ዋዜማ- መንግስትና ሕወሓት በደቡብ አፍሪቃ በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት መሰረት ዛሬ ደግሞ ስምምነቱን መተግበር የሚያስችላቸውን ወታደራዊ አፈፃፀም፣ የመሰረታዊ አገልግሎትና ስብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴን የተመለከተ ሰነድ ፈርመዋል።
በኬንያ ናይሮቢ የተፈረመው ስምምነት የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን አግባብና የጊዜ ሰሌዳ እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት ውጪ በትግራይ ውስጥ ያሉ ታጣቂ ኀይሎች ከክልሉ የሚወጡበትን መርሃግብር ይዟል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የሕወሃት ወታደራዊ አመራሮች ዛሬ ዛሬ ናይሮቢ ላይ የፈረሙት የጋራ ስምምነት መግለጫ ከተካተቱት አንኳር ጉዳዮች መካከል ከፊሎቹ የሚከተሉት ናቸው፤
– የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ አዛዦች ከመጭው ሰኞ ጀምሮ በሰባት ቀናት ውስጥ ለወታደራዊ ኃይሎቻቸው ገለጻ ለማድረግ፣
– ከወታደራዊ አዛዦች ገለጻ በኋላ፣ በትግራይ በአራት የተለያዩ ቀጠናዎች በአራት ቀናት ውስጥ ኃይሎቻቸው ግጭት እንዲያቆሙ፣
– ይህንኑ ተከትሎ ፌደራል መንግሥቱ በሁሉም የትግራይ ክልል አካባቢዎች ላይ ሥልጣኑን እንዲያረጋግጥ፣
– የውጭ ኃይሎች እና ከመከላከያ ሠራዊት ውጭ ያሉ ሌሎች ታጣቂዎች ከክልሉ እንዲወጡ ሲደረግ ጎን ለጎን፣ ከሕወሃት ኃይሎች ከባድ የጦር መሳሪያ ትጥቆችን የማስፈታት ሂደት እንዲጀመር፣
– ዛሬ የጋራ መግለጫ ስምምነቱ በተፈረመበት ዕለት የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች የሚያቋቁሙት ከሁለቱ ወገኖች ሁለት ሁለት አባላትና ከአፍሪካ ኅብረት አንድ ተወካይ ያለው የጋራ ኮሚቴ፣ ቀላል የጦር መሳሪያዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ዝርዝር ዕቅድ አውጥቶ በ14 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ
ሁለቱ ወገኖች የተስማሙባቸው ተጨማሪ ጉዳዮች-
– ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን ለማስቆም፣
– ሰላማዊ ሰዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል፣
– ሲቪሎችን ከጸጥታ ኃይሎች ጥቃት ለመጠበቅ፣
– የሲቪል ተቋማትን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና
– ይህን አንቀጽ ጥሶ የተገኘ አካል ቅጣት እንዲጣልበት
– የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍሰትን ለማቀላጠፍ እና በዕርዳታ አቅርቦት ላይ ለመተባበር፣
– ወደ ትግራይ ክልል የሚገባ ሰብዓዊ ዕርዳታ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥርና ፍተሻ ውስጥ እንዲያልፍ፣
– ረድሬት ድርጅቶች ጥያቄ ሲያቀርቡ ለሠራተኞቻቸው የደኅንነት ዋስትና ለመስጠት፣
– በዕርዳታ ካሚዮኖች ላይ ከመነሻቸውና መድረሻቸው ላይ ብቻ ሁለት የፍተሻ ጣቢያዎች እንዲኖር ፣
– ከአፍሪካ ኅብረት የስምምነቱ አፈጻጸም ተቆጣጣሪ ቡድን ጋር ለመተባበር፣
– የአፍሪካ ኅብረት የስምምነቱ ተቆጣጣሪ ቡድኑ ስምምነቱ በተፈረመ በ10 ቀናት ውስጥ ሥራውን እንዲጀምር እና
– ለተቆጣጣሪ ቡድኑ የደኅንነት ዋስትና የሚሰጠው መከላከያ ሠራዊት እንዲሆን የሚሉት ይገኙበታል።
[ዋዜማ ]