ዋዜማ ራዲዮ- ባለፉት ሶስት ወራት ከፍተኛ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ከዐረብ ሀገራት ወደ ኤርትራ እየገቡ መሆኑን የዋዜማ ምንጮች አመለከቱ።
ምንጮች በማስረጃ እንዳረጋገጡት ከመስከረም ወር ጀምሮ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከዓሰብ ወደብ በስተሰሜን በሚገኝ አካባቢ አምስት ሚራጅ 2000 ተዋጊ አውሮፕላን ፣ሲ-17 ግሎባል ማስተር ወታደራዊ የትራንስፖርት አውሮፕላን፣ ሶስት ቻይና ሰራሽ ሰው አልባ የጥቃት አውሮፕላን ወደ ኤርትራ አስገብታለች።
ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ ከሰላሳ በላይ ታንኮችና ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችም ዓሰብ በሚገኘው ጦር ሰፈር እንደሚገኙ የዋዜማ ምንጮች ከነ-ማስረጃው አረጋግጠውልናል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬት እና ሳዑዲ አረቢያ በየመን ለሚያደርጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ የዓስብ ወደብ አካባቢን ወታደራዊ መርከቦች በማስፈር ለጊዜያዊ የአቅርቦት አገልግሎት እንደሚጠቀሙ ቢገልፁም የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ በተናጠል ከኤርትራ ጋር የረጅም ጊዜ ስምምነት በማድረግ የጦር ሰፈር ግንባታ ጀምራለች።
የጦር ሰፈሩ በደርግ ዘመን የተሰራና አነስተኛ መንደርደሪያ ያለው ሲሆን በቅርብ ወራት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንደርደሪያውን በማስፋፋት በርካታ አውሮፕላኖች የሚያስተናግድና መጠለያ ያለው የጦር ሰፈር እየሆነ ነው።
የግንባታው ስፋት ወታደራዊ ሰፈሩ ለረጅም ጊዜ ታቅዶ እየተሰራ ለመሆን ወታደራዊ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ሳዑዲ አረቢያና ዓረብ ኤምሬትስ የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው ቢሆኑም ሳዑዲ የራሷ ወታደራዊ ይዞታ እንዲኖራት ፍላጎት እንዳላት ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ይናገራሉ።
በጉዳዩ ስጋት የገባው የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞውን ለሁለቱም አረብ ሀገራት የገለፀ ቢሆንም ሰሚ ያገኘ አይመስልም።
ወታደራዊ እንቅስቃሴው በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ባይሆንም በማዕቀብ ስር ለምትገኘው ኤርትራና በዚያ ለሚገኙ ተቃዋሚዎች የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲያገኙ ቀዳዳ ይከፍታል በሚል አዲስ አበባ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ከጀመረች ሰነባብታለች።
ኢትዮጵያ ሳዑዲ ዐረቢያ በጅቡቲ የጦር ሰፈር እንድትከፍት ጅቡቲን በማግባባት ጥሪ ያደረገች ሲሆን ሳዑዲ ከአስር በላይ ሀገሮች በምታስተናግደው ጅቡቲ በቂ ቦታ የለም በሚል ጉዳዩን በይደር ይዛዋለች።
ጅቡቲ ግን ሳዑዲ የጦር ሰፈሯን በጅቡቲ ለመክፈት ተስማምታለች በቅርቡም ስምምነት ይፈረማል ብላለች።
የዐረብ ሀገራቱ ወታደራዊ መስፋፋት በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ የሚቀጥል ቢሆንም ጉዳዩን ለማርገብ ከአዲስ አበባ በኩል ግራ መጋባት መኖሩን በርካታ ታዛቢዎች ይስማማሉ።