Photo- AA City Administration page

ዋዜማ- የከተማ ማስዋብና የኮሪደር ልማት ግንባታን ተከትሎ የአዲስ አበባ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ቅጣቶችን አሻሽሎ ማውጣቱንና ይህን የሚያስፈፅሙ ስድስት ሺህ ደንብ አስከባሪዎችን ማሰማራቱን ዋዜማ ተረድታለች። 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለዋዜማ እንደተናገሩት በጽዳትና ተያያዥ ህገ-ወጥ ተግባራት ዙሪያ ቀድሞ ሲጠቀምበት የነበረው ደንብ ቁጥር 150/2015 ተሻሽሎ ጠንከር ያለ ቅጣት የሚጥለው አዲሱ ደንብ ከሰኔ ወር ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።

የቀደመው ደንብ የወጣው ባለፈው ዓመት ነበር።

ለአብነትም በመንገድ ላይ የተተከሉ የዘንባባ ዛፎች “በውድ የተገዙ እና ብርቅዬ በመሆናቸው”  ዛፎቹ ላይ ጉዳት ያደረሰ ግለሰብ እስከ 300 ሺ ብር እንደሚቀጣ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ነግረውናል።

ደንቡ ተግባራዊ መረደግ ከጀመረ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ቅጣቱ የተጣለባቸው ግለሰቦች መኖራቸውንም ሀላፊው ተናግረዋል።

ዋዜማ የተመለከተችው በከንቲባ አዳነች አቤቤ ተፈርሞ የወጣው ደንብ፣ ከሰኔ 10 2016ዓም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን መኪና ባልተፈቀደ ቦታ በማጠብ ወይም በማሳጠብ አካባቢው እንዲቆሽሽ ያደረገ ማንኛውም ሰው ማለትም መኪናውን ያጠበ 2000 ብር እንዲሁም ያሳጠበ 20 ሺህ ብር ይቀጣል።

የመኖሪያ ቤት ቆሻሻ ማዝረክረክ 2000 ብር፣ የድርጅት 50ሺ ብር፣ እንደሚያስቀጣ እና ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ የጣሉትን ቆሻሻ በማንሳት ማጽዳት ግዴታ እንደሆነ ይገልጻል።

ከመፀዳጃ ቤት ውጭ በማንኛውም ቦታ ሽንት መሽናት ወይም መጸዳዳት 2ሺ ብር ፣ማንኛውም በመንገድ የሚንቀሳቀስ ሰው የሲጋራ ቁርጥራጭ፣ የሶፍት ወረቀት፣ ፌስታል፣ የጫት ገረባ፣ የትራንስፖርት ቲኬት፣ የሞባይል ካርዶችን፣ የማስቲካና ከረሜላ ሽፋኖች፣ የመሳሰሉት ጥቃቅን ደረቅ ቆሻሻን ባልተፈቀደ ቦታ፣ በፓርኮች፣ በአረንጓዴ ቦታ፣ በኮሪደር መሰረተ ልማቶች፣ በመናፈሻ ቦታ፣ በሕዝብ መናፈሻ፣ በመንገድ መናፈሻ፣ በመንገድ፣ በመንገድ አካፋይ፣ በመንገድ ዳርቻ፣ በአደባባይ፣ በፕላዛ ቦታ ፣ የመንገድ ቱቦ፤ ድልድይ ውስጥ፤ በክፍት ቦታ በመሳሰሉት ላይ ከጣለ 2ሺ ብር በመቀጣት የተጣለውን ቆሻሻ በማንሳት ማጽዳት ይጠበቅበታል።

በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት ተመሳሳይ ቦታዎች ቄጠማ፤ ሳር፤ የበቆሎ ሽፋን ወይም ቆረቆንዳ፤ ጭድ፤ ሸንኮራ አገዳ፤ የሽንብራና የባቄላ እሸት ገለባ፤ የፍራፍሬ ልጣጭ እና የመሳሰሉት ሲሸጥ አካባቢውን ያቆሸሸ ወይም ግብዓቱን ተጠቅሞ ተረፈ ምርቱን የጣለ ማንኛውም ሰው 5ሺ ብር ቅጣት ተጥሎበታል።

ወቅታዊና ልዪ ዝግጅት አከናውኖ በአሉ ሲጠናቀቅ በእለቱ ወድያው አካባቢን ያላጸዳ 50ሺ ብር እንዲሁም አመታዊ፣ ወርሀዊና ሳምንታዊ የእምነት በአላት አከናውኖ ሲያጠናቅቅ አካባቢውን ካላፀዳ 20ሺ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል።

በደንቡ ላይ የተጠቀሱትን ቅጣቶች የሚያስፈጽሙ 6ሺ100 ደንብ አስከባሪዎች መሰማራታቸውንም ተረድተናል።

ጥፋት ፈፅመው የቅጣት ገንዘቡን የመክፈል አቅም እንደሌላቸው የተረጋገጠ ከሆነ በምትኩ አካባቢ በማፅዳት ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ (ስፖርት) በማድረግ ቅጣቱ ይካካስላቸዋል።

ቋሚ አድራሻ የሌላቸው ደግሞ ከፖሊስ ጋር በሚደረግ ትብ ብር ቅጣቱን እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ደንቡ ያትታል።

በደንቡ መሰረት ተጠሪነቱ ለሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስተዳደር ለሆነው የደንብ ማስከበር ባለስልጣን በባለቤትነት በመቆጣጠር ወደ ክፍለከተማ እና ወረዳዎች በማወረድ እንዲተገብር ያደርጋል።

በደንቡ መሰረት በቅጣቱ ወቅት የተያያዙ ንብረቶች በጨረታ ወይም ወድያውኑ በመሸጥ የሚወገዱ ሲሆን በቅጣት ሂደት ላይ ለመቀጣት ፈቃደኛ ያልሆነ ግለሰብን በፍርድቤት በመክሰስ ክስ መመስረት እንዲሁም የቅጣቱን እጥፍ ክፍያ እንዲከፍል እንደሚደረግ ይገልጻል።

ደንቡ የተሻሻለው በአዲስ አበባ ከተማ ክፍት የተደረጉ አምስት የኮርደር ልማት ቦታዎች በአግባቡ መጠቀም እና ጉዳት እንዳይደርስ መጠንቀቅ በማስፈለጉ ነው ተብሏል።[ዋዜማ]