• የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ገደብ ሁለት ሳምንታት ቀርተውታል።

ዋዜማ- አምስት ያህል የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የትጥቅ ትግል የጀመሩ አማፅያንና የቀድሞ የመከላከያ ወታደራዊ መኮንኖች የታቀፉበት አዲስ ምክር ቤት በቀጣዮቹ ቀናት ምስረታውን ይፋ እንደሚያደርግና የትግራይ ክልልን አስተዳደር ለመረከብ ራሱን እያዘጋጀ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ካሰባሰበችው መረጃ ተገንዝባለች። 

የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም እና በቅርቡም በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ በነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ምክትል ፕሬዚደንትና የዲሞክራታይዜሽን ዘርፍ ሃላፊ የነበሩት ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ፤ ባለፈው አመት ሐምሌ ወር መጨረሻ 4 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁለት ነባር ወታደራዊ አመራሮችን ያቀፈ ስብስብ መፍጠራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ጀነራሉ የሚመሩት ‹‹የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ›› የተሰኘው ስብስብ አረና ትግራይ፣ ባይቶና፣ ውናት እና ስምረት ፓርቲዎችን ያካተተ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ወታደራዊ አመራሮቹም፤ ራሳቸው ጀነራል ጻድቃን እና ጀነራል ተክላይ አሸብር (ወዲ አሸብር) መሆናቸውንም በወቅቱ ተናግረዋል፡፡

ይኸው ስብስብ በውስጡ የታቀፉት አባል ፓርቲዎች ላይ ለውጥ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ስምረት፣ ባይቶና፣ ዓረና ትግራይ፣ ትንሳኤ 70 እንደርታ እና ቃንጪ ሓቂ የተባሉትን 5 የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች፡፡

በተለይም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ የስልጣን ጊዜ የሁለት ሳምንታት እድሜ የቀረው መሆኑን ተከትሎም ፤ ራሱን ከትግራይ ሃይሎች የነጠለው እና በአፋር የሚንቀሳቀሰው የ‹‹ሓራ መሬት›› ወይም የትግራይ ሰላም ሃይል በመባል የሚጠራው ታጣቂ የስብስቡ ወታደራዊ ክንፍ እንዲሆን ከስምምነት መደረሱንም ዋዜማ ከስብስቡ አባል ፓርቲ ሃላፊዎች ለማረጋገጥ ችላለች፡፡

አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለየብቻ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በክልሉ ውስጥ ያለውን ስርአት ለማስወገድ ብቸኛው አማራጭ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ እንደሆነም ነው ብለው እንደሚያምኑ ሃላፊዎቹ ይናገራሉ።

ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ፣ ብርጋዴር ጀነራል ገብረእግዚአብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ)፣ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ)፣ ኢንጅነር አሰፋ አብርሃ እና ጀነራል ተክላይ አሸብር (ወዲ አሸብር) በተመሳሳይ መልኩ በየፊናቸው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት ሃላፊዎቹ፤ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ክንፉን በማጠናከር ወደ ትግራይ መግባት እና ስርአቱን ማስወገድ ዋነኛ አላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ 

የህወሃት አመራሮች ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው ያሉ ሲሆን፤ ‹‹ይህ እንዲሆን አንፈቅድም›› ብለዋል፡፡

ቀጣዩን የጊዜያዊ አስተዳደርነት ቦታ በመቆናጠጥ ክልሉን የማስተዳደር ጥረት መጀመሩን፤ ይህንን ለማሳካትም መንግስታዊ ቅርጽ ያለው ምክር ቤት እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡ 

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት የስልጣን ጊዜ ከማብቃቱ በፊት በቅርቡ በአዲስ አበባ ይፋ እንደሚደረግ እና ለስራ ማስኬጃ እንዲሁም ለሰራዊት የሚሆኑ ገቢ የማሰባሰብ ስራዎች እለመጀመር እቅድ መኖሩንም ተረድተናል።

በፌደራሉ መንግስት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ ይኖር እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ 

በ2016 ዓ.ም አጋማሽ በህወሃት ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ በርካታ የክልሉ የቀድሞ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ከሕወሓት መደበኛ መዋቅር በመውጣት የራሳቸውን የፖለቲካ ስብስቦች እያጠናከሩ ይገኛሉ፡፡ [ዋዜማ]