ባለፈው አንድ ዓመት የግድቡን ሕልውና የሚፈታተኑ በርካታ የውስጥ ችግሮች የተከሰቱበት ነበር
ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ድል ያስመዘገበችበትን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ አመት የውሀ ሙሌትን አከናውናለች።የግድቡ ግንባታ በደረሰበት ደረጃ የአባይ ውሀ በአናቱ ላይ ሲሄድ በብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣብያ በቀጥታ በተላለፈ ምስል ተበስሯል። ኢትዮጵያ ላይ በግድቡና በትግራይ ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ አለማቀፍ ጫና የበዛበት አመት እንደመሆኑ የሁለተኛው አመት ሙሌት ለሀገሪቱ ፖለቲካዊም ዲፕሎማሲያዊም ድል ነው።
የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የተያዘው ውሀ በቅርብ ወራት በሁለት ተርባይን የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት የሚያስችለን ነው ብለዋል። ግድቡ በሁለት አመታት በጥቅሉ 18.4 ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ውሀ እንደሚይዝ ከዚህ ቀደም ይፋ የተደረገው የመንግስት እቅድ ያሳያል።የተጠቀሰውን መጠን ውሀ ለመያዝ የግድቡ የመሀል ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር መሆን አለበት።
ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ የሚይዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዚህ በኋላ በጥቅሉ 49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እስኪያከማች በየክረምቱ በተከታታይ እንደሚሞላ መርሀ ግብር ተይዞለታል። ህዳሴ
ግድብ 49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ለመያዝ ቁመቱ ከባህር ጠለል በላይ 625 ሜትር ላይ መድረስ አለበት። ግድቡ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ከዚህ በኋላ ከ 2 እስከ 5 ዓመታትንመታትን ሊፈጅበት እንደሚችል አስቀድሞ የተዘጋጀው የግንባታ ዕቅድ ያመለክታል።
የግድቡ ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 625 ሜትር ከደረሰና ከዚያም ካለፈ በሙሉ አቅሙ ኀይል ማመንጨት የሚችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። የግድቡ ቁመት ግንባታ ተጠናቆ 645 ሜትር ደርሶ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ሲይዝ በክረምት ወራት ከ49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ያለው ውሀ እየተለቀቀ የግድቡ ውሀ 625 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያለውን ደረጃ ይዞ እንዲቀጥል እንደሚደረግ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር ያወጣው እቅድ ያሳያል።
በቀጣዩ ዓመት የሶስተኛው ዙር የውሀ ሙሌትም 10.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ መጠን ያለው ተጨማሪ ውሀ ለመያዝ ታቅዷል።።በእቅድ የተያዘውን የሶስተኛ አመቱን ውሀ ለመያዝም የግድቡ ቁመት 608 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ መሆን አለበት። አራተኛው አመት ላይ የህዳሴው ግድብ ዋናው የመሀል ክፍል ቁመቱ 617 ሜትር ሲሆን ተጨማሪ 10.4 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን ይይዛል። እንዲሁም በአምስተኛ አመት በ625 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ቁመት 10 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን እንዲይዝ ታስቧል።
የህዳሴው ግድብ ከባህር ጠለል በላይ 645 ሜትር ከፍታ ሲኖረው በጥቅሉም 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንደሚይዝ ይጠበቃል።
የሁለተኛው ዙር የውሀ ሙሌት ……..ብዙ ፈተና አልፎ የተከናወነ ነው
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ምእራፍ የውሀ ሙሌት በሁለት አመታት በጥቅሉ 18.4 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን እንዲይዝ ታስቦ ሲሰራ ቆይቷል። ባለፈው አመት የመጀመርያ አመት ሙሌት ሲከናወን ግድቡ 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ነበር የያዘው።ግድቡ ይህን ያክል ውሀ ለመያዝ የመሀሉ ክፍል ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 565 ሜትር መድረስ ነበረበት።የኮንክሪት ሙሌቱም የግድቡን ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 565 ሜትር አድርሶት ስለነበረ የመጀመርያ ምእራፍ የመጀርያ ዙር ውሀ ሙሌት በስኬት ተጠናቋል።
የሁለተኛ አመት ውሀ ሙሌት ወቅት የግድቡ ቁመት 595 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ እንደሚሆንና 13.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውሀ እንደሚይዝም የግንባታ ዕቅዱ ያስረዳል ።ሆኖም የሁለተኛው አመት ሙሌት በብዙ ፈተናዎች የተተበተበና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ነበር። የግድቡ ከፍታ ከታሰበው የቁመት ልክ ለመድረስ የተወሰኑ ሜትሮች ሲቀረው ውሀው በግድቡ አናት እንዲፈስ ተደርጎ የሁለተኛው ዓመት ሙሌት ተበስሯል። የግድቡ ጉድለት ከነበሩት ችግሮችና ሀገሪቱ ካለችበት አስቸጋሪ ፈተና አንፃር ስኬታማ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ለዋዜማ አስረድተዋል።
በሀገሪቱ ስር በሰደደው የውጪ ምንዛሪ ዕጥረት ሳቢያ ሀገሪቱ የግንባታውን አብይ ክፍል ለሚያከናውነው የጣሊያኑ ኩባን ያ ሳሊኒ ኢምፕሪጂሊዮ በወቅቱ ተገቢውን ክፍያ ለመፈፀም የማይቻልበት ደረጃ ተደርሶ ሰንብቷል። ክፍያውን በዩሮ ካልተከፈለው ስራውን ማከናወን እንደሚሳነው የገለፀው ሳሊኒ ስራውን እስከማቋረጥ የሚያስገድ ሁኔታ ላይ ደርሶ እንደነበረም ዋዜማ ከምንጮቿ ስምታለች።
በሌላ በኩል በዚህ አመት ህዳሴ ግድብ በሚገነባበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የነበረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ የትራንስፖርት እክል ፈጥሮ ግብዓት በወቅቱና በበቂ ማቅረብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በቅርቡ በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የችግሩን መጠንና መንግስትም አደናቃፊ እንቅስቃሴዎችን ለመቋቋም የወሰደውን እርምጃ አብራተርዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የነበረው አለማቀፍ ጫና በተለይም አሳሪ የህግ ስምምነት እንድትፈርም ለማስገደድ ሲባል የግብፅ ወዳጅ የሆኑ ሀገራትና ተቋማት ለልማት ስራዎች የተገኘ ብድርን በማዘግየትና በማሰናከል የእጅ ጥምዘዛ ሞክረውባታል። በዚህም ቀላል የማይባል ቃል የተገባ የውጪ ምንዛሪ ሳይመጣ ቀርቷል። የትግራይ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ደግሞ አለማቀፉ ጫና ሀገሪቱ ልትሸከመው የሚከብዳት ሆኖ ቀጥሏል።
ከነዚህ ሁሉ ችግሮች ጋር ግድቡን አሁን ለበቃበት ደረጃ ማድረሱ የሚደነቅ አፈጻጸም ሆኗል። [ዋዜማ ራዲዮ]