- ከአንድ ባንክ ብቻ በአንድ ወር ውስጥ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጥቷል
ዋዜማ – ከቅርብ ወራት ወዲህ ከግል ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው ብር እየወጣ መሆኑን ዋዜማ ሰምታለች። ክስተቱን ተከትሎ አንዳንድ የግል ባንኮች ለደንበኞች በቂ ብድር ለማቅረብ የሚያደፋፍር የገንዘብ መጠን እጃቸው ላይ የለም።
ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነ በሚያዝያ ወር ብቻ ከአንድ ባንክ (የባንኩን ስም የሸሸግነው መልካም ስሙን ላለመጉዳት መሆኑ ይታወቅልን) 6.5 ቢሊየን ብር ወጪ ሆኗል። ከባንኩ የወጣው የብር መጠንም ፣ የወጣውም በአጭር ቀናት መሆኑ በራሱ በባንኩም ሆነ ፣ በሁሉም የግል ባንኮች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል።
የዚሁ ባንክ የመረጃ ምንጫችን እንደነገረን ከሆነ አብዛኛው ብር ከባንኩ ወጥቶ ወደ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው የሄደው። የወጣው የገንዘብ መጠን ባንኩን ግር ከማሰኘቱ ባሻገር ለደንበኞች ብድር ማቅረቡን ጋብ እንዲያደርግ አስገድዶታል።
ከሌሎች ሁለት የግል ባንኮችም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጥቷል ወይንም ወደ መንግታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገብቷል።
የገንዘብ መውጣቱ ችግር ውስጥ የከተታቸው የግል ባንኮች ከሰሞኑ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውርን ዝግ ማድረጋቸውን ተረድተናል።
በዚህም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በርካታ የባንክ ደንበኞች ገንዘባቸውን ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ ለማዘዋወር በእጅጉ መቸገራቸውን አስተውለናል።
አንድ የባንክ ተጠቃሚ ነጋዴ ለዋዜማ እንደተናገሩት ፣ የኮንደሚኒየም የንግድ ቤት ጨረታን አሸንፈው ፣ የጨረታውን ዋጋ አስራ አንድ ሚሊየን ብር ለመንግስት ለመክፈል ከአንድ የግል ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማዘዋወር በጣም ተቸግረው እንደነበር ገልጸውልናል።
ገንዘብ ከግል ባንክ ቅርንጫፎች ለማውጣት ብርቱ ሙግት እንደገጠማቸውም ገልጸውልናል።
ወቅቱ በርካታ ባንኮች ለጥሬ እቃ እና መሰል የስራ ማስኬጃዎች ብድርን የሚያቀርቡበት ቢሆንም ፣ በጥሬ ገንዘብ እጥረት ሳቢያ ብድር መቀዛቀዙም ተነግሯል።
ዋዜማ እንደሚባለው ከግል ባንኮች የወጣው ገንዘብ ወደ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው ወይ የገባው ስትል ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ አንድ የባንኩ የስራ ሀላፊን ጠይቃለች።
ሀላፊውም “ከግል ባንኮች ወጣ የሚባለው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ወደ መንግስታዊው ባንክ መቷል ብዬ መናገር ባልችልም ከቅርብ ወራት ወዲህ የባንካችን የግል ቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ ጥሩ ጭማሪ አሳይቷል። የቁጠባ መጠናችንም ከእቅዳችን አንጻር ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ሆኗል ።” ብለው አጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭም 1 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር መድረሱንም ጠቁመውናል።
ከግል ባንኮች ገንዘብ ሊወጣ የሚችልበት ብቸኛ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ከፍተኛ ገንዘብ አስቀማጭ ነጋዴም ሆነ አምራቾች አሁን ላይ ከግል ባንኮች ይህ ነው የሚባል የውጭ ምንዛሬ እያገኘ ባለመሆኑ ነው ብለውናል ሀላፊው።
ንግድ ባንክ የግል አስቀማጮች መሳብ የቻለው የውጭ ምንዛሪ ለነጋዴዎች ማቅረብ ጀምሮ ነው ወይ ? በሚል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ ሀላፊው ጥያቄ ብናቀርብም በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሆኖም ከሌሎች ምንጮች ለማጣራት ባደረግነው ጥረት የተወሰኑ አምራቾች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከንግድ ባንክ ጥቂት የውጭ ምንዛሪ እንደተለቀቀላቸው መረዳት ችለናል። ከነዚህ ውስጥም አንዱ አምራችም ሁለት ሚሊየን ዶላር እንደተለቀቀለት አጣርተናል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመንግስታዊው ባንክ ዘንድ ቢኖርም በግል ባንኮች ግን ይብሳል።የግል ባንኮች ደንበኞቻቸው ምርት ልከው ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ ሰጥተው ፣ 20 በመቶውን ለደንበኛቸው በማድረግ፣ 10 በመቶውን ብቻ ነው መጠቀም የሚችሉት። ይህ ደግሞ በቂ ደንበኛ በእጃቸው እንዲያቆዩ አያደርጋቸውም። [ዋዜማ]