ዋዜማ ራዲዮ- በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትና መቀሌ ተደብቀው የነበሩት የሜቴክ ዋና ስራ አስኪያጅ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
የመንግስት የፀጥታ ምንጮች እንደነገሩን የሜቴክ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ሁመራ አካባቢ በፌደራል ፖሊስና በትግራይ ክልል ልዩ ሀይል ትብብር በቁጥጥር ስር ውለው ወደ አዲስ አበባ ተወስደዋል።
ክንፈ ወደ ሁመራ የሄዱት ለሽሽት እንደነበረ ቢነገርም እስካሁን ከመንግስት ወገን ማረጋገጫ አልተገኘም።ግለሰቡ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ከስራ ሀላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን ያለፉትን ወራት መቀሌ ተሸሽገው ቆይተዋል።
ሜጀር ጀነራል ክንፈ በሜቴክ ውስጥ ተፈፅሟል ለተባለው በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ምዝበራና ብልሹ አሰራር ተጠርጣሪ ሲሆኑ ቀደም ሲል የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ስራተኞች ለምርመራ በፖሊስ ተይዘዋል።
ፖሊስ ሌሎች የደህንነት መሪዎችን ለመያዝ ሙከራ እያደረገ መሆኑንም ስምተናል ። ዝርዝር እናክልበታለን።