ዋዜማ- የሀገሪቱ ሁለተኛ ትልቅ ከተማና የአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጀምራለች። የከተማዋ አስተዳደር ለዋዜማ እንደነገሩት የባህር ዳር የኮሪደር ልማት አንድም የሚያፈናቅለው ነዋሪ አልያም የሚያፈርሰው እዚህ ግባ የሚባል መኖሪያና የንግድ አካባቢ የለም።
የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ለዋዜማ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ እንዳብራሩት ሀምሳ ሜትር ስፋት ያለው – ሀያ ሁለት ኪሎሜትር የሚጠጋው የባህርዳር የኮሪደር ፕሮጀክት የመጀመሪያው ክፍል ስራ በመጪው ህዳር ይጠናቃቃል።
በፕሮጀክቱ የሚፈናቀል ነዋሪ የሌለው ባህርዳር አስቀድሞ በፕላን የተሰራች ከተማ በመሆኗና መንገዶቿም ሰፋፊ ስለሆኑ ነው። መጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ከቀድሞው ጊዮን ሆቴል እስከ አሮጌው ዓባይ ድልድይ ድረስ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ገልጸዋል።
በጦርነት ላይ ሆናችሁ ፣ በርካታ የሰብዓዊ ቀውስ ባለበት ሁኔታ እንዴት ወደ ኮሪደር ልማት ገባችሁ? በጀቱ የህዝቡን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት ቢውል አይሻልም ወይ? ብለን የጠየቅናቸው የባህርዳር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በግጭቱ ሳቢያ “የሚቋረጥም ሆነ የተቋረጠ የልማት ስራ የለም ይልቁኑም የአባይ ድልድይን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አካሂደናል” ብለውናል።
ከንቲባው ግጭቱ በክልሉ ልማት ላይ የሚያስከትለውን ብርቱ ጫና ቢያቃልሉትም በተግባር የባህርዳር ከተማ ከ22 ኪሎ ሜርት የኮሪደር ልማት ዕቅዱ መስራት የጀመረው የመጀመሪያ ክፍሉን 3.5 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ለሌሎች ፕሮጀክቶችም ቢሆን ተቋራጮች የረጅም ጊዜ የክፍያ ስምምነት እንዲገቡ ይጠየቃሉ። የአሁኑ ፕሮጀክትም የተጀመረው በመንግስት የልማት ተቋም በሆነው የአማራ መንገድ ስራዎች ድርጅት ነው።
ለዚሁ የኮሪደር ልማት የተያዘውን በጀት በተመለከተ አቶ አስሜ ይፋ ማድረግ እንደማይፈልጉና ምስጢር መሆኑን ነግረውናል።
የኮሪደር ልማቱ የባህርዳርን የብስክሌት አብዮት የመመለስና ማራቶንን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማካሄድ የሚያስችል ብቃት ለመፍጠር ራዕይ አለው። [ዋዜማ]