ዋዜማ- በሕወሓት ሃይሎች፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት በስፋት በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀንና በመረጃ ትንተና ተቋማት እየተነገረ ነው። እየተነገረ ካለው ውጪ የጦርነት ዝግጅት እየተደረገባቸው ነው በሚል በሚጠቀሱ አካባቢዎች ስላለው ሁኔታ ዋዜማ ነዋሪዎችን አነጋግራ ይህን ዘገባ አዘጋጅታለች።
ኣዲግራት፣ ዘላምበሳ፣ሽራሮ እና ኢሮብ
አቶ በርኸ እና ባልደረባቸው የኣዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ በሙያቸው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ናቸው፡፡ እየተባባሰ የመጣውን ፖለቲካዊ ውጥረት ተከትሎ በጭንቀት መዋጣቸውን የሚገልጹት መምህራኑ፤ ጦርነቱ ከዛሬ ነገ ይጀመራል በሚል ፍራቻ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ስጋቱን ተከትሎ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ ማሻቀቡን እና ካለው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ጋር ተዳምሮ ፈታኝ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ1300 እስከ 1500 ብር ይሸጥ የነበረው 5 ሊትር ዘይት ከ2350 እስከ 2500 ብር ፤ ጤፍ በኩንታል ከ12 ሺህ 500 እስከ 14 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ፤ ቡና እንደየ አይነቱ መነሻ ዋጋው 1150 ብር የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን መነሻ ዋጋው 1600 ብር መድረሱን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ የመሰረታዊ ሸቀጦች እንዲሁም የምግብ ፍጆታዎች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነግረውናል፡፡ የነዳጅ እጥረት በመኖሩ ምክንያትም ከዚህ ቀደም ከ90 እስከ 100 ብር ይከፈልበት የነበረው የአጭር ርቀት ጉዞ ከ250 እስከ 500 ብር እንደሚከፈል ተናግረዋል፡፡
ከአዲግራት ከተማ ጥቂት ኪሎሜትሮች ርቃ በምትገኘው ‹‹ዛላምበሳ›› እና በሰሜን ምእራባዊ ዞን በምትገኘው ‹‹ሽራሮ››ም በተመሳሳይ መልኩ የተጋነነ የዋጋ ንረት የሚስተዋል ሲሆን ጦርነቱ ‹‹በቅርቡ ሊቀሰቀስ ይችላል›› በሚል ፍራቻ ነዋሪዎች ያላቸውን ገንዘብ በየቀኑ ከባንክ እያወጡ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከባንኮች በቀን ማውጣት የሚቻለው የገንዘብ መጠን 1000 ብር ሲሆን ነዋሪዎች በየእለቱ የሚያወጡትን ገንዘብ በጥሬው ማስቀመጥ እና በመዝናኛ ስፍራዎች የነበራቸውን እንቅስቃሴም መግታታቸውን ገልጸውልናል፡፡
በወረዳ እና ቀበሌ የተደራጁ በተለምዶ ‹‹ልምአት ጉጅለ›› በመባል የሚጠሩት ካድሬዎች፤ ነዋሪዎች ለክፉ ቀን የሚሆናቸውን የጤፍ፣ ስንዴ ወይም ገብስ እህል ፣ ቆሎ፣ ድርቆሽ እና የመሳሰሉትን እንዲያዘጋጁ እና ጥሬ ገንዘብም እንዳያባክኑ ቤት ለቤት በመዞር ማሳሰቢያ መስጠታቸውን ሰምተናል፡፡ በከተሞቹ ውስጥ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ቢቀዛቀዝም፤ በድንበር አካባቢ ግን ከጥሬ ገንዘብ እጥረት ጋር ተያይዞ በናቅፋ እና ዶላር የሚፈጸም ግብይት አለ ብለዋል፡፡
የኤርትራ ጦር ትግራይ ገብቷል?
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የዛላምበሳ ከተማ ነዋሪዎች ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ የኤርትራ ጦር ዩኒፎርም ቀይሮ ወደ አካባቢው ገብቷል ብለው እንደሚጠረጥሩ ይናገራሉ፡፡
‹‹የኤርትራ ወታደሮች ገብተዋል እየተባለ ይወራል፡፡ ይህን ስንሰማ ባለፈው ጦርነት የተፈጠረውን ስለምናስብ በጣም እንጨነቃለን፤ እንፈራለን፡፡ እርግጠኛ ሆነን መናገር ባንችልም የኤርትራ ወታደሮች የሚጫሙትን ፕላስቲክ ጫማ ያደረጉ፤ ነገር ግን የትግራይ ሃይሎች የሚለብሱትን ዩኒፎርም የለበሱ፤ መንገድ ላይ ድንገት አስቁመው ወዴት እየሄድን እንደሆነ የሚጠይቁ፤ የምንሄድበትን ቦታ ስንነግራቸው የቦታው ስም ግራ የሚያጋባቸው ታጣቂዎችን እናያለን›› በማለት አብራርተዋል፡፡
የአዲግራት ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህራንም ከቀናት በፊት መሰል ሁኔታ እንደገጠማቸው ጠቅሰው፤ ‹‹ከአዲግራት ትንሽ ወጣ ብሎ ፋጺን ወይም ዕዳጋ ሓሙስን የማያውቅ የለም፡፡ በድንገት ያስቆሙን የትግራይ ሃይሎችን ዩኒፎርም የለበሱ ወታደሮች በድንገት አስቁመውን ወዴት እንደምንሄድ ጠየቁን፤ ወደ ዕዳጋ ሓሙስ አልናቸው፡፡ እሱ ደግሞ የት ነው ብለው ሲጠይቁን፤ ከተጫሙት ጫማ እና አጠቃላይ ገጽታቸው ጋር ተዳምሮ የኤርትራ ወታደሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠረጠርን›› ሲሉ ሁኔታውን አብራርተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከእኩለ ሌሊት እስከ ንጋት ሰአት ባለው ጊዜ የተሸፈኑ የጭነት ተሸከርካሪዎች ከኤርትራ በዛላምበሳ አድርገው ወደ አዲግራት፣ መቐለ እና ሌሎችም ከተሞች እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንደ ሳሙና፣ ጤፍ እና መሰል መሰረታዊ ሸቀጦች ወደ ኤርትራ ይጓዛሉ፤ አንዳንድ ጊዜም ባዶ መኪኖች ወደዚያ መስመር ሲጓዙ እንመለከታለን፤ ሌሊት ግን ጭነት ይዘው ተሸፍነው ነው የሚገቡት፤ ክፍት ሆኖ ያየው ሰው ባይኖርም፤ እዚህ ከተማ ውስጥ መሳሪያ እየገባ እንደሆነ ነው የሚወራው፤ እኛም እንደዚያ ነው የምንጠረጥረው›› ብለዋል፡፡
በኢሮብ ከተማ እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ ውጥረት እንደፈጠረባቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፤ የኤርትራ ወታደሮች በከዚህ ቀደሙ ጦርነት ወቅት ገብተው እስካሁን ‹‹እንዳልጌይዳ›› እና ‹‹ወረዓትለ›› ከሚባሉት ቀበሌዎች አለመውጣታቸውን አመልክተዋል፡፡
የኤርትራ ጦር ከትግራይ እና አማራ ክልሎች ጋር በተከዜ ወንዝ በሚዋሰነው ‹‹ኦም-ሓጅር›› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጦሩን ማስጠጋቱን የገለጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሁመራ አካባቢ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ በጭንቀት መዋጣቸውን ነው የሚገልጹት፡፡ ከኤርትራ ጦር ባሻገር የትግራይ ሃይሎች እንቅስቃሴ እና የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው በከፍተኛ መጠን መግባት፤ ‹‹ጦርነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀረበን ነው ብለን እንድናስብ ሆነናል›› በማለት ስጋታቸውን አጋርተውናል፡፡
መከላከያ ሰራዊት ወደ ሰሜን እየተሰባሰበ ነው
የመከላከያ ሰራዊት ግጭት ካለባቸው የኦሮሚያ፣ አማራ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች እየወጣ ስለመሆኑ ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች፡፡
ሰራዊቱ ለአመታት የግጭት ቀጠና ከሆነው የቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን ወረዳዎች ለቆ እየወጣ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በዞኑ የወንበራ፣ ድባጤ እና ቡለን ወረዳ ነዋሪዎች የሸኔ ታጣቂዎች የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ዋዜማ ከነዋሪዎቹ ሰምታለች።
የመከላከያ ሰራዊት “ጋሌሳ” ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ላይ ወደ ሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ጠቅልሎ መግባቱን ጠቅሰው፤ከጥር 30 ጀምሮ የክልሉን አካባቢዎች ለቅቆ እየወጣ እንደሆነ እና ይህ የሆነበት ምክንያትም ወደ ሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ሊያቀና በመሆኑ እንደሆነ መስማታቸውን የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች ነግረውናል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ፣ ምእራብ ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ሲንቀሳቀስ የቆየው ሰራዊትም በተመሳሳይ መልኩ ካለፈው ወር ጀምሮ እየወጣ እንደሆነ የገለጹት የዋዜማ ምንጮች፤ ወጣቶችና አርሶ አደሮች አካባቢያቸውን ‹‹ከሸኔ እንዲጠብቁ›› በሚል ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ገብተው ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሰራዊቱ በአማራ ክልል ደብረታቦር ከተማን ጨምሮ ግጭት ካለባቸው የደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች መውጣቱን ተከትሎ የፋኖ ሃይሎች ከተማዋን መቆጣጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት ትግራይና አፋርን እንዲሁም አማራና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑት አካባቢዎች መስፈሩን የገለጹት የዋዜማ ምንጮች፤ ወደ አፋር ፣ ሁመራ እና ቆቦ አካባቢዎች በብዛት እየገባ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ [ዋዜማ]
