PHOTO- REUTERS/Tiksa Negeri

ዋዜማ ራዲዮ-የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሰራተኞቹን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ አዲስ አደረጃጀት እያዘጋጀ ነው። በስራቸው ያለመቀጠል ስጋት ያደረባቸው ሰራተኞቹ ለተቃውሞ እየተዘጋጁ ነው።

የመከላከያ ምርቶችን ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች ተለይቶ ዘጠኝ ፈብሪካዎችን በስሩ ይዞ የተደራጀው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በስሩ ዘጠኝ ሺህ የሚሆኑ ሰራተኞችን አቅፎ ይዟል። ሆኖም ኮርፖሬሽኑ አዲስ ያወጣው የሰራተኛ ፍላጎት መዋቅር ብዙዎችን ከስራ ገበታ የሚያፈናቅል ነው የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።

ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው በኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ለኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር የገባ የቅሬታ ደብዳቤ አዲሱ የኮርፖሬሽኑ የሰራተኛ ፍላጎት መዋቅር ፣ የሰራተኛውን ጥቅምና መብትን የማያስከብር ፣ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ፣ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁን ያልተከተለ እንዲሁም መነሻውና ግቡ ግልጽ ያልሆነ ነው በሚል ትችት ያቀርባል። የሰራተኞቹ ደብዳቤ በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ቀድሞ በነበሩ አመራሮች ስግብግብነት የተበዘበዘ እንዲሁም መጣ በተባለው ለውጥ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም አሁን የተዘጋጀው መዋቅር እንዳሳዘናቸው ይገልጻል። ይህም ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ችግር ውስጥ ወድቃ ነባር ሰራተኞችን እንደገና ፈትኖ ለመቅጠር ያቀደው እቅድ ተገቢ እንዳይደለም ያብራራል። የኮርፖሬሽኑ ችግርና ለኪሳራ ሲዳርገው የቆየው አሁን ያለው የሰራተኛ ብዛት ሳይሆን የአመራር ድክመት በመሆኑ አካሄዱ እንዲስተካከልም ሰራተኞች በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።


የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ያዘጋጀው የሰራተኛ ፍላጎት መዋቅር ለዋና መስሪያ ቤቱ እና በስሩ ላሉ ዘጠኝ ፋብሪካዎች ለእያንዳንዳቸው በተናጠል የሰራተኛ ፍላጎት መዋቅር አስጠንቷል። ዋዜማ ራዲዮ የተወሰኑት የኮርፖሬሽኑን የሰራተኛ ፍላጎት መዋቅር ጥናቶችን ተመልክታለች። ለአብነትም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት የተሰራው ባለ 85 ገጽ የሜቴክ ዋና መስሪያ ቤት የተጠናቀቀ የሰራተኛ ፍላጎት መዋቅር የተጠናቀቀ ሪፖርት ፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና መስሪያ ቤት አሁን ላይ ያሉ የሰራተኞች ብዛት 803 ሲሆን በአዲሱ መዋቅር መሰረት ግን ለሜቴክ ዋና መስሪያ ቤት የሚያስፈልገው ሰራተኛ 412 ብቻ መሆኑን ያነሳል። በጥናቱ ትርፍ ሆነው የተገኙት 391 የዋናው መስሪያ ቤት ሰራተኞች ላይ መንግስት ውሳኔን እንዲያሳልፍ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።

የመዋቅር ጥናቱ የስራ ሂደት መንዛዛትን መቀነስና ውጤታማነት ማምጣትን ለዚህ መነሻነት አቅርቧል። የኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት የሰው ሀይል ክፍል 51 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በአዲሱ መዋቅር የሚፈለገው 12 ብቻ መሆኑን ስነዱ ያትታል። በፋይናንስ ዘርፍ ደግሞ 117 ሰዎች በስራ ላይ ያሉ ሲሆን የሚፈለገው ግን 27 ብቻ ነው ይላል አዲሱ መዋቅር። በፕሮጀክት እቅድና ክትትል ክፍል ስርም አሁን ላይ 62 ሰዎች በስራ ላይ ሲሆኑ አዲሱ መዋቅር ግን 13 ሰራተኛ ብቻ ነው የሚፈልገው ።

በኮርፖሬሽኑ ስር ያሉ የዘጠኝ ፋብሪካ ሰራተኞችም ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እንደሚገጥማቸው ሰምተናል። አሁን ላይ በኮርፖሬሽኑ ስር ያሉ አዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ፣ፓወር ኢኪውፕመንት ማምረቻ ፣ ቢሸፍቱ አውቶሞቲቭ ፣ አቃቂ ቤዚክ ሜታል ፣የብረታ ብረት ፋብሪኬሽንን ጨምሮ የዘጠኝ የኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎች ሰራተኞች በግማሽና ከግማሽ በላይ በአዲሱ መዋቅር ከስራ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

ቢሸፍቱ አውቶ ሞቲቭ ፋብሪካ አሁን ላይ ሶስት ሺህ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በአዲሱ የሰራተኞች አደረጃጀት የሚያስፈልገው አንድ ሺህ ብቻ በመሆኑ ሁለት ሺህ ሰራተኞቹ ከመዋቅሩ ውጭ ይሆናሉ።

ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘውና ለኮንስትራክሽን እና የብረታ ብረት ምርቶች ማምረቻ የሚያገለግሉ ማሽኖች የሚሰሩበት የብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ውስጥ ያሉ ማሽኖች የፋብሪካው ግቢ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መኪኖች ጋራጅነት ይፈለጋል በሚል በሙሉ ተነቃቅለው ተወስደዋል። ማሽኖቹም ወዴት እንደተወሰዱ አይታወቅም። በፋብሪካው ውስጥ ያሉ ሰራተኞች እስካሁን ደሞዝ የሚከፈላቸው ይሁን እንጂ የተጠናቀቀው አዲሱ መዋቅር ሲተገበር ከስራ ውጭ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው ። አቃቂ ያለው ቤዚክ ሜታል ፋብሪካም ለወራት ብዙ ሰራተኞችን ከስራ ውጭ አድርጎ ደሞዝ እየከፈለ የቀየ ሲሆን አዲሱ መዋቅር ተግባራዊ ሲሆን እጣ ፈንታቸው ይለያል ተብሏል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከሰራተኞች አንጻር የደረሰበት ወሳኔ ብዙ ቅሬታዎችን ያስነሳው የሰራተኛ ቁጥር በመቀነሱ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ነው። በብዙ ፋብሪካዎቹ እና በዋና መስሪያ ቤቱ የሚቀነሰውን ቀንሶ የሚቀረውን ለማስቀረት የትምህርት ዝግጅቶችን መስፈርት እንደለየ እና ፈተና እንደሚፈትንም ገልጿል። ሆኖም በፋብሪካዎችም ሆነ በዋና መስሪያ ቤት ብዙዎች የሌላቸው የትምህርት ዝግጅት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ እና ረጅም አመት የስራ ልምዶች መስፈርት እንዲሆኑ መካተታቸውን ተረድተናል።

በሌላ በኩል ከሜቴክ ዋና መስሪያ ቤት ውጭ ላሉት የፋብሪካ ሰራተኞች የጽሁፍ : የተግባርና የቃል ፈተና እንደሚዘጋጅም ሰምተናል። የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች እንደ ትምህርት ዝግጅታቸውና የስራ ልምዳቸው እስከ ፊታችን ሰኔ 4 ድረስ በየዘርፎቻቸው ከሚቀርቡላቸው ሶስት የስራ መደብ አማራጮች በአንዱ ላይ አመልክተው ለፈተና እንዲዘጋጁ ተነግሯቸዋል። ከሚቀርቡላቸው ሶስት የስራ መደብ አማራጮች ውስጥ የትምህርት ዝግጅታቸውም ሆነ የስራ ልምዳቸው የማይዛመድ ከሆነም ከስራ መገለል ይጠብቃቸዋል። ሆኖም የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች በተቆረጠላቸው ቀን የስራ መደብ ምርጫም ሆነ ለፈተና እንደማይቀመጡ እየገለጹ መሆኑን መረዳት ችለናል። ተቃውቸሟቸውን ለመግለጽ የተዘጋጁም አሉ ።

የተዘጋጁ መስፈርቶች በአመዛኙ በርካታ ሰራተኞችን ከስራ ማግለልን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የሚገልጹት ሰራተኞች ኮርፖሬሽኑ መስፈርቱን የሚያሟላ ሰራተኛ ካጣ የስራ መደቦችን ክፍት አድርጎ እንደሚያቆይ ገልጾልናል ብለዋል።ሆኖም በተቃራኒ የውጭ ቅጥር ለመፈጸም አላማ ተይዞ መዋቅሩ እንደተሰራ መረጃ እንዳላቸው የገለጹልን የተቋሙ ሰራተኞች አሉ።

ኮርፖሬሽኑ በአዲሱ መዋቅር ከስራ ውጭ የሚሆኑ ሰራተኞች እንዲደራጁ አደርጋለሁ ሲል ለሰራተኞቹ ገልጿል።ነገር ግን በምን የስራ ዘርፍ ለማሰማራት እንደሚያደራጃቸውና ምን አይነት ዝግጅትስ እንዳደረገ አልገለጸም።


አሁን ላይ ኮርፖሬሽኑ ያዘጋጀው ከግማሽ በላይ የሆኑ ሰራተኞቹን ከስራ ገበታቸው የሚያፈናቅላቸው መዋቅር ከአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ጋር የሚቃረን ከመሆኑም በላይ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ ችግር ውስጥ እየገባ በርካታ ቁጥር ያለውን ሰራተኛ ለመቀነስ ማሰቡም ትችት እየቀረበበት ነው።


የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከተቋቋመ ጀምሮ በውስብስብ የአሰራር ብልሽቶች የተተበተበና ለኪሳራ የተዳረገ ፣ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮቹም ለእስር የተዳረጉበት ነው። በ10 ቢሊየን ብር ካፒታል የተመሰረተው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ተፈራርቀውበት አሁን ላይ በህይወት ሞሲሳ ዋና ዳይሬክተርነት እየተመራ ይገኛል። [ዋዜማ ራዲዮ]