amisom-goob

በእንግሊዝኛ ምህፃረ-ስያሜው “አሚሶም” (African Mission in Somalia/AMISOM) የተሰኘው በሱማሊያ የሰፈረው ሃይል እኤአ በ2007 በዑጋንዳ 1600 ወታደሮች ነበር የተቋቋመው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከቡሩንዲ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ዑጋንዳ የተውጣጡ 22 ሺህ ወታደሮች አሉት፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም ዓቀፍ ሰላም አስጠባቂ ጦር ለማሳመራት ፍቃደኛ ባለመሆኑ አሚሶም እነሆ የምስራቅ አፍሪቃ ወታደሮች ስብስብ ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ያም ሆኖ አሚሶም በአፍሪካ ህብረት ታሪክ በጣም ትልቁ ህብረ-ብሄራዊ ጥምር ሃይል ሆኗል፡፡

ለመሆኑ የአፍሪካ ህብረት ጦር አልሸባብን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ የተሳነው ምን ዓይነት ፈተናዎች ቢያጋጥሙት ነው?  የአሚሶም አደረጃጀትና ወታደር ያዋጡ ሀገሮች የሚያራምዷቸው የተናጥል ፍላጎቶች ከአሚሶም ተልዕኮ ጋር ይጣጣማሉን? የአሚሶም መፃዒ እጣ ፋንታስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡(ቻላቸው ታደሰ የአሚሶምን የወቅቱ ይዞታና ፈተናዎች ተመልክቶታል- አድምጡት)

 

ራሱን እንደ ዓለም ዓቀፍ ሙጃሃዲን በመቁጠር ከአልቃይዳ ጋር መወገኑን ያሳወቀው አልሸባብ ላለፉት ስምንት ዓመታት የሱማሊያውን ፌደራላዊ መንግስት በመገልበጥ በሸሪያ የሚመራ መንግስት ለማቋቋም ፍልሚያ ላይ ነው፡፡
አሚሶምም እኤአ በነሃሴ 2011 ዓ.ም አልሸባብን ከሞቃዲሾ ካባረረ ጀምሮ በተከታታይ በርካታ ቦታዎችን ነፃ አውጥቷል፡፡

በስምንት ዓመት ታሪኩ በጣም ስኬታማ የሆነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ በአልሸባብ ላይ ድል መቀዳጀት ችሏል፡፡ የኬንያ ጦር ሰራዊት እኤአ በ2012 የኢትዮጵያ ደግሞ በ2014 በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን አሚሶምን መቀላቀላቸው ይታወሳል፡፡ ይህም ለአሚሶም ጥንካሬ ፈጥሮለታል፡፡
አልሸባብም ታዋቂው ኮማንደሩ አህመድ አብዲ ጎዳኔ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ የድሮን ጥቃት ከተገደለ በኋላ ፍፃሜው መቃረቡን የገመቱ ታዛቢዎች በርካታ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ የአልሸባብን እንቅስቃሴ ሁሉ የአልሞት ባይ ተጋዳይ መፍጨርጨር አድርገው ያዩታል፡፡

በአንፃሩ በርካታ ይዞታዎቹን መልቀቁን ከመዳከም ይልቅ ከስትራቴጂና ታክቲክ ለውጥ ጋር ብቻ የሚያያይዙት ታዛቢዎችም ብዙ ናቸው፡፡ በእርግጥም አልሸባብ እስካሁንም ለአሚሶምና ለሱማሊያ መንግስት ብቻ ሳይሆን በተናጥልም የኢትዮጵያ ሰራዊትን እየፈተነ ይገኛል፡፡ ድንበር ተሻግሮ በሚያደርሳቸው የሽብር ጥቃቶችም ለኬንያ የእግር እሳት ሆኖባታል፡፡ በሞቃዲሾ በሚገኙ የመንግስት ተቋማት፣ ዲፕሎማቶች በሚያዘወትሯቸው ሆቴሎች ላይም ከባድ አደጋዎች ማድረሱን ቀጥሏል፡፡

ከጥቂት ወራት ወዲህም በአሚሶም ላይም የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ጀምሯል፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር በአሚሶም ስር ያሉ የቡሩንዲ ወታደሮች የሚቆጣጠሩትን ካምፕ አጥቅቶ ከሰባ በላይ ወታደሮችን መግደሉ ይታወሳል፡፡ በያዝነው ወር መጀመሪያ ደግሞ በደቡብ ሱማሊያ በታችኛው ሸበሌ ግዛት በኡጋንዳ ወታደሮች ይዞታ ስር በነበረ የአሚሶም ካምፕ ላይ የተቀናጀና ድንገተኛ ጥቃት አድርሶ ሃምሳ ያህል የዑጋንዳ ወታደሮችን መግደሉንም የምዕራባዊያን ምንጮች ጭምር አረጋግጠዋል፡፡ ምንም እንኳን የኡጋንዳ መንግስት አስራ ሁለት ወታደሮቹ ብቻ እንደተገደሉበት ቢናገርም፡፡ እንዲያውም አልሸባብ በርካታ ወታደሮችን መማረኩንም እየተናገረ ነው፡፡
ሁለቱ ጥቃቶች በአሚሶም የስምንት ዓመት ታሪክ ተወዳዳሪ እንደሌላቸው በርካታ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ጥቃቶቹን ተከትሎም አሚሶም በደቡባዊና ማዕከላዊ ሱማሊያ ከሚገኙ አንዳንድ ይዞታዎቹ ለማፈግፈግ ሳይገደድ እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
መቼም አሚሶም በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እንደተወጠረ አይካድም፡፡ አንዱ ዋነኛ ችግሩ የራሱ ስኬት እስረኛ መሆኑ ነው፡፡ የሰው ሃይል፣ ሎጅስቲክና የመሳሪያ አቅርቦቶች እጥረት ነፃ ያወጣቸውን ሰፋፊ ግዛቶች ተቆጣጥሮ እንዳይቆይ እንቅፋት እንደፈጠሩበት ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ሃያ ሁለት ሺህ ወታደሮቹን በቅርቡ ነፃ ባወጣቸው ሰፋፊ ግዛቶች በማስፈሩ ሃይሉ ከምንጊዜውም በላይ ሳስቶበታል፡፡ ስለሆነም ለአልሸባብ የደፈጣና የፊት ለፊት ጥቃት ተጋልጧል፡፡
የአሚሶምን ታሪክ በማጥናት ላይ ያሉት ፕሮፌሰር ፖል ዊሊያምስ እንደሚሉት ከሁሉም በላይ የማጓጓዣና ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች እጥረት አንድ የአሚሶም ሃይል ጥቃት ሲፈፀምበት ሌላኛው በቶሎ እንዳይደርስለት አድርጓል፡፡ የአልሸባብን ሃይሎች እስከ ጫካ ድረስ ተከታትሎ ማጥቃት ያልቻለውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአሚሶም አዛዦች የተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ድጋፍ እንዲሰጣቸው ወይም ተጨማሪ ወታደሮች እንዲላኩላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ምላሽ ግን አላገኙም፡፡ ኡጋንዳ ግን በቅርቡ የተወሰኑ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችን ሰጥታለች፡፡ ችግሩን የባሰ የሚያደርገው ደግሞ አውሮፓ ህብረት ወጪው ስለበዛበት ለአሚሶም የመደበውን በጀት በ20 ፐርሰንት ሊቀንስ መሆኑን ሐምሌ ላይ ማስታወቁ ነው፡፡

በውጊያ ሞራላቸው ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ማወቅ ቢያስቸግርም የአሚሶም ወታደሮች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ መሆኑም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ እንዲያውም ለበርካታ ወራት ክፍያ የማያገኙ ወታደሮች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ተሳታፊ ሀገሮች ከአፍሪካ ህብረት ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት የአንድ ወታደር ወርሃዊ ደመወዝ አንድ ሺህ ሃያ ስምንት ዶላር ብቻ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግን ለአስተዳደራዊ ወጪ እየተባለ ሁለት መቶ ዶላር ከእያንዳንዱ ወታደር ይቀነሳል፡፡

ሌላው ከባድ ፈተና አሚሶም መደበኛ የውጊያ ዶክትሪን የሚከተል ሰራዊት (conventional army) ሆኖ ሳለ አልሸባብ ግን ስትራቴጂውንና ታክቲኩን በቀላሉ የሚቀያይር ሽምቅ ተዋጊ (guerilla force) ሃይል መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም አሚሶም ነፃ ያወጣቸውን ሰፋፊ ግዛቶችና ከተሞችን ሲጠብቅ አልሸባብ ግን ከተማዎችን የሚያገናኙ መንገዶችን በመዝጋት የአሚሶምን ስንቅና ትጥቅ አቅርቦት ለማሰናከል ተመችቶታል፡፡
በኢትዮጵያና አሚሶም ድጋፍ ሲደረግለት የኖረው የሱማሊያ መደበኛ ጦር ሰራዊትም በደንብ ተደራጅቶ የፀጥታውን ሙሉ ሃላፊነት መረከብ አለመቻሉ ሌላኛው ችግር ሆኗል፡፡ በውጊያ ያሚያሳየው ብቃትና የመዋጋት ፍላጎቱም በጣም አናሳ ሆኗል፡፡ የሰራዊቱ አዛዦችም በሙስና የተዘፈቁ እንደሆኑ የአሚሶም ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የአሚሶም ወታደሮችና ከፍተኛ የጦር አዛዦችም ቢሆኑ በህገ ወጥ ኮንትሮባንድ ንግድ፣ በሴቶች አስገድዶ መድፈር፣ በንፁኃን ሰዎች ግድያና በሌሎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውንጀላ ይቀርብባቸዋል፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱም ከአልሸባብ ጋር ጭምር እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ለአብነት ያህልም የዑጋንዳ ወታደሮች ባለፈው ሃምሌ ሰባት ንፁሃን ዜጎችን ያለ ምንም ምክንያት በመግደላቸው አሚሶም ይቅርታ ለመጠየቅ ተገዶ ነበር፡፡ አልሸባብም በቅርቡ በኡጋንዳ ጦር ላይ ጥቃት የፈፀመው ያንን ደም ለመበቀል እንደሆነ አስታውቋል፡፡ እነዚህ ነገሮች አሚሶም ከሱማሊያዊያን ጋር ያለውን ግንኙነት ክፉኛ መጉዳታቸው አይቀርም፡፡ በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነትም ይጎዳዋል፡፡

አሚሶም በአደረጃጀቱ ያልተማከለ በመሆኑ አባል ሰራዊቶቹ ከማዕከላዊው ዕዝ ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም የላላ ነው፡፡ የውጊያ ዶክትሪናቸውም ይለያያል፡፡ በቅርቡ አንድ የአሚሶም ኮማንደር ለቪኦኤ ሬዲዮ እንደተናሩት አንዳንዶቹ እንዲያውም ትዕዛዝ የሚቀበሉት ከአሚሶም ዋና አዛዥ ሳይሆን ከየሀገሮቻቸው መንግስታት ነው፡፡ ይህም የአሚሶምን ውስጣዊ ተግዳሮት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

የአምስቱ ሀገሮች ሰራዊቶች የሚቆጣጠሯቸው ቦታዎችም ስለሚለያዩ በአሚሶም ውስጥ ያለውን የእርስ በርስ ቅንጅት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ለአብነትም በቡሩንዲ ወታደሮች ላይ ጥቃት ሲፈፀም በቅርብ ርቀት የነበሩ የኡጋንዳና ኢትዮጵያ ወታደሮች በቶሎ መድረስ እንዳልቻሉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡
አሚሶምን ከሚያስወቅሱት ነገሮች መካከል ሌላኛው የሟቾችንና ቁስለኞችን ቁጥር አለማሳወቁ ነው፡፡ የስዊድኑ ስቶኮልም ዓለም ዓቀፍ የሰላም ጥናት ኢንስትቲዩት በቅርቡ ባወጣው ጥናት እንደሚለው እኤአ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የአሚሶም ሟች ወታደሮች ብዛት በጠቅላላው ከ1,100 በላይ ደርሷል፡፡ የተመድ ባለስልጣናት ግን እኤአ እስከ 2013 ድረስ ብቻ ሦስት ሺህ ያህል ወታደሮቹ እንደተገደሉበት ተናግረው ነበር፤ ተመድ በኋላ መረጃውን አስተባበለ እንጂ፡፡ እነዚህ አሃዞች ግን ኢትዮጵያና ኬንያ በተናጥል ባካሄዷቸው ዘመቻዎች የሞቱትን አይጨምሩም፡፡

ተሳታፊ ሀገሮችም መረጃውን ከአሚሶም ሳይቀር በመደበቅ ብሄራዊ ሚስጢር አድርገው ይይዙታል፡፡ የኢትዮጵያም ጦር ከአሚሶም ጋር ከመቀላቀሉ በፊት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ስለጉዳዩ ሲጠየቁ የጉዳት መጠንን ለፓርላማው የማሳወቅ ግዴታ እንደሌለባቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሀገሮቹ መረጃውን የማያወጡበት ምክንያት አልሸባብ ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እንዳይጠቀምበትና የተዋጊዎቻቸው ሞራል እንዳይጎዳ አስበው ሊሆን ቢችልም ሚስጢራዊነቱ ግን የመንግስታቱንና የአሚሶምን ተጠያቂነት ብሎም አመኔታ የሚያሳጣ መሆኑ እሙን ነው፡፡ የአልሸባብንም ሆነ የአሚሶምን እውነተኛ ጥንካሬና ድክመት ለማወቅም አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአፍሪካ ህብረትና በተሳታፊ ሀገሮች መካከል የተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ ለሟች ቤተሰቦችና ቁስለኞች ካሳ እንደሚከፈል ይገልፃል፡፡ የቁጥሩ አለመታወቅ ግን የካሳ ክፍያው ግልፅነት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ክፍያው የማይፈፀምበት አጋጣሚዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ቢፈፀምም እንኳን በጣም እንደሚዘገይ ተዓማኒ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚፈፀመው ክፍያም በስምምነቱ ከተገለፀው በታች እንደሆነ ፕሮፌሰር ፖል ውሊያምስ ይናገራሉ፡፡
ለአብነት ያህል ባለፈው ነሃሴ በተላለፈ አንድ የቪኦኤ ዘገባ የአንድ ቡሩንዲያዊ ሟች ወታደር ቤተሰቦች ሰላሳ ሺህ ዶላር የደም ካሳ የተቀበሉት ከአስራ አምስት ወራት በኋላ እንደሆነ ተገልፆ ነበር፡፡ ሌላ የአካል ጉዳት የደረሰበት ቡሩንዲያዊ ወታደርም ዓመታትን ከፈጀ ብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከአፍሪካ ህብረት 10 ሺህ ዶላር ብቻ እንደተሰጠው ለቪኦኤ መናገሩ ይታወሳል፡፡ በአሚሶም ጥላ ስር ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሟች ወታደሮች ቤተሰቦችና ቁስለኞችም በምን ሁኔታ እንደሚስተናገዱ ምንም መረጃ የለም፡፡

ሌላው የአሚሶም ተግዳሮት የየሀገሮቹ ፍላጎት አለመጣጣም ነው፡፡ በሱማሊያ ጉዳይ ላይ ኬንያና ኢትዮጵያ የየራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅሞች እንዳሏቸው እሙን ነው፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሱማሊያን ስለማትፈልግ አልሸባብ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ አትፈልግም እየተባለች ትታማለች፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን በግዛቷ ከአልሸባብ ቀጥተኛ ጥቃት አጋጥሟት አለማወቁን በመንተራስም አንዳንድ የኬንያ ፓርላማ አባላት ይህንኑ ጥርጣሪያቸውን ያስተጋቡበት ውቅት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአልሸባብ ዒላማ ያልሆነችበት ምክንያት ግን ራሱን የቻለ ጉዳይ ስለሆነ ለሌላ ጊዜ ማቆየቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ከጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከአሚሶም ጋር ከቀላቀለ በኋላም ከሱማሊያ መንግስት ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት አድርጎ በተናጥል ልዩ ተዋጊ ወታደሮቹንና ፖሊሶችን ማዝመቱን ቀጥሎበታል፡፡ ከወራት በፊትም ከሦስት ሺህ በላይ ወታደሮቹን ወደ ሱማሊያ እንዳስገባ የተለያዩ ዜና ምንጮች መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ከአሚሶም ጥላ ውጭ የመንቀሳቀስ ፍላጎት በተወሰኑ ሀገሮች ላይ ቅሬታ ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል፡፡ ባለፈው ነሃሴ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተቆጣጠሯት ሂራን ግዛት በድንገት ሲለቁ በቅርብ ርቀት ለነበሩት የጅቡቲ ወታደሮች ቀድመው ባለማሳወቃቸውም የጅቡቲ ጦር አዛዦች ከባድ ቅሬታ አሰምተው ነበር፡፡
ኬንያ በበኩሏ ነፃ ያወጣችውን አካባቢ “ጁባላንድ” የተሰኘ ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሆን አድርጋለች፡፡ ዋና ዓላማዋም የአልሸባብ ሰርጎገቦች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ የፀጥታ ቀጠና መከለል ነው፡፡ የምዕራባዊያን ዋና ዓላማም ቢሆን በሱማሊያ የከተሙ ዓለም ዓቀፍ ሽብርተኞችን መመንጠር እንጂ እንደ አፍጋኒስታን ዓይነት የሀገር ግንባታ ዕቅድ እንደሌላቸው እሙን ነው፡፡
በሱማሊያ መስከረም 2016 ላይ ብሄራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ዕቅድ ቢያዝም አሚሶም ግን የተረጋጋ የፀጥታ ሁኔታ መፍጠር ስለመቻሉ አጠራጣሪ እየሆነ ነው፡፡ ራሱ አሚሶም ከምርጫው ቀደም ብሎ እንደሚወጣ የተወሰነው ውሳኔም ተግባራዊነቱ ያጠራጥራል፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ አሚሶም ከአጥቂነት እንደገና ወደ ተከላካይነት እንዳይመለስ ያሰጋል፡፡
መቼም አሚሶም አፍሪካ በታሪኳ ካየቻቸው የሰላም ተልዕኮዎች ሁሉ በአደገኛነቱ ተወዳዳሪ ያለው አይመስልም፡፡ ስለሆነም አባል ሀገሮች ጉዳታቸው እየጨመረ ሲሄድ ወታደሮቻቸውን በተናጥል ለማስወጣት ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ ያኔ የተባበሩት መንግስታት ተጨማሪ ሰራዊት ለማዝመት ይፈቅዳል ብሎ መጠበቅ አዳጋች ነው፡፡ በጠቅላላው ሲታይ የሱማሊያ ፖለቲካዊ ሁኔታ የአሚሶምን ዕጣ ፋንታ እየወሰነው ነው፡፡ የአሚሶም ነባራዊ ሁኔታና መፃዒ ዕጣ ፋንታም እንዲሁ የሱማሊያን፡፡