ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ስለተገደሉት ዜጎች ጉዳይ እንዲያጣራ የተሰየመውና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለው መርማሪ ቦርድ የማጣራት ተልዕኮውን እንዲያቋርጥ መታዘዙን የዋዜማ ምንጮች አመለከቱ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ስብሳቢ በአቶ ታደሰ ወርዶፋ የሚመራውና አስራ ሁለት አባላትን ያካተተው መርማሪ ቡድን ከመጋቢት 16 እስከ መጋቢት 24 ድረስ ወደ ሞያሌ ተጉዞ ምርመራ የማካሄድ እቅድ ነበረው።
ይሁንና መጋቢት 16 የመርማሪ ቡድኑ አባላት ወደ ሞያሌ ለመጓዝ በተሰባሰቡበት ወቅት “ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ” ነው በሚል ከጉዟቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን የቡድኑ አንድ አባል ይናገራሉ።
“የተወሰነው ጉዞውን መቀጠል አለብን አንመለስም ስንል ሌሎች ደግሞ መመለስ አለብን ስላሉ ጉዞው ሳይካሄድ ቀርቷል” ይላሉ ለዋዜማ ጉዳዩን ያሰረዱት አባል።
የመርማሪ ቡድኑ እንዲመለስ የትኛው ባለስልጣን ትዕዛዝ እንደሰጠ እንደማያውቁም ይናገራሉ።
ቡድኑ ወደ ሞያሌ ተጉዞ ከሟች ቤተሰብ፣ ከቁስለኞች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመነጋገርና መረጃ በማሰባሰብ በመከላከያ ሰራዊቱ ስለተገደሉት ዜጎች አጣርቶ ለመምጣት ተልዕኮ ነበረው። ከዚህ በኋላ መርማሪ ቡድኑ ስራውን ይቀጥል እንደሆነ አባላቱ ብዙም ተስፋ አያደርጉም።
የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በመረጃ ስህተት ነው በሚል ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች ገድለው አስራ ሶስት ያቆሰሉ ሲሆን ስምንት ሺ ያህል ወገኖች ደግሞ ወደ ኬንያ ተሰደዋል።
ድርጊቱ በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን መንግስት ድርጊቱን የፈፀሙትን የሰራዊቱ አባላት ትጥቅ አስፈትቶ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተናግሯል።
የሰራዊቱ አባላይ የኦነግ ታጣቂዎች በድንበር በኩል ጥሰው ገብተዋል የሚል መረጃ ደርሶት ለወታደራዊ ግዳጅ ወደ አካባቢው እንደተሰማራም መንግስት ገልጿል።
ወታደራዊ አዋቂዎች ግን ሽምቅ ተዋጊን ለመምታት የተንቀሳቀሰ ስራዊት እንዴት በመሀል ከተማና ህዝባዊ እንቅስቃሴ በሚደረግበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን መለየት ይሳነዋል? ሲሉ መንግስት የሰጠውን ምክንያት ተዓማኒነት አጠራጣሪነት ያሰምሩበታል።
መንግስት ባለፉት ሁለት አመታት በተለያየ መንገድ ለተከሰቱ ግድያዎች አጣሪ ቡድ አቋቁሜ ጥፋተኞችን ለፍርድ አቀርባለሁ ቢልም እስካሁን ተዓማኒ የሆነ ማጣራት ተደረጎ ለፍርድ የቀረበ አካል የለም። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]
https://youtu.be/E37hFPGLYLI