ዋዜማ ራዲዮ- በሶስት አዳዲስ ዳኞች የተሰየመው የፌደራሉ ከፍተና ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሀመድ (አብዲ ኢሌ)፣ የክልሉ የቀድሞ ሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ የነበሩትን ወ/ሮ ረሀማ እና በክስ መዝገቡ የተካተቱ ሌሎች 47 ግለሰበችን ጉዳይ ተመልክቷል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥር 20 2011 ዓም በመሰረተው ክስ የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 47 ግለሰቦች በክልሉ በተለያዩ ስብሰባዎች እና በፌስቡክ ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት አብያተ ክርስትያናት መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ተጠያቂ ናቸው ማለቱ ይታወሳል፡፡
ከ47ቱ ውስጥ 15ቱ በችሎት የቀረቡ እና 7 እስካሁን እየተፈለጉ ያሉ ተከሳሾ ያሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ችሎቱ ከዚህ ቀደም ወስኖ ነበር፡፡
ረቡዕ ጥቅምት 19 ችሎቱ ሲሰየም የአቶ አብዲ ሞሀመድን የእምነት ክህደት ቃል የተቀበለ ሲሆን ተከሳሹ ወንጀሉን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ካሉ በኋላ በዝርዝር ሀሳባቸውን እንዲገልፁ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡
ችሎቱ ፈፅሜያለው ወይም አልፈፀምኩም የሚለውን ብቻ ለጊዜው ግለፁ ያላቸው ቢሆንም ጠበቆች የደምበኛቸው ሀሳብን የመግለፅ መብት እንዲከበር መጠየቃቸውን ተከትሎ አቶ አብዲ አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡
በቀዳሚነት የተከሰሱበትን ጉዳይ በመጥቀስ የጀመሩት አቶ አብዲ እኔ ከ10 አመት በፊት ይህን ክልል ለማስተዳደር ስረከብ እዛ ያሉ ክርስቲያኖች እንኳን የሀይማኖት በዓል በአደባባይ ሊያከብሩ ቀርቶ በየቤታቸውም አያከብሩም ነበር ታቦት እንኳን በመከላከያ ታጅቦ ነበር የሚወጣው ብለዋል፡፡
ቀጥለውም ” ለክልሉ ያለው ሁለት አማራጭ ወይ እንደዳርፉር የዩኤን ሰላም አስከባሪ ማስገባት ወይም ደግሞ የፌደራል መንግስት እንዲያስተዳድረው ማድረግ ነበር ፤ ነገር ግን እንደ አንድ አመራር ማድረግ ያለብኝን ቀን ከሌሊት ሰርቼ በእኔ ጊዜ የእምነት ነፃነት እንዲኖር አድርጊያለሁ፣ በክልሉ የነበረውን ነገር ፍራቻ ሸሽተው የነበሩ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ሰርቻለው ፣ ተከብሮ የማያውቀው የመስቀል እና የደመራ በዓል እንዲከበር አድርጊያለው ለዚህ ደግሞ የሶማሌ ህዝብ ምስክሬ ነው” ብለዋል፡፡
አቶ አብዲ አክለውም “እንደአጋጣሚ ሆኖ ግን ከ2008 ዓም ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ ከተሰተው የፖለቲካ ምስቅልቅል ጋር ተያይዞ ብዙ ክልሎች ላይ እንደተፈጠረው ያለ ችግር ሶማሌ ክልል ላይ ተፈጠረ፣ አሁንም በተለያዩ ክልሎች ግድያ አለ መፈናቀል አለ ቤተክርስቲያንም እየተቃጠለ ነው ፣ ሀምሌ 26ትም ሶማሌ ክልል ላይ ይሄው ነው፡፡ የተከሰተው እኔ እንኳን እንዲህ ላደርግ በወቅቱ የተሰማኝን ሀዘን በቦታው ቤተክርሲያንም ሄጄ ገልጫለው” ብለዋል፡፡
“እኔ የተባለውን ወንጀል አልፈፀምኩም፣ ተያዘ ተብሎ የተወራውም ትክክል አይደለም ፡፡ እኔ በህግ ትፈለጋለህ ስባል ራሴ ነኝ ደውዬ የት ልምጣ ያልኩት፡፡ የምመራው የፀጥታ አካል እያለ ብቻዬን ነው ና የተባልኩበት ቦታ የየሄድኩት፡፡ ነገር ግን ይህን የሚያውቁ የመንግስት አካላት ዝም ማለታቸው አግባብ አይደለም ፡፡ ነገ በእነሱ ላይም እንደሚደርስ ሊያስቡት ይገባል” ብለዋል፡፡
አቶ አብዲ አጠቃለውም “እኔ ይህን የምናገረው የክልሉ ህዝብ እውነታውን እንዲረዳ ነው፡፡ ሀይል የፈጣሪ መሆኑን አምናለው፡፡ ፍትህ የምጠብቀውም ከአላህ ብቻ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አንድ ቀን እውነታውን ይረዳል” ብለዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]