ዋዜማ ራዲዮ- ከሰሞኑ በኋይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ወጪው ከ200 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሆን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።
የግድቡ ስራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ የህዳሴው ግድብ ኋይል ማመንጨት መጀመሩ በይፋ በተበሰረበት መርሀ ግብር ላይ እስካሁን ድረስ 163 ቢሊየን ብር ወጭ እንደተደረገበት መናገራቸው አይዘነጋም።
ዋዜማ ራዲዮ ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ባለሙያዎች እንደሰማችውም የህዳሴውን ግድብ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ ከዚህ በኋላ በትንሹ ከ40 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል። በ2003 ዓ.ም የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የተያዘለት 80 ቢሊየን ብር ያህል ሲሆን እስከ ማጠናቀቂያው ተጨማሪ 120 ቢሊየን ብር የሚፈልግ ፕሮጀክት ሆኗል።
የሕዳሴው ግድብ ከተጀመረ በሁዋላ የኋይል ማመንጫ ተርባይኖችን በተመለከ ሶስት ጊዜ የእቅድ ክለሳ የተደረገ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የተርባይኖቹ ቁጥር በመጀመሪያ ዕቅድ ውስጥ ከተያዘው 16 ተርባይን በሶስት እንዲቀንስ ተደርጓል። አሁን ግድቡ 13 ተርባይኖች እንዲኖሩት ተደርጎ እየተገነባ ነው።
ፕሮጀክቱ ሲጀመር የኮንክሪት ግንባታውም የኤሌክትሮ ሜካኒካልና ብረታብረት ስራዎች ለጣልያኑ ሳሊኒ ኢምፕሪጂሎ እንዲሰጥ የነበረውን እቅድ ተለውጦ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የብረት ስራዎችን የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ገና ከተቋቋመ አመት ላልሞላው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) እንዲሰጥ በመደረጉ የወጪና የጊዜ ኪሳራ ማስከተሉን መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል።
በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ኮርፖሬሽኑ የሕዳሴ ግድቡን ኮንትራት ሲነጠቅ ገና የተሳካ የአንድ ተርባይን ገጠማ ሳይደረግ ለፕሮጀክቱ የተያዘውን አጠቃላይ ወጪ 80 ቢሊየን አልፎ 98 ቢሊየን ደርሶ ነበር።የ
ኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የብረታብረት ስራዎች ከሜቴክ ከተነጠቁ በሁዋላ በ2012 ዓ.ም መንግስት ግድቡን በ135 ቢሊየን ብር እንደሚጨርሰው የሚያሳይ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። ሆኖም ግድቡ ከሚኖረው ተርባይኖች ውስጥ 12ቱ ገና ስራ ሳይጀምሩ ወጪው 163 ቢሊየን ብር ደርሷል።
የዋጋ ንረት ለወጪ ጭማሬው አስተዋጽኦ ቢኖረውም በግንባታ ሂደት ያሉ ውስብስብ ችግሮች በዋና ምክንያትነት ተቀምጠዋል። ሜቴክ ከሰራቸው ስራዎች ውስጥ ፈርሰው የተሰሩ የግድቡ ክፍሎች አሉ።
ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያን ያጋጠማት የጸጥታ ችግር ከዚያም የሰሜኑ ጦርነት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ፈተና ሆኖ ቆይቷል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሞኑ የፓርላማ ንግግራቸው ለግድቡ ስራ ግብአቶችን ማጓጓዝ የሰው ህይወትን ያስከፈለ መስዋእትነትን የጠየቀ እንዲሁም ሲሚንቶ የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎችም በጸጥታ ስጋት ምክንያት ፈቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]