PM Abiy Ahmed and GERD engineering team – FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ያለፉትን ሳምንታት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች የማምረት ብቃት ሙከራ የተደረገለትና የተሳካ ውጤት ያስገኘው የሕዳሴው ግድብ ነገ ዕሁድ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

ዋዜማ ከቀናት በፊት እንደዘገበችው፣ በሁለት የኋይል ማመንጫ ተርባይኖች በውሀ የመሞከር ስራ በስኬት የተከናወነ ሲሆን አሁን ግድቡ የመጀመሪያ ዙር የኤሌክትሪክ ኋይል ማመንጨት የሚጀምርበት ዕለት በግድቡ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ይሆናል።


ነገ ይህን የግድቡን ታሪካዊ ምዕራፍ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መንግስት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ተገንዝበናል። በዕለቱ በግድቡ ስፍራ የተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩም ታውቋል።


የግድቡ ግንባታና ውሀ የመያዝ ሂደት በቀጣዮቹ ዓመታትም የሚቀጥል ሲሆን በግድቡ ዙሪያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር የሚደረገው ድርድርም አዲስ ገፅታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። በተለያዩ አደራዳሪዎች ለዓመታት የዘለቀው ውይይት ዕልባት ሳያገኝ በእንጥልጥል ይገኛል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2012 አ.ም እና 2013 አ.ም ሁለት ክረምቶች ለተከታታይ ጊዜ ውሀ ይዟል። በ2012 አ.ም ክረምት የግድቡ ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 565 ሜትር ላይ ደርሶ 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የያዘ ሲሆን ባለፈው አመት ክረምት ደግሞ መንግስት የግድቡን ቁመት እና የያዘውን ተጨማሪ ውሀ በቁጥር ባይገልፅም የውሀ ሙሌቱ የተሳካ እንደነበር አስታውቋል።

ባለፈው አመት ግድቡ ቁመቱ 595 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ መድረስ እንደሚጠበቅበት እና የሚይዘው ተጨማሪ ውሀም 13.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን የግድቡ የግባታ እቅድ ያሳያል። ሆኖም ሀገሪቱ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር የግድቡ ግንባታ እቅድ መሳካቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ቢኖሩም ህዳሴው ግድብ በሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ሀይልን ማመንጨት እንደሚያስችለው ግን ማረጋገጥ ተችሏል።

ግንባታው ከተጀመረ 11 አመታት ሊደፍን ቀናት በቀሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ሲደረግ የነበረው ድርድር በአፍሪካ ህብረት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ግብጽና ሱዳን በውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ ስምምነት ይፈረምልን በማለታቸው ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ አይነቱ ስምምነት ጥቅሜን ይጎዳል በማለቷ ድርድሩ ሳይቋጭ ቀርቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]