ዋዜማ- ኢትዮጵያ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ፣ም አንስቶ የብር የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጓን ተከትሎ፣ የአፈር ማዳበርያ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ መረዳት ችላለች።
ይህ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየው፣ መንግሥት በዚህ ዓመት ለአርሶ አደሩ ለሚያቀርበው ማዳበርያ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ አደርጋለሁ ባለበት ጊዜ ነው።
መንግስት ከ2017 እስከ 2018 ዓ፣ም ላለው የምርት ዘመን በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበርያ እንደሚያስገባ መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መሠረት መንግሥት በዚህ ዓመት የማዳበርያ ዋጋ ላይ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ ካደረገ፣ ለእያንዳንዱ ኩንታል ማዳበርያ 3 ሺሕ 500 ብር ድጎማ አድርጓል ማለት ነው።
መንግስት በዚህ መጠን ድጎማን አድርጌያለሁ ቢልም፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ካሰባሰብነው መረጃ መረዳት እንደቻልነው የማዳበርያ ዋጋ ከባለፈው ዓመት አንጻር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር እና ባሕርዳር ዙርያ አካባቢ ካሉ አርሶ አደሮች ዋዜማ እንደሰማቸው ከሆነ፣ ለተያዘው ዓመት የምርት ጊዜ የአንድ ኩንታል ማዳበርያ ዋጋ ከ8 ሺሕ እስከ 9 ሺሕ ብር እንደሆነ ከየአከፋፋይ ዩኒየኖቻቸው እንደተነገራቸው ነግረውናል። ይህ ባለፈው ዓመት ከ3 ሺሕ 500 እስከ 4 ሺሕ ብር ከነበረው ዋጋ ከእጥፍ በላይ ከፍ ያለ መሆኑን መረዳት ችለናል። ሆኖም በዩኒየኖች አማካኝነት የሚነገረው ዋጋ ትክክለኛ መግዣው ዋጋ እንዳልሆነ እና ማዳበርያ በነጋዴዎች በኩል በተደጋጋሚ እንዲሸጥ ስለሚደረግ፣ ዋጋው ከዚህም ከፍ እንደሚል ሰምተናል።
ባለፈው ዓመትም የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ በኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ከተገጸው ዋጋ ከ2 ሺህ ብር በላይ ጭማሪ ተደርጎበት ይገዙ እንደነበር የነገሩን አርሶ አደሮች፣ ለዚህ ዓመት ከተነገረው የ8 እና 9 ሺህ ብር ዋጋ ተጨማሪ እንዳይጠየቁ ስጋት እንዳላቸው ገልጸውልናል።
ከኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቦር ዞን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችም አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ በ9 ሺህ ብር ለመግዛት እንደተመዘገቡ ነግረውን፣ ይህም ከአምናው አንጻር ከእጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ የታየበት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል፣ በዚሁ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ለዚህ ዓመት የመኸር እርሻ ወቅት የሚሆናቸውን ማዳበሪያ ዋጋ ገና እንዳልተነገራቸው ገልጸውልን፣ ለበልግ እርሻ በገዛነው ማዳበሪያ ላይ የታየው ጭማሪ ግን በመኸር እርሻውም ላይ ተመሳሳይ ጭማሪ እንደሚኖር ጠቋሚ ነው ብለውናል። ባለፈው ዓመት ለበልግ እርሻ ከኅብረት ስራ ዩኒየኖች የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ 3 ሺሕ 500 ብር የተተመነ ሲሆን፣ ለዚህ ዓመት ግን የሁለት ሺህ ብር ጭማሪ አሳይቶ የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ ከዩኒየኖች 5 ሺሕ 500 ብር ነበር ብለውናል። ለመኸር የምርት ወቅት በሚቀርበው ማዳበርያ ላይም ከዚህ የባሰ የዋጋ ጭማሪ ይኖራል ብለው እንደሰጉ ነግረውናል።
የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉን ተከትሎ፣ የአንድ አሜሪካ ዶላር ዋጋ ከ58 ብር ተነስቶ ሰሞኑን በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ126 ብር እንዲሁም በግል ንግድ ባንኮች ደሞ 130 ብር እየተሸጠ ይገኛል። በዚህ የምንዛሬ ተመን ልዩነት ሳቢያ በማዳበርያ ዋጋ ላይ የሚመጣው የዋጋ ልዩነት ወደ አርሶ አደሩ እንዳይተላለፍ መንግስት በኩንታል 3 ሺሕ 500 ብር እደጉማለሁ ቢልም፣ ይህን ያህል የዋጋ ልዩነት መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ያነጋገርናቸው ሁሉም አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት ዩሪያ እና ዳፕ በተሰኙት የአፈር ማዳበሪያዎች ዓለማቀፍ ገበያ ላይ ካለፈው ዓመት እስከዚህ ዓመት ድረስ የተጋነነ ጭማሪ አልታየም። በ2014 ዓ፣ም የአንድ ሜትሪክ ቶን ዩሪያ ዋጋ 700 የአሜሪካ ዶላር ተሻግሮ በታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ጭማሬ ካሳየ በኋላ፣ በተከታይ ዓመታት ቅናሽ አሳይቶ በ2015 ዓ፣ም 358 ዶላር፣ በ2016 ዓ፣ም 350 ዶላር፣ በዚህ ዓመት ደሞ በሜትሪክ ቶን 325 የአሜሪካ ዶላር ሆኗል።
ሌላኛው የማዳበሪያ ዓይነት ዳፕ፣ ካለፈው ዓመት እስከዚህኛው ዓመት በቶን ከ530 እስከ 595 ዶላር ባለው ዋጋ መካከል ነው በዓለማቀፍ ገበያ ሲሸጥ የቆየው።
የማዳበርያዎቹ ዓለማቀፍ ዋጋ የተጋነነ ጭማሪ ሳያሳይ መንግስት 84 ቢሊየን ብር ድጎማ አድርጎም፣ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በአገር ውስጥ የማዳበርያ ዋጋ ላይ ታይቷል። ለዚህ ዓመት የምርት ዘመን በማዳበሪያ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሬም፣ በቀጣይ ዓመት በሰብል ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት ያስከትላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል። በግብርና ሚንስቴር የግብርና ግብዓት አቅርቦት መሪ ሥራ አስፈጻሚ መንግሥቱ ተስፋዬ፣ ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአፈር ማዳበሪያ ላይ መንግሥት ድጎማ ባያደርግ እንዲሁም ታክስ እና ቀረጥ ቢታከልበት ኖሮ፣ ዋጋው አሁን ካለበት ይልቅ እንደነበር ገልጸዋል። [ዋዜማ]