ዋዜማ- ራሳቸውን ከሀገር አቀፉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የነጠሉት የትግራይ የሀይማኖት አባቶች ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማነጋገር ወደ አዲስ አበባ ሊመጡ መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ራሳቸውን “መንበረ ሠላማ” ብለው የሚጠሩትና በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ተከትሎ ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ተነጥለው የራሳቸውን ሲኖዶስ ሰይመናል ያሉት የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትና አባቶች፣ አንድ ልዑክ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሊልኩ መሆኑን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ጳጳሳት ተናግረዋል።

ልዑካኑን ካወቀሩት እና ከመንበረ ሰላማ አባቶች መካከል የሆኑት አባ አረጋዊ የተባሉ አባት፣ ልዑኩ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በወቅታዊው ጉዳዮች ዙሪያ ይወያያል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ለዋዜማ ነግረዋታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ በትግራይ ድጋሚ እያንዣበበ ስላለው የጦርነት ዐውድ በማንሳት፣ በክልሉ ድጋሚ ጦርነት ከተቀሰቀሰ እንደ ከዚህ ቀደሙ ቀላል እንደማይሆንና የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

ዐቢይ አክለውም፣ በክልሉ ድጋሚ ጦርነት እንዳይካሄድ ለማስቀረት የሐይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የክልሉ ተወላጆች የጦርነት ነጋሪት ሰባኪ የሆኑ አካላትን በመምከር የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም። ይህንኑ ተከትሎ፣ በክልሉ የሚገኙት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችና የ”መንበረ ሠላማው” አባላት በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ መቀሌ ውስጥ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውንና በጽሁፍ መግለጫ ማውጣታቸውን አባ አረጋዊ ለዋዜማ ገልጸዋል።

በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሃይማኖት አባቶቹ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ የሚወያይ ልዑክ ሰይመው ወደ አዲስ አበባ ሊልኩ መሆኑን መግለጣቸውን አባ አረጋዊ ለዋዜማ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ የሰጡት አስተያየት የትግራይን ሕዝብ ለአዲስ ጠፋት ሊያጋልጥ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ አባቶቹ ለዋዜማ በላኩት የጽሁፍ መግለጫቸው ላይ ሠፍሯል።

የሃይማኖት አባቶቹ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተያየት በትግራይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደማያንጸባርቅ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና አጋሮቹ ባለፉት አምስት ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ ባደረሱት ወታደራዊ ጥቃትና ኢኮኖሚያዊ በደል ሳቢያ ሕዝቡ በከፍተኛ ስቃይ እና መከራ ውስጥ እንደሚገኝ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው ያለው የሃይማኖት አባቶቹ መግለጫ፣ በየፕሪቶሪያ የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት ምንም እንኳ በትግራይ የተኩስ ድምጽን ቢያስቀረም፣ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩ በተለይ ከቀያቸው የተፈናቀሉ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ወደ መኖሪያቸው ባለመመለሳቸው በሞትና በስቃይ መካከል ይገኛሉ በማለት የችግሩን ጥልቀት አብራርቷል።

ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የትግራይን እውነተኛ ምስል እና የትግራይ ህዝብ ምኞት ዘላቂ ሰላም መሆኑን ለጠቅላይ ሚንስትሩ የሚያስረዳ ልዐካን ቡድን ለመላክ መወሰናቸው ተገልጧል።

አባቶቹ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ወክለው የሚላኩትን ሽማግሌዎች በክብር ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ እምነታቸው የጸና መሆኑንም ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ፣ በክልሉ ለሰላም የሁለት ቀናት ጾምና ጸሎት እንዲደረግም ጥሪ አድርገዋል። በትግራይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶችና ጳጳሳት አቡነ ማትያስ ከሚመሩት ዋናው ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጥለው “መንበረ ሠላማ” የተባለውን ሲኖዶስ በተናጥል ያቋቋሙት፣ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ሕዝብ ላይ መዓት ሲወርድና በቤተክርስቲያናት ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አጋርነቱን ማሳየት አልቻለም በማለት ነበር።

ትግራይ የሚገኙ አባቶች የቤተክርስቲያኗን ቀኖናዎችና ሕግጋት በጣሰ መልኩ በተናጥል ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን ያወገዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በክልሉ የሚገኙት አባቶች ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸውና ወደ ሲኖዶሱ እንዱመለሱ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ችግሩ አልተፈታም። [ዋዜማ]