[ዋዜማ ሬዲዮ] የኢትዮጵያና ኬንያ ኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ መገባደድን ተከትሎ ኬንያ በቀጣዮቹ ወራት የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ኀይል ግዥ እንደምትጀምር በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለዋዜማ ነግረዋል።
ከዓመታት በፊት በኬንያ እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ በኢትዮጵያ በኩል እስከ ሁለቱ ሀገሮች ድንበር ድረስ የተከናወነው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ባለፈው ዓመት ተጠናቋል።
በኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል በተደረሰው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት መሠረት ኬንያ በሚቀጥሉት አምስት ወራት ውስጥ ቅድመ ዝግጅቶቿን አጠናቃ የኤሌክትሪክ ግዥ ትጀምራለች ተብሎ ይጠበቃል።።
የኃይል መስመር ዝርጋታው በኢትዮጵያ በኩል ከተጠናቀቀ ዓመት ቢያልፈውም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጩ እስካሁን ድረስ ያልተጀመረው በኬንያ በኩል ዝግጅቶች ስላልተጠናቀቁ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ሞገስ መኮንን ለዋዜማ ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ሽያጩ ሲጀመር፣ ኢትዮጵያ ለኬንያ ከ1 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ኃይል ትሸጣለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ሃላፊው ለዋዜማ ገልጸዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ይህንን የሁለቱን ሀገሮች ጉርብትና የበለጠ የሚያጎለብት ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ በሁለቱ ሀገራት በኩል ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በቀጣዮቹ ወራት የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለመጀመር በኬንያ በኩል ያሉ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ለዋዜማ አረጋግጠዋል።
ከ56 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማያገኝበት ሁኔታ እና በሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት ችግር እያለ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሽያጭ መጀመር ምን ያህል ተገቢ ነው በሚል ላነሳነው ጥያቄ አቶ ሞገስ ሲመልሱ “ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የአገልግሎት እንጅ የኃይል [መጠን] አቅርቦት ችግር የለባትም። ለደንበኖቻችን በሚፈልጉት ልክ ነው ኤሌክትሪክ ኃይል የምናቀርበው” ብለዋል ።
ከ10 ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ ፕሮጀችት አጠቃላይ ወጪው 1.3 ቢሊየን ዶላር ሲሆን፣ ከዓለም ባንክ $684 ሚሊየን ዶላር፣ ከአፍሪቃ ልማት ባንክ 338 ሚሊየን ዶላር ድጋፍና በሁለቱ ሀገራት (ኬንያ 88 ሚሊየን ዶላር ኢትዮጵያ 32 ሚሊየን ዶላር) ወጪ የሚሸፈን ነው።
የኀይል ማስተላለፊያ መስመሩ 1,068 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን በኢትዮጵያ 437 ኪሎ ሜትር በኬንያ ደግሞ 631 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።
ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር ከደረሰችበት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት በተጨማሪ፣ ለጅቡቲ እና ሱዳን ኤሌክትሪክ ኃይል እንደምትሸጥ ይታወቃል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ለጉረቤት ሀገራት ካቀረበችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ውስጥ 90 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷን እና ይህም ገቢ ቀደም ባሉት ዓመታት ይገኝ ከነበረው እጅግ የላቀ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀደም ሲል መግለጹ ይታወሳል። [ዋዜማ ሬዲዮ]