ዋዜማ- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የተቀዋሚ ፓርቲ ተወካዩ ዮሐንስ ተሠማ ያለመከሰስ መብታቸው በተነሰባት ክስ ዋስትና ተፈቀደላቸው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ባጸደቀው አወዛጋቢ የሕገመንግሥት ማሻሻያ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በማሻሻያው ላይ የሕገመንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጥ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ የታሰሩት ዮሐንስ ተሠማ፣ በዋስ እንዲፈቱ የክልሉ ፍርድ ቤት መወሰኑን ዋዜማ ሠምታለች።

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ቦዴፓ) ተመራጭ የሆኑት ዮሃንስ ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቤተታ ያቀረቡት፣ ከሌሎች ሁለት የፓርቲው አባላት ከሆኑ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን ነበር። የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓርብ፣ መስከረም 23፣ 2018 ዓ፣ም ባዋለው ችሎት፣ ዮሐንስ በ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ውሳኔ ማሳለፉን የዮሃንስ ባልደረቦች ለዋዜማ ገልጠዋል፡፡

የክልሉን ሕገመንግሥት ማሻሻያ በመቃወም የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄ ያቀረቡት ዮሐንስ፣ ያለመከሰስ መብታቸውን ባጡበት ክስ የመጀመሪያው ዋስትና የተፈቀደላቸው፣ ከታሰሩ ከሰባት ወራት በኋላ ነው፡፡ ፖሊስ የሕዝብ ተወካዩን ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ያሰራቸው፣ “የክልሉን ሕገ መንግሥት ለመናድ በመንቀሳቀስ” እና “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር” ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት ነበር።

ፍርድ ቤቱ ለዮሃንስ የዋስትና መብት የሰጣቸው፣ ተከሳሹን በተደራራቢ ወንጀሎች የጠረጠራቸው አቃቤ ሕግ ግለሰቡ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በቂ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም በማለት እንደሆነ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ዓርብ’ለት ባዋለው ችሎት፣ የክስ መዝገባቸው በ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲዘጋ ውሳኔ መስጠቱን ባለደረቦቻቸው ነግረውናል፡፡ ምንም እንኳ የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ መዝገቡ እንዲዘጋ ቢወስንም፣ ዮሐንስ በሌላ ወንጀል የእስር ፍርድ ስለተፈረደባቸው ከእስር መውጣት አልቻሉም ተብሏል፡፡

ዮሃንስ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ በኋላ፣ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ የቆየ ሌላ የክስ መዝገብ በድጋሚ ቀስቅሶ፣ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ አምስት ዓመት ከ10 ወር እስራት እንዳስፈረደባቸው ይታወሳል፡፡ ዮሐንስ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ከታሰሩ በኋላ፣ ከአምስት ዓመት በፊት በተቋረጠ ክስ የተፈረደባቸው፣ ከከተማ መሬት ሊዝ ጋር በተያያዘ ፈጽመውታል ባለው ወንጀል ነው፡፡

የክስ ዝርዝር ይዘቱ የሚመለከተው፣ ዮሃንስ የመንግሥት አካል ፈቃድ ሳያገኙ በአሶሳ ከተማ 328 ካሬ ሜትር የመንግሥት ባዶ ቦታ ይዘዋል የሚል ነበር። ዮሐንስ ከተቋረጠ በኋላ ተቀስቅሶ አመስት ዓመት በተላለፈባቸው ፍርድ ላይ ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ መጠየቃቸውን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ያለመከሰስ መብታቸው በተነሳበት ክስ የዋስትና መብት ማግኘታቸው፣ የእስር ቅጣት በተፈረደባቸው ሌላኛው ክስ ላይ ስለሚኖረው አንደምታ የሕግ አግባቦችን እየፈተሹ መሆኑን ባለደረቦቻቸው ተናግረዋል፡፡ በአዋጅ ቁጠር 203/2017 የጸደው የክልሉ የሕገመንግሥት ማሻሻያ፣ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ወንበር ብዛት ከ99 ወደ 165 ከፍ ማሳደጉን ተከትሎ፣ የፍትሐዊነት ጥያቄ ቀርቦበት ጉዳዩ በፌደራሉ የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ ተይዟል፡፡

የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባኤ ገና በአቤቱታው ላይ ውሳኔ ያልተሰጠ ቢሆንም፣ የክልሉ ምክር ቤት ግን ከኹለት ወር ገደማ በፊት በማሻሻያው ላይ የተነሱ ስጋቶችን ለመመለስ በሚል ዳግም ማሻሻያ ማድረጉን እና ሆኖም የክልሉ ምክር የድጋሚ ማሻሻያ በትክክል ዝርዝሩ ምን እንደሆነ ሳይገለጽ በድምጽ ብልጫ እንዲጸድቅ ተደርጓል በማለት የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካዮች ቅሬታቸውን መግለጣቸውን ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል። [ዋዜማ]