ዋዜማ- በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ “ሹም ተምቤን” የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ ምዝገባ ፍቃድ በማግኘት በምስረታ ሂደት ላይ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች፡፡
“ሹም ተምቤን ፓርቲ” ከምርጫ ቦርድ የምስረታ ፍቃድ ያገኘው ሐምሌ 23፣ 2017 ዓ፣ም እንደነበር ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች፡፡
የቀድሞው የሕወሓት አመራሮችን ካካተተው ከእነ ጌታቸው ረዳ ቡድን የተነጠሉ ግለሰቦች ያቋቋሙት እና የሕወሓት ተቃዋሚ መሆኑን የገለጠ “ውድብ ወለዶ ትግራይ” ወይም የትግራይ ትውልድ የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲም፣ መስከረም 10፣ 2018 ዓ፣ም በመቀሌ ከተማ ባካሄደው ጉባኤ በይፋ እንደተመሠረተ የሚታወስ ነው።
በሕወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ፣ የእነ ጌታቸው ረዳ ቡድን ከመሠረተው ስምረት ፓርቲ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ለመንቀሳቀስ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የክልላዊ ፓርቲነት ቅድመ ምዝገባ ፍቃድ ወይም የምዝገባ ፍቃድ ያገኙ ፓርቲዎች ብዛት ሦስት ደርሷል።
እነ ጌታቸው ረዳ እና አጋሮቻቸው የመሰረቱት ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲም፣ የመስራች ጉባኤውን በአዲስ አበባ ዓርብ፣ ጥቅምት 14፣ 2018 ዓ፣ም ጀምሮ እያካሄደ ነው። ጉባኤው ማምሻውን ጌታቸው ረዳን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫም አካሂዷል። የፓርቲው መስራች ጉባኤ፣ እስከ ቅዳሜ፣ ጥቅምት 15 ድረስ እንደሚቀጥል ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 18፣ 2017 ዓ፣ም ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ ያገኘው ስምረት ፓርቲ፣ በትግራይ ያለውን ያልተረጋጋ የጸጥታ ሁኔታ በመጥቀስ ነሐሴ 17፣ 2017 ዓ፣ም በመቀሌ ከተማ ሊያካሂድ የነበረውን መስራች ጉባኤ መሰረዙ ይታወሳል፡፡
ፓርቲው በመቀሌ በከፈተው ዋና ቢሮው ላይ የታጠቁ አካላት በሐምሌ፣ 2017 ዓ፣ም ጥቃት እንደፈጸሙበት ከገለጠ በኋላ፣ ፓርቲው በትግራይ መስራች ጉባኤውን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ በመግለጽ ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ አቅርቦ ነበር። ስምረት ፓርቲ ይህንኑ መስራች ጉባኤውን ማካሄድ የጀመረው፣ መስራች አባላቱን ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ በመጥራት መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች፡፡
ሆኖም በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁሉም የፓርቲው አባላት በዚህ መስራች ጉባኤ ላይ መሳተፍ አለመሳተፋቸውን ዋዜማ ለጊዜው ማረጋገጥ አልቻለችም።
በዚሁ የስምረት ፓርቲ መስራች ጉባኤ ላይ ከ200 በላይ የምስረታ ፈራሚዎች መሳተፋቸው የተገለጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ የጉባዔው ተሳታፊዎች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የፓርቲው አባላትም ይገኙበታል ተብሏል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ መሰረት፣ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ አራት ሺህ መስራች አባላት እንዳሉት ማስረጃ ማቅረብ ያለበት ሲሆን፣ ከአጠቃላይ መስራች አባላቱ መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑትም ፓርቲው በሚንቀሳቀስበት ክልል መደበኛ ነዋሪዎች መሆን አለባቸው።
አብዛኞቹ የስምረት ፓርቲ ጥንስስ መስራቾች በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሕጋዊ የፖለቲካ ሰውነቱን ያጣው ሕወሓት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡ ከፓርቲው መሥራቾች መካከል፣ ቀደም ሲል የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዱሁም አሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑትን ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተወሰኑት በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን ተሰጥቷቸው በአዲስ አበባ ሰንበትበት ብለዋል፡፡
ጌታቸው ከሕወሓት ከተነጠሉ ጓዶቻቸው ጋር ስምረት ፓርቲን የመሰረቱት፣ ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የሕወሃት ቡድን በተራዘመ የአስተዳደር ግልበጣ ሴራ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳነት መንበራቸው እንዲለቁ ግፊት እንደተደረገባቸው በመግለጽ ወደ አዲስ አበባ ከሸሹ በኋላ እንደነበር አይዘነጋም።
የትግራይ ጸጥታ ኃይል፣ ስምረት ፓርቲ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሰውን የትግራይ ታጣቂ ቡድን ይመራል በማለት ካሁን ቀደም መወንጀሉ አይዘነጋም። ስምረት በበኩሉ፣ አመራር የሚሰጠው አንድም ታጣቂ ቡድን በስሩ እንደሌለ ገልጦ፣ በወቅቱ ውንጀላውን አስተባብሏል። በምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሠረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስራቸው ታጣቂ ቡድን የማደራጀትም ሆነ ለየትኛውም ታጣቂ ቡድን ድጋፍ ማድረግ አይችሉም። [ዋዜማ]
