል ከሱዳን ወታደራዊ ድጋፍ ከማግኘት ባሻገር በሱዳን ጦር ሃይል እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ የሱዳንን ጦር ደግፎ እየተሳተፈ እንደሆነ የሚገልጹ ተደጋጋሚ ክሶች ይቀርቡበታል፡፡

በጎ ፈቃደኛና ሚሊሻውን ወደ ማዕከላዊ ጦር አደረጃጀት

ወታደራዊ ሃይሉ በ4 ግንባሮች የተከፋፈለ ሲሆን ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምእራብ እና ምስራቅ ግንባር በመባል ይጠራሉ፡፡ አራቱ ግንባሮች በስራቸው 12 ክፍለ ጦሮች (አርሚ) አሏቸው፡፡ 

በዚህ ረገድ ጄነራል ኃይለሥላሴ ግርማይ (ወዲ እምበይተይ) የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ሁሉንም ክፍለ ጦሮች የሚያስተባብሩ ሲሆን፤ብርጋዴር ጄነራል ምግበይ ኃይለ የምዕራብ ግንባር ዋና አዛዥ፣ ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ (ጆን መዲድ)  የደቡብ ግንባር አዛዥ እንዲሁም የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ (ማንጁስ) የሰሜኑን ግንባር ይመራሉ፡፡  

ሰራዊቱ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ የግንባር እና የክፍለ ጦር አዛዦች የስልጣን ሽግሽግ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ሰራዊቱን ከመደበኛ ተዋጊነት አውድ አውጥቶ ወጥነት ያለው ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በአሁኑ ወቅትም፤ የግንባር አዛዦች በጦርነቱ ወቅት እንደነበረው በአንድ ማእከላዊ ስርአት ወይም ሴንትራል ኮማንድ ስር እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ እንደሆነ የሚገልጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የሰራዊት አባላት፤ ከዚህ ቀደም በምስራቅ ግንባር አርሚ 3 ዋና አዛዥ የነበሩት እና የሰራዊቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ሃላፊ ጀነራል ሃይለስላሴ ግርማይ (ወዲ እምበይተይ) የሰራዊቱን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በበላይነት እንደሚመሩ ገልጸዋል፡፡ ይኸው ‹‹ሴንትራል ኮማንድ›› የሚመራው ግን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱ ወቅት የሰሜን ግንባር አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ማሾ በየነ ባሉበት ሃላፊነት መቀጠላቸውን እና በጦርነቱ ወቅት የምስራቅ ግንባር አዛዥ በመሆን ሲመሩ የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ (ድንኩል) ወደ ምእራብ ግንባር መዛወራቸውን ነግረውናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምእራብ ግንባር ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ምግበይ ሃይለ፤ የሰራዊቱን አጠቃላይ የሥልጠናና የሪፎርም ኃላፊነት ደርበው ይዘዋል። 

በሪፎርሙ መሠረት፣ በየግንባሩ ያሉ ክፍለ ጦሮች (አርሚዎች) ያለ ማዕከላዊ ዕዝ (Central Command) ትዕዛዝ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ጥብቅ ክልከላ ተጥሏል፡፡ ቀደም ሲል በፈቃደኝነት ይዋጋ የነበረው ሰራዊት፤ አሁን በመደበኛነት የመንግሥት ደመወዝተኛ እንዲሆን በሚል አዲስ የፋይናንስ መዋቅር መዘርጋቱን ፕሬዚደንቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

ሕወሓት እንደ ‹‹መኸተ ካውንስል››

ይህ ካውንስል በቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተቋቁሞ የነበረውን እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተውን ጊዜያዊ ምክር ቤት በማፍረስ በ2018 ዓ.ም የተቋቋመ ነው፡፡ በክልሉ የተፈጠረውን ፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ የተመሰረተው ይኸው ካውንስል፤ የህወሃት የስራ አስፈጻሚ እና ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን፤ የግንባር አዛዦች እና ለህወሃት ‹‹ታማኝ ናቸው›› የተባሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ያካተተ ሲሆን፤ የካውንስሉ ሊቀ-መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መሆናቸውን ለክልሉ መንግስት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በካውንስሉ ውስጥ በምክትልነት ሃላፊነት ይመራሉ፡፡

በክልሉ ውስጥ የሚሰጡ ማናቸውም ፖለቲካዊም ሆኑ ወታደራዊ ውሳኔዎች በዚህ ካውንስል እንደሚያልፉ ጠቅሰው፤ ይኸው የወታደራዊ አመራሮች ሽግሽግም የካውንስሉ ውሳኔ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ የካውንስሉ ዋነኛ አላማ የህወሃትን ስርአት እንዲሁም የፖለቲካ የበላይነት ማስቀጠል እንደሆነ ያብራሩት የዋዜማ ምንጮች፤ ካውንስሉ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ በላይ ሆኖ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል፡፡

የከፍተኛ መኮንኖች ክፍፍል

ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንዲሁም አቶ ጌታቸው ረዳ በሚመሯቸው የህወሃት ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ በሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች መካከልም በተመሳሳይ  ልዩነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም፤ በነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም አርሚ 15ን በማንቀሳቀስና ዲሽቃ የጫኑ ከባድ ተሸከርካሪዎችና መሳሪያዎችን ይዘው የጊዜያዊ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በመክበባቸው ‹‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለማድረግ አሲረዋል›› በሚል የተከሰሱት ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ ገብረ እና ስርአቱን እንደሚቃወሙት በይፋ የገለጹት ጀነራል ተክላይ አሸብር (ወዲ አሸብር) ራሳቸውን ከጦሩ ማግለላቸው ይታወሳል፡፡

‹‹ከኮር በላይ›› የተባሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በጥር ወር ፤ 2017 ዓ.ም ባደረጉት ስብሰባ ያሳለፉትን ከህወሃት ጎን የመሰለፍ ውሳኔ በመቃወም ራሳቸውን ያገለሉት ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና ጀነራል ገብረእግዚያብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ)ም በተፈጠረው ልዩነት ሳቢያ በአፋር የሚንቀሳቀስ የራሳቸውን ታጣቂ ሃይል መመስረታቸው አይዘነጋም፡፡

ለሂደቱ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደነገሩን በተዋጊ ሀይሉ ፣በፓለቲካ አደረጃጀቱና በሕወሓት መካከል የተወሰነ የመደራረብም የመጣረስም ዝንባሌ ያለው ይህ አወቃቀር ሕወሓት የተሻለ ቁጥጥርና የመሪነት ሚና እንዲኖረው የሚያደርግ ሲሆን በክልሉ የተፈጠረውን የስልጣን ሽኩቻ በማስፋት በኩል አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።[ዋዜማ]