ዋዜማ ራዲዮ- የቀድሞው የኢሕአዴግ የረጅም ጊዜ ውጭ ግንኙነት ሃላፊ ሴኮቱሬ ጌታቸዉ እና የቀድሞ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት በሪሁን ተወልደ ብርሃን ከድምጸ ወያነ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ህወሐት እያካሄደ ያለው ውጊያ ዐላማ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ እንደሆነ ገልጸዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ደብረፂዮን ገብረሚካዔል በዚህ ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ የውጊያው አላማ በህልውናችን ላይ የተቃጣብንን አደጋ መመከትና ራሳችንን መከላከል ነው ብለው ነበር።

ጦርነቱም በትግራይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚስፋፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ፌደራል መንግሥቱ በመቀሌ ከተማ መሰቦ አካባቢ ትናንት የፈጸመው የአየር ድብደባ ከቀድሞዎቹ ሁለት ሥርዓቶች ቀጥሎ በከተማዋ የተደረገ ሦስተኛው ድብደባ ነው ያሉት ሁለቱ ግለሰቦች፣ ድርጊቱ በዐለማቀፍ የጦር ወንጀል ያስጠይቃል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ላይ በኦሮሚያ ክልል የሚታይ ሕዝባዊ እንቢተኝነት መኖሩን እና ይህም በቀሩት የሀገራችን አካባቢዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድዋል።

መንግሥት በወለጋ እና በደቡብ አካባቢ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ለማንቀሳቀስ ያደረገውን ሙከራ የአካባቢው ሕዝብ ተቃውሞታል በማለትም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ስግብግብ ጁንታ” ያሉት የህወሐት ቡድን በመላ ሀገሪቱ ስውር ቡድኖችን በማደራጀት የብሄርና በሀይማኖት ግጭት በመቀስቀስ ሀገር ለማፍረስ ተሰማርቷል ሲሉ ከሰውታል።


በተለይም በህወሐት እና ኦነግ ሸኔ መካከል በቅንጅት የሚደረግ ተደጋጋሚ ሀገር የማተራመስ እንቅስቃሴ ስለመኖሩ መንግስት መረጃ አለኝ ብሏል። [ዋዜማ ራዲዮ]