የኬንያ መንግስት ግማሽ ሚሊዮን ያህል የጎረቤት ሀገር ስደተኞችን ያስጠለለባቸው ግዙፎቹን ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ባንድ ዓመት ውስጥ ለመዝጋት የወሰነው ባለፈው ወር ነው፡፡ ከዚህ ውሳኔ በኋላ አዲስ ሱማሊያዊያን ስደተኞችን እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል፡፡ መንግስት መጠለያ ጣቢያዎቹ ለአልሸባብ ሽብርተኞች መፈልፈያ ሆነዋል የሚል መከራከሪያ ያቀርባል፡፡
በመቶሺዎች የሚቆጠሩትን ስደተኞች ያለ ፍቃዳቸው ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ውሳኔ ግን ዓለም ዓቀፍ ውግዘት ገጥሞታል፡፡ የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ በዕርዳታ ለጋሽ ምዕራባዊያን ውሳኔውን እንዲቀለብስ ቢለመንም “ከዚህ በኋላ በቃኝ!” ብሏል፡፡ በተለይ ከቀናት በኋላ ነሃሴ ላይ ጠቅላላ ምርጫ የምታካሂደው ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ወደ ናይሮቢ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ባደረጉት ውይይት ሀገራቸው ተመላሽ ስደተኞችን ለመቀበል መዘጋጀቷን መገልፃቸው ለናይሮቢ የልብ ልብ ሰጥቶታል፡፡
ግዙፎቹን ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ከናካቴው ዘግቶ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ከብሄራዊ ደህንነት፣ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ሰብዓዊ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ጋር የተቆራኙ በርካታ አንድምታዎች አሉት፡፡ ለመሆኑ የኬንያ መንግስት ካምፖቹን ለመዝጋት የሚያቀርበው መከራከሪያ አሳማኝ ነውን? የካምፖቹ መዘጋት ለኬንያ ብሄራዊ ደህንነት ምን ዓይነት ትሩፋቶችና መዘዞች ያመጣ ይሆን? መንግስት ከፀረ–ሽብር ስትራቴጂ ሌላ የተለየ ምክንያት ይኖረው ይሆን? የሚሉት ጥያቄዎች ትኩረት የሚስቡ ሆነዋል፡፡
[ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ አለው፡ በድምፅ የተዘጋጀውን ያድምጡ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]
“መጠለያ ጣቢያዎቹ ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ስለሆናቸው የአካባቢ መራቆት አስከትለውብኛል፤ ወደፊትም የተፈጥሮ ሃብት መመናመኑ የጎሳ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል” በማለት የኬኒያ መንግስት ለመዝጋቱ ምክንያት የሚለውን ይናገራል፡፡ መከራከሪያው የተፈጥሮ ሃብት በተለይም መሬት በኬንያዊያን ስነልቦና ውስጥ ልዩ ስፍራ ያለው መሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል፡፡ የአሜሪካ መንግስት የኬንያን አየር ክልል በአደገኛ ቀጠናነት መፈረጁንም እንደ ቆስቋሽ ምክንያት የሚጠቅሱ ታዛቢዎች አሉ፡፡
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ አልሸባብ በኬንያ ብሄራዊ ደህንነት ላይ ግልፅና ቀጥተኛ አደጋ መደቀኑ አሌ የማይባል ነው፡፡ መንግስት ከአልሸባብ ጋር በሁለት ግንባር እየተፋለመ ይገኛል፤ ሱማሊያ ውስጥ እና ሀገሩ ውስጥ፡፡ አልሸባብ ከሦስት ዓመታት በፊት በናይሮቢው ዌስትጌት የገበያ ማዕከል ላይ ባደረሰው ሽብር ጥቃት ከ60 በላይ ንፁን ዜጎች ተገድለዋል፡፡ ታች አምና ደሞ በሰሜናዊ ኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ከ140 በላይ ንፁሃን አልቀዋል፡፡ በእርግጥም ጥቃቶቹ ከኬንያዊያን አዕምሮ በቀላሉ የሚጠፉ አይደሉም፡፡
እዚህ ላይ ግን አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል፡፡ ጥቃቶቹ ከመጠለያ ጣቢያዎቹ ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ትስስር አላቸው ወይ? የሚል ፡፡ ዓለም ኣቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤትና ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት ግን መንግስት ሽብር ፈፃሚዎቹ ከስደተኛ ካምፖች ጋር ቁርኝት ያላቸው ስለመሆኑ ወይም ካምፖቹ የሽብርተኞች መፈልፈያ ምሽግ ስለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የለውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ መንግስትም የመከራከሪያውን እውነታነት የሚያሳይ ምንም አስተማማኝ ማስረጃ አቅርቦ አያውቅም፡፡ ባለፈው ግንቦት መጨረሻ ቱርክ ኢስታንቡል በስደተኞች ላይ በተወያየው ዓለም ዓቀፍ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የኬኒያ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ዊሊያም ሩቶ የ2013ቱ የዌስትጌት ገበያ ማዕከልም ሆነ የታች አምናው የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ጥቃቶች በስደተኛ ካምፖች ውስጥ የተጠነሰሱ ናቸው ቢሉም ማስረጃ ግን አላቀረቡም፡፡
ከራሱ ከኬንያ መንግስት የሚወጡ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ግን የእስካሁኖቹ ሽብር ጥቃት ፈፃሚዎቹ ሀገር–በቀል ሱማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኬንያዊያን ዜጎች እንጂ ከስደተኛ ካምፕ የተመለመሉ ወይም ትስስር ያላቸው አለመሆናቸውን ነው፡፡ በጋሪሳ ዩኒቨርስቲና ዌስትጌት ገበያ ማዕከል ላይ የደረሱት ሽብር ጥቃቶችም የተቀናበሩትም ሆነ የተፈፀሙት በሀገር በቀልና ዓለም ዓቀፍ ሽብርተኞች መሆኑ የመንግስት መከራከሪያን ውሃ እንዳያነሳ አድርጎታል፡፡ ከቀናት በፊት ሱማሊያ ውስጥ የተገደለው የጋሪሳው ጥቃት አቀነባባሪ ሞሃመድ ኩኖ የኬንያ ሱማሌ ተወላጅ ነው፡፡
በሰሜናዊ ምስራቅ የሚኖሩ የኬንያ ሱማሊዎች ከሀገሪቱ ሃብትና ስልጣን ክፍፍል እንዲሁም መሰረተ–ልማቶች በበቂ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ለበርካታ ዓመታት በማዕከላዊው መንግስት ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ሱማሊያዊያን ስደተኞች ደሞ ከኬንያዊያን–ሱማሌዎች ጋር የቋንቋ፣ የጎሳ፣ የባህል እና የሃይማኖት ቁርኝት ያላቸው ናቸው፡፡ ዳዳብ ካምፕ ያረፈበትን አካባቢም እንደ ታላቋ ሱማሊያ ግዛት አድርገው የሚያዩ ሱማሊያዊያን ቀላል አይደሉም፡፡
እነዚህ እውነታዎች ከኬንያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጋር ተዳምረው ሀገር በቀል የአክራሪነት ዝንባሌዎች ስር እንዲሰዱና የሽብር ህዋሶች እንዲፋፉ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል፡፡ ታዛቢዎች በርካታ ሱማሊኛ ተናጋሪዎች ላሏት ሀገር ሱማሊያዊያን ስደተኞችን አስገድዳ መመለሷ ለውስጣዊ አንድነቷና ደህንነቷ አደገኛ ነው የሚሉትም ለዚህ ነው፡፡
በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት አልሸባብ ኬንያ ዕምብርት ላይ ሽብር ጥቃት መፈፀም የቻለው ስደተኛ ካምፖች ምቹ ሁኔታ ፈጥረውለት ሳይሆን ስር የሰደደውን ሙስና እንደ ክፍተት በመጠቀም ጭምር ነው፡፡ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ለዚህ መፍትሄ አድርገው የሚያቀርቡት የፀጥታ ሃይሎችን አወቃቀር መቀየር ቢሆንም በመጭው ዓመት ከሚካሄደው ምርጫ በፌት ለውጥ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
የቀድሞው የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ሚልተን ኦቦቴ በኡጋንዳ ተጠልለው የነበሩትን ሩዋንዳዊያን ስደተኞች ባግባቡ ባለመያዛቸው ባሁኑ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ይመራ የነበረውን አማፂ ኃይል እንዲቀላቀሉ መንገድ እንደጠረጉላቸው በአስረጅነት በመጥቀስ የኡሁሩ ኬንያታ ውሳኔም በራስ ላይ አደጋ መጋበዝ ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ የአልሸባብ ሰርጎገብነትን እንደ ምክንያት ጠቅሶ ካምፕ መዝጋት ለሽብርተኛው አማፂ የፕሮፓጋንዳ ድል ይሆናል በማለት፡፡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በሱማሊያ ማህበራዊ አገልግሎቶችም ሆኑ ፀጥታና የስራ ዕድሎች ባለመኖራቸው ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚፈጠር ሲከራከር ሌሎች ታዛቢዎች ደሞ ተመላሽ ወጣቶች ተስፋ በማጣት ለአልሸባብ መሰረት መስፋት ምቹ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት የውሳኔውን አደገኛነት ያነሳሉ፡፡ ተመላሾቹም በኬንያ ላይ ጥላቻ ላለማሳደራቸው ዋስትና ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡
ናይሮቢ ጦሯን ከአሚሶም ልታስወጣ እንደምትችል በፕሬዝዳንቷ በኩል በቅርቡ ሀገሪቱን ለጎበኘው የፀጥታው ምክር ቤት ልዑካን ተናግራለች፡፡ ይህንን ዛቻ በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ያነሱት በወታደሮቻቸው ላይ የሚፈፀሙት ጥቃቶች ጉዳታቸው በመጨመሩ? በሀገራቸው ላይ ሽብር ጥቃቶች በመደጋገማቸው? ወይስ በምዕራባዊያን ገንዘብ ዕርዳታ እጥረት? የሚሉት ጉዳዮች መወያያ ሆነው ከርመዋል፡፡ መንግስት እንደ ምክንያት የሚያቀርበው አውሮፓ ህብረት ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ለአሚሶም የመደበውን ባጀት በ20 በመቶ መቀነሱን ነው፡፡ የመጠለያ ጣቢያዎቹ መዝጋት ውሳኔ የምዕራባዊያንን እጅ በመጠምዘዝ ተጨማሪ ዕርዳታ ለማግኘት ከሚደረግ ስትራቴጂ ጋር የሚያይዙት ወገኖችም ለአሚሶምም ሆነ ለስደተኞች በቂ ዕርዳታ ከተገኘ ውሳኔውን የማይቀየርበት ምክንያት የለም ይላሉ፡፡ ቱርክ ሶሪያዊያን ስደተኞችን ለምታስተናግድበት ከአውሮፓ ጠቀም ያለ ማካካሻ ዕርዳታ ማግኘቷ ለኬንያ መንግስት ዓይን ገላጭ ሳይሆን አልቀረም፡፡
ከነዚህ ሁሉ መላ ምቶች በተጨማሪ በሌላ በኩል በሱማሊያ ያለው ወታደራዊ ዘመቻ ስኬታማ ባለመሆኑ ሊሆን እንደሚችልም የሚገምቱም አልጠፉም፡፡ በቅርቡ በአሚሶም ስር ያሉ ከመቶ ሃምሳ በላይ የሚሆኑ ኬንያዊያን ወታደሮች በአልሸባብ ጥቃት ተገድለዋል፡፡ ምንም እንኳ የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ትክክለኛውን የሟች ወታደሮቹን ቁጥር እስካሁን ባይገልፅም ገለልተኛ ምንጮች ግን የሟቾቹን ቁጥር ወደ 200 ያደርሱታል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ የኬንያ ወታደሮች በሱማሊያ በህገወጥ ንግድ እንደተሰማሩ የሚያሳዩ የተመድ ሪፖርቶች መውጣታቸው በኬንያ ወታደራዊ ዘመቻ ስኬት ላይ ጥላ አጥልቷል፡፡ በአሚሶም ላይ ከባድ ጥቃቶች ማድረሱን አጠናክሮ የቀጠለው አልሸባብ ከጥቂት ከቀናት በፊትም በኢትዮጵያዊያን ወታደሮች ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ በርካቶችን መግደሉን ዓለም ዓቀፍ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡
ከጅምሩም ኬንያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ያዘመተችው አልሸባብን በማጥፋት በደህንነቷ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ ነበር፡፡ ብዙ የተወራለት የኬንያው “ዘመቻ ሊንዳ ኒቺ” (Operation Linda Nchi) ግቡን ሳይመታ ስደተኞችን መመለስም ሆነ ወታደሮችን ማስወጣት ጋሪውን ከፈረሱ የማስቀደም ያህል አድርገው የሚወስዱት ታዛቢዎች ቀላል አይደሉም፡፡ 3, 600 ወታደሮቹን በታችኛውና መካከለኛው ጁባ ግዛቶች ያሰማራ ሲሆን አውሮፓ ህብረት ለአንድ ኬንያዊ ወታደር በወር አንድ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወርሃዊ ደመወዝ ይከፍላል፡፡ የኬንያ መንግስት ደሞ ከእያንዳንዱ ወታደር 20 በመቶውን ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ተቀናሽ ያደርጋል፡፡
በቅርቡ አይኤስአይኤስ የተሰኘው ዓለም ኣቀፍ አሸባሪ ድርጅት ወደ ሱማሊያ ፊቱን ማዞሩን መግለፁ ሱማሊያ ለኬንያ ብሄራዊ ደህንነት ምን ያህል አደገኛ ሆና እንደምትቀጥል አመላካች ነው፡፡ በቅርቡም የኬንያ ፖሊስ ከአይ.ኤስ.አይ.ኤስ ጋር ግንኙነት ያለው የሽብር መረብ የባዮሎጂካል (አንትራክስ) ሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲያሴር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፆ ነበር፡፡ ኬንያ ከሱማሊያ ጋር ረዥምና ለቁጥጥር የሚያስቸግር ድንበር ስለምትጋራ ሽብርተኞች ከስደተኛ ጣቢያዎች ይልቅ ከሱማሊያ ወደ ኬንያ ሰርጎ ለመግባት አመቺ ሆኖላቸዋል፡፡
እኤአ በ2013 ኬንያ፣ ሱማሊያና የተመድ ስደተኞች ድርጅት ሱማሊያዊያን ስደተኞችን በፍቃደኝነት ለመመለስ የሦስትዮሽ ስምምነት ደርሰው የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሃያ ወራት ውስጥ የተመለሱት 13 ሺህ ያህል ብቻ ናቸው፡፡ ዓለም ዓቀፉ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር በያዝነው ዓመት ብቻ 50 ሺህ ስደተኞችን ለመመለስ ቢያቅድም በቅርቡ ግን በበጀት ዕጥረት ሳቢያ ዕቅዱን ማሳካት እንደማይችል አስታውቋል፡፡ በእርግጥ ሂደቱ አዝጋሚ ቢሆንም በጎ ፍቃደኛ ተመላሾች ወደ ሱማሊየ ገብተዋል፡፡ ትኩረታቸውን በሶሪያዊያን ስደተኞች ላይ ያደረጉት ምዕራባዊያን ለሱማሊያዊያን ስደተኞች ተጨማሪ ባጀት ይመድባሉ የሚለው ግምት እምብዛም ነው፡፡
በጠቅላላው ስደተኛ ካምፖቹን መዝጋት አለመዝጋት በሁለት ታሳቢዎች ማለትም ምዕራባዊያንና ተመድ ለኬንያና አሚሶም በሚሰጡት የገንዘብና ወታደራዊ ዕርዳታ ወይም በአልሸባብ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ላይ የሚመሰረት ይመስላል፡፡