ዋዜማ- የስዊድን መንግሥት፣ በአገሩ ለምትገኘው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲሰጥ የቆየውን ዓመታዊ ድጎማ ማገዱን የአገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮ ዘግቧል።
የእምነት ማኅበረሰቦችን የሚረዳውና ከመንግሥት ጋራ ያላቸውን ግንኙነት የሚያስተባብረው የመንግስት ኤጀንሲ ለቤተ ክርስቲያኒቱ በየዓመቱ ይሰጣት የነበረውን 800 ሺህ ክሮነር (85 ሺህ ዶላር ገደማ) ድጎማ ያገደው የስዊድን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ መሆኑን አስታውቋል።
የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ (Swedish Security Service) ሪፖርት ቤተ ክርስቲያኒቱ “የኤርትራ መንግሥትን በመወከል ወይም ከእርሱ ጋራ በመተባበር በስዊድን የሚገኙ ዜጎችን መሠረታዊ ነጻነት የምትጥስበት አደጋ/ስጋት አለ” በማለት ከሷል።
“ብላንክ ስፖት” የተባለው ሚዲያ እንደዘገበው፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሰጣት ድጎማ የኤርትራ መንግሥትን በገንዘብ ሊያግዝ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ ተወካይ አብርሃም ተስፋይ “ከኤርትራ መንግሥት ጋራ ምንም ግንኙነት የለንም። ግንኙነታችን ኤርትራ ከሚገኘው የቤተ ክርሲትያኒቱ ሲኖዶስ ጋር ብቻ ነው” በማለት ክሱን አስተባብለዋል። ውሳኔውን በመቃወም አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። በስዊድን ተመዝግበው የአገሩን ሕግ አክብረው ሲሰሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል። ክሱ አዲስ አለመሆኑንና ለዓመታት ሲያስተባብሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲስ ለሚመጡ ስደተኞች፣ እንዲሁም ብቸኝነት ለሚያጠቃቸው ሰዎችና ለወጣቶች የምትሰጠው አገልግሎት ከግምት አለመወሰዱ እንዳሳዘናቸውም አልሸሸጉም።
አንዳንድ የስዊድን እና የኖርዌ ፖለቲከኞችንና ፓርቲዎች በአገራቸው ከሚኖሩ የኤርትራ ስደተኞች መካከል ሸሽተነዋል የሚሉትን የአገራቸውን መንግሥት የሚደግፉ እንዳሉ በመጥቀስ የተሰጣቸው ጥገኝነት እንዲሻር መገፋፋት ከጀመሩ ቆይተዋል።
በኖርዌ፣ ሐሰተኛ መረጃ በማቅረብ የተገኘ የመኖሪያ ፈቃድም ሆነ ዜግነት በሕግ ሊቀማ ይችላል። በስዊድን ዜግነትን መቀማት በሕግ የተፈቀደ ባይሆንም አሁን ያለው አዝማሚያ ወደዚያ እንደሚያደርስ ነዋሪዎች ይጠቁማሉ።
የኖርዌ የስደተኞች ጉዳዮች ኤጀንሲ ባለፈው ወር የአምስት ኤርትራውያን ስደተኞች የኖርዌ ዜግነት እንዲቀማ ጥያቄ ማቅረቡ ተዘግቦ ነበር።
“የብላንክ ስፖት” ሪፖርት እንደሚለው፣ የሌሎች ሃያ ያህል ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ ተሰርዟል። ይህ እርምጃ በፍርድ ቤት ከጸና ከአገር እስከመባረርም ሊያደርሳቸው ይችላል። ለስደተኞቹ ፈቃድና ዜግነት መገፈፍ የቀረበው ምክንያት ከኤርትራ መንግሥት ጋራ የቅርብ ግንኙነት አላቸው፣ መንግስቱን በገንዘብ ጭምር ይረዳሉ የሚል ነው። [ዋዜማ]
