ዋዜማ ራዲዮ- ከቅርብ ወራት ወዲህ በውዝግብ የተጠመደው የሰማያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት በጋዜጠኞች ፊት ግብ ግብ ገጠሙ።
ከወራት በፊት ፓርቲው ነባሩን ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን አግዶ በምትኩ አቶ የሺዋስ አስፋን የመረጠ ሲሆን ነባሩን ምክር ቤት በትኗል። ነባሩ አመራር ግን ድርጊቱ ህግን የጣሰ ነው በሚል ሲቃወም ቆይቷል።
ማክሰኞ ዕለት (ዛሬ) አዲሱ አመራር የፓርቲውን የ2009 በጀትን በሚመለከት መግለጫ ሊሰጥ ጋዜጠኞችን ጠርቶ ነበር ይሁንና በቀድሞው የም/ር ቤት አባልነት እና በአዳዲሶቹ አመራሮች መሀከል በተፈጠረው ዘለፋና ግጭት ፕሮግራሙና ጋዜጣዊ መግለጫው ተሰርዟል።
በቅርቡ የተመረጠው አዲሱ አመራር የ2009 የፓርቲውን በጀት ለማሳወቅ ጋዜጠኞችን ቢሮው ይጠራል በዚያ መሀል ፓርቲው ከአባልነት አግጃቸዋለሁ ያላቸው የም/ቤት አባላት ቢሮው በመድረስ አዲሱ አመራር ምንም አይነት ፓርቲውን የተመለከተ መግለጫ መስጠት አይችልም በሚል ተቃውሞ ያነሱና ህጋዊ ውክልና እንደሌላቸው ለጋዜጠኞች ይነግራሉ።
የአዲሱ ተመራጭ የአቶ የሽዋስ አሰፋ ቡድን ደግሞ ተቃውሞ ያነሱትን ሰዎች ከግቢው ለማስወጣት ሲሞክሩ ሁኔታው ይባባስና በሁለቱም ወገኖች መሀከል እጂግ ፀያፍ የሆኑ ምልልሶች ተደርጓል ።
በአዲሱ የፓርቲው አመራሮች ከፓርቲው አባልነት ተባራችኃል የተባሉት የቀድሞ የም/ር ቤት አባላት ያሰሙ የነበሩት ተቃውሞ ህጋዊው የፓርቲው መሪ ኢ/ር ይልቃል ናቸው እኛም በጠቅላላው ጉባኤ የተመረጥን የም/ር ቤት አባላት በመሆናችን እናንተ ፓርቲውን ወክላችሁ መግለጫ ለመስጠት በምርጫ ቦርድ በኩል ህጋዊ ተቀባይነት አላገኛችሁም ፣ህጋዊ ውክልና አለን የምትሉ ከሆነ የተሰጣችሁን ሰነድ ለመገናኛ ብዙሀን አባላት አሳዩ ይህንን ምድረግ ካልቻላችሁ መግለጫ ልትሰጡ አትችሉም ብለው ከመቃወማቸውም በላይ የተደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ በመቃወም አቤቱታችንን ለቦርዱ በማስገባታችን ህግ በያዘው ጉዳይ ላይ ምንም ማድረግ አትችሉም በሚል ከልክለዋል።
አዲሱ አመራር ተቃዋሚዎችን ማስቆምም ሆነ የተጠየቀውን የቦርድ ሰነድ ማቅረብ ባለመቻሉ ውዝግቡ አሳፋሪ በሆኑ የስድብ ቃላት ተቀይረው አንዱ ባንዱ ለሰአታት ሲዝት በቦታው ሆነው የመገናኛ ብዙሀን አባላት ሲመለከቱ ነበር ። ዛቻውና ስድድቡን የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ተቁም የሆነው የአ. አ አስተዳደር ቴሌቪዥን ሁሉንም ነገር ይቀርፅ ነበር ።
ተቃውሞውና ተራ አፍ እላፊ በተነሳበት የሰማያዊ ፓርቲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ አዲሱ ተመራጭ አቶ የሽዋስ አሰፋና ሌሎች አባሎቻቸው የነበሩ ሲሆን የቀድሞው የፓርቲው የም/ር ቤት አባላት ተገኝተዋል በውዝግቡ ላይ የፓርቲው የቀድሞ መሪ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት በቦታው አልታዩም።