ዋዜማ ራዲዮ- የዘመናዊ ዉትድርና አባት በመባል የሚሞካሹት ሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሉ የሥራና የሕይወት ዘመንን የሚተርክ መጽሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዉሏል፡፡ ፀሐፊው አቶ ዓለምነህ ረጋሳ ሲኾኑ በቀድሞው የባህል ሚኒስቴር የሥነ ጽሑፍ አደራጅ ኾነው ከመሥራታቸው በላይ በርካታ የመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ላይ ተሠማርተው ቆይተዋል፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢፌድሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፕሬስ ሕዝብ ግንኙነትና የቃለ ጉባኤ ማደራጃ አገልግሎት ኃላፊ ኾነው ከሰሩ በኋላ ወደ ፕሬዚደንቱ ጽሕፈት ቤት በማምራት አሁን የኢፌድሪ የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት የፕሮቶኮልና ተቀዳሚ ዳይሬክተር በመኾን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
በ148 ገጾች የተሰናዳው የሜጀር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሉ መጽሐፍ የባለታሪኩን ከ1906 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 1953 ዓ.ም ያሉትን የ47 ዓመታት ጉዞን ይቃኛል፡፡
በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለው ይህ መጽሐፍ የባለታሪኩን የልጅነት አስተዳደግ፣ የማይጨው ዘመቻና ስደት፣ ክብር ዘበኛን መልሶ እስከማደራጀት ያለውን ታሪክ በቀዳሚ ምዕራፍ ይተርካል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የቃኘው ሻለቃ ጦር ምስረታና የኮርያ ዘመቻንና የጄኔራሉን የኮሪያ ቆይታ በስፋት ይዳስሳል፡፡
በምዕራፍ አራት የጄኔራሉን የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሾመትና የሕዝባዊ ኑሮ እድገትን የያዘ ሲኾን የመጽሐፉ የመጨረሻው ምዕራፍ የሜጀር ጄኔራሉን አሟሟት የሚተርክ ነው፡፡
በመጽሐፉ ቀዳሚ ገጽ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚደንት ኮሎኔል መለሰ ተሰማ በመጽሐፉ ባለታሪክ ዙርያ ስሜታዊ የሚመስል አድናቆትን በማኅተም አስደግፈው ጽፈዋል፡፡ “…ሰውየው በጦር ግንባር እንደወታደር የተዋጋ፣ እንደ ወታደር መሪ ያዋጋ፣ ጀግና ስለአገሩ ፍቅር ልቡ የነደደ፣ ተጋድሞ የተገረፈ፣ በስቃይ ልቡ ያልተሸበረ፣ በዓላማው የጸና፣….” በሞል ዘለግ ያለ አድናቆትን ችረዋቸዋል፡፡
በማስተር ማተሚያ ቤት የታተመው ይህ መጽሐፍ በጸሐፊው የግል አሳታሚነት በ85 ብር ለአገር ዉስጥ አንባቢ ቀርቧል፡፡