(ዋዜማ ራዲዮ)-አቤል ተስፋዬ የሚለውን ስሙን የዛሬ አምስት ዓመት የሚያውቁት ምናልባት ቤተሰቦቹና ጥቂት ጓደኞቹ ብቻ ሳይኾኑ አይቀሩም። አቤል መኮንን ተስፋዬ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 16፣1990 በቶሮንቶ ፤ካናዳ የተወለደ ሲሆን በአያቱ እጅ ስላደገ አማርኛን አቀላጥፎ ይናገራል፡፡
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ ግን ማንነቱን ሳይገልጽ The Weeknd በሚል ስም ዩቱብ ላይ በጫናቸው የሙዚቃ ስራዎቹ የታዋቂነትንና የዝናን መሰላል ቀስ በቀስ እየተረማመደ ድንገት ከዝነኝነት ጫፍ ላይ ተገኘ። ያም ኾኖ “ይህ ልጅ ማነው?” የሚለው ጥያቄ ግን ዝነኛ ኾኖም አልቀረለትም። እስካሁንም ይጠየቃል።
የአቤል ተስፋዬን ድምፅ አልባ ዝና ተንተርሶ መዝገቡ ሀይሉ ያሰናዳውን ዘገባ እነሆ
ዝነኝነትና መደበቅ አብረው የማይሔዱ ቢመስልም አቤል ግን በራሱ መንገድ ሁለቱን አቻችሎ እስካሁን ዘልቋል። የፖፑ ከያኒ አቤል ተስፋዬ ወይም The Weeknd አሁንም ቢኾን የታዋቂ ሰዎችን ኑሮ የጥበብ ስራቸውን ያህል ለሚከታተሉ ሰዎች የማይጨበጥ ኾኖባቸዋል።
ዋነኛው ራሱን የሚደብቅበት መንገድ ደግሞ መገናኛ ብዙኃንን አለማናገሩ ነው። እስከዛሬ ድረስ ብዙም ቃለ መጠይቅ አድርጎ የማያውቀው አቤል አሁንም ቢኾን ይህን አቋሙን የሚያስለውጠው ምክንያት የተገኘ አይመስልም። ባለፈው የፈረንጆች ዓመት “ሮሊንግ ስቶን” ለሚባለው መጽሔት ከሰጠው ዘርዘር ያለ ቃለ መጠይቅ በቀር አቤል ስለራሱ የሚናገረው ነገር ብዙም አይገኝም። ሲቢሲ የተሰኘው የካናዳ ሬዲዮም ይህን ክፍተት ለመሙላት በማሰብ በሚመስል መልኩ ከአቤል ጋር ቃለ መጠይቅ በማድረግ ብቸኛዋ ካናዳዊት ጋዜጠኛ እንደ ኾነች ከሚነገርላት ከአኑፓ ሚስትሪ ጋር ቃለመጠይቅ በማድረግ ስለ አቤል አነጋግሯታል።
ከ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን እናት እና አባቱ በቶሮንቶ ከተማ፤ ካናዳ የተወለደው አቤል ተስፋዬ አስተዳደጉም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ይመስላል። በአማርኛ አፉን መፍታቱና በልጅነቱ ከአያቱ ጋር ቤተክርስትያን እየሔደ ያስቀድስ እንደ ነበረም ስለልጅነት ታሪኩ የጻፉ ይጠቁማሉ። ቤተሰቡ ውስጥ እየሰማ ያደገው የኢትዮጵያ ሙዚቃም አፉን የፈታበት የሙዚቃ ቋንቋም ተደርጎ ሲቀርብ ይሰማል። የትዝታ እንጉርጉሮና የአስቴር አወቀ ስርቅርቅታ በአቤል ዜማዎች ውስጥ አስተዋጽዖ እንዳላቸው እዚህም እዚያም በተነገሩ ቁርጥራጭ ታሪኮቹ ውስጥ ሲጠቀሱ ይሰማል። ያም ኾኖ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አቤልም ሙዚቃውም እንግዳ ናቸው።
“The Hills” የተሰኘ ዘፈኑን በአንድ ወቅት ከታዋቂዋ ከኒኪ ሚናዥ ጋር በሌላ ጊዜ ደግሞ ከ አሊሽያ ኪይስ ጋር በመድረክ ባቀረበበት ጊዜ የቀላቀላቸው የአማርኛ እንጉርጉሮዎች በመጠኑ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከመታየታቸው በቀር በዓለም ዝነኛ የኾነው አቤል በኢትዮጵያ ብዙም የታወቀ አይመስልም። ይህ የሙዚቃ ስራ በተለያዩ ሰዎች ወደ ዩቱብ ቻናል የተጫነ ሲሆን አንዱ ቻናል ከ 602 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል፡፡ በቅርቡ “Fifty Shades of Grey” ለተሰኘው ፊልም ማጀቢያ ኾኖ የቀረበው “earned it” የተባለው ዘፈኑ ለኦስካር ሽልማት ሲታጭና ከዚያም ጥቂት ቀደም ብሎ በሌሎች የሙዚቃ ሽልማቶች ምክንያት ዝናው ሲወጣ በጥቂቱም ቢኾን “ልጃችን” የሚል ቅጽል ሲሰጠውና ኢትዮጵያዊነቱ እየጎላ ሲነገር መሰማት ጀምሯል። ይህ ሙዚቃ በዩቱብ ብቻ ወደ 178 ሚሊዮን ጊዜ ተጎብኝቷል ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአቤል ታዋቂነት የሚገለጽባቸው አድናቆቶች በድንገት እዚህ ደረጃ ለደረሰ ለማንኛውም ከያኒ እንደ ስኬት የሚቆጠር ትልቅ ማዕርግ ነው። ከቦክስ ኦፊስ የደረጃ ሰንጠረዥ ክብሩና ከሽልማቶቹ ጎን ለጎን በንግግር የሚሰጡት አድናቆቶች አስገራሚ ናቸው። “ማይክል ጃክሰን አልሞተም” ወይም “አዲሱ ማይክል ጃክሰን አቤል ይኾን?”፣ “አዲሱ የ RnB ገጽ”፣ “”የሙዚቃን ታሪክ የቀየረ” የሚሉት አባባሎች ምን ያህል ትልቅ ስፍራ እንደተሰጠው የሚያሳይ ነው። ከሁሉም ይልቅ አስገራሚ የኾነው አባባል ግን “the best thing that has happened to music” ወይም “ለሙዚቃ የተበረከተ ትልቁ ስጦታ” የሚለው አባባል ነው። እነኚህ አባባሎች ምንም ያህል የተጋነኑ ቢኾኑ እንኳን አንድ ነገር ማሳየታቸው ግን ግልጽ ነው። አቤል ምን ያህል እንደተወደደና ምን ያህል ትልቅ ስፍራ እንዳገኘ የሚያሳዩ ናቸው።
በአንድ ወቅት ያለ ድምጽ አስመስሎ በመዝፈን ውድድር ላይ ቀርቦ የነበረው ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ቶም ክሩዝ አስመስሎ ለመጫወት የመረጠው የ አቤልን “I cant feel my face” የተባለ ዘፈን ነበር። ቶም ክሩዝ ይህን ዘፈን ለምን እንደመረጠው ቀድሞ ባደረገው ማብራርያ ላይ ምን ያህል አቤልን እንደሚያደንቀው ሲናገር ተሰምቷል። ችግሩ እንደ ብዙ የአቤል አድናቂዎች ቶም ክሩዝም የዘፈኑን ይዘት የተረዳው አለመምሰሉ ነው። ቶም ክሩዝ የዚህን ዘፈን ይዘት ቢረዳው ኖሮ ባለው ስብዕና ምክንያት ይህን ዘፈን አይመርጠውም ነበር የሚሉ ተቺዎችም እንዲነሱበት ምክንያት ኾኖም ነበር።
አቤልን ልጃችን እያሉ ማድነቅ የሚቃጣቸው ኢትዮጵያውያንም እንደ ቶም ክሩዝ ሁሉ የዘፈኖቹን ግጥሞች ይዘት ቢያጤኗቸው ይቀበሏቸው ይኾን የሚለው ጥያቄ እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ይመስላል። የአቤል ዘፈኖች ከለስላሳ ጥዑመ ዜማቸውና ልብ ከሚያሞቀው ምታቸው በስተጀርባ የያዟቸው መልዕክቶች እንኳን ለሐይማኖታዊ ሥነ ምግባር ትልቅ ስፍራ በሚሰጥበት በኢትዮጵያ ይቅርና ሆሊዉድ አካባቢም ቢኾን አነጋጋሪ ናቸው። ቶም ክሩዝ ያቀነቀነው “I cant feel my face” የሚለው ዘፈንም የፍቅር ዘፈን አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ሲተረጉሙት እንደነበረውም ከሳቅ ብዛት የሚመጣ የፊት መደንዘዝንም አያመለክትም። የአቤል ዘፈን ከዚህ ይልቅ የሚያወድሰው በኮኬይን የመደንዘዝን ስሜት ነው።
አብዛኞቹ ዘፈኖቹም ከዚህ የሚርቁ አይደሉም። አቤል ስለኮኬይን ባይዘፍን ስለ ልቅ ወሲብ ይዘፍናል። የአቤልን ሙዚቃ የሚዘግቡት ታዛቢዎች ሁሉ ይህን የአቤልን ዘፈኖች ልዩ ባህርይ ከሙዚቃ ችሎታው እኩል ሲያነሱት ይታያል። ዘፈኖቹም ኾነ የመድረክ ንግግሮቹ ሊቆጣጠረው በማይችል መልኩ በጸያፍ ቃላትና በወሲብ ገለጻ የተሞሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት የአቤል ዘፈን ይህንኑ ያህል አነጋጋሪ ለነበረው “Fifty Shades of Grey” ፊልም ማጀቢያነት መመረጡም የሚያስደንቅ ሊኾን አይችልም።
አቤል ከኢትዮጵያ የሙዚቃም ይኹን አጠቃላይ ባሕል የሚያዛምደው የሚመስለው ነገር ቢኖር የዘፈኖቹ የተለየ ቅላጼ ነው። ከዚያ አልፎ ግን እንደ ኢትዮጵያ ዘፈኖች እንኳን የስነ ምግባር ሰባኪ በኾኑባት አገር የአቤል ግጥሞች ተቀባይነት ማግኘታቸው አጠያያቂ ሳይኾን አይቀርም።