ዋዜማበአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሰረት ክልላዊ የ6ኛ ክፍል መመዘኛ ፈተና መጀመሩን ተከትሎ የ7ኛ ክፍል ተመዝጋቢ ተማሪዎች፣ ወደ አዲስ አበባ ለመዛወር የመመዘኛ ፈተና የመውሰድ ግዴታ እንደተጣለባቸው ዋዜማ ተረድታለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከክልሎች የ6ኛ ክፍል ትምህርት አጠናቀው በመሸኛ ወደ አዲስ አበባ ለመዛወር የሚያመለክቱ የ7ኛ ክፍል ተማሪዎችን በፈተና ሳልመዝን አልቀበልም የሚል ውሳኔ አሳልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2016 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ምዝገባ ከመጀመሩ አንድ ሳምንት አስቀድሞ ውሳኔውን ለሁሉም ክፍለ ከተሞች የትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በደብዳቤ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ትምህርት ቢሮው ያስተላለፈውን ደብዳቤ ዋዜማ የተመለከተች ሲሆን፣ ከተማ አስተዳደሩ የሚያዘጋጀውን “ደረጃውን የጠበቀ” የተባለውን ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች 6ኛ ክፍል ደግመው እንዲማሩ ያዛል፡፡ የከተማ አስተዳደሩን መመዘኛ ፈተና ማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡ ተማሪዎች የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው መቀጠል ይችላሉ፡፡

ውሳኔውን ተፈጻሚ እንዳደርጉ ትዕዛዝ የወረደላቸው የከተማዋ ትምህርት ቤቶች፣ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ ለመዛወር ያመለከቱ ተማሪዎችን ስም ዝርዝር በክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች በኩል ለቢሮው ማሳወቅ እንዳለባቸው በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል፡፡

በትምህርት ቢሮው ምክትል ኃላፊ ወንድሙ ኡመር ተፈርሞ ለክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የተላለፈው ይህ ውሳኔ፣ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚዛወሩ የ7ኛ ክፍል ተመዝጋቢ ተማሪዎች የሚስተናገዱበት ወጥ አሰራር ለመዘርጋት ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በተለያዩ ምክንያች ኑራቸውን ወደ አዲስ አበባ የቀየሩ ወላጆችና ተማሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ቅሬታ አንስተዋል፡፡ ውሳኔው ቅሬታው የቀረበበት በሁለት መንገድ ሲሆን፣ አንደኛው ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆነው ክልል አቀፍ ፈተና በወሰዱ ወይም ባልወሰዱ የሚል መለያ አለማስቀመጡ ነው፡፡ 

ሁለተኛው ቅሬታ ደግሞ ተማሪዎቹ በተማሩባቸው ክልሎች በየትምህርት ቤታቸው በተሰጣቸው ፈተና መሰረት፣ ወደ 7ኛ ክፍል ማለፋቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሳለ በትምህርት መጀመሪያ ወቅት ዳግመኛ መፈተናቸው ተገቡ አይደለም የሚል ነው፡፡

ከአዲሱ የትምህርት ፖሊስ ተግባራዊ መደረግ በፊትም አንድ ተማሪ ከተማረበት ክልል ማለፊያ ውጤት ማምጣቱን ማረጋገጫ ለሚዛወርበት ክልል ትምህርት ቤት ካቀረበ በሁሉም ክልሎች ተቀባይነት አለው፡፡ 

ከተማ አስተዳደሩ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ በክልላቸው መመዘኛ ያለፉ ተማሪዎችን በራሴ ፈተና መዝኘ ካላለፉ አልቀበልም ማለቱ የሕግ አግባብ የሌለው በመሆኑ ውሳኔው አንዲሻር ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የተማሪ ወላጆች ጠይቀዋል፡፡

በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖለሲ መሰረት ካለፈው የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ ለ6ኛ ክፍል ተማሪዎች አንደኛ ደረጃ የማጠናቀቂያ ፈተና እንዲጀመር ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሁሉም ክልሎች ወጥ በመሆነ መንገድ ክልላዊ መመዘኛ ፈተና ባለመጀመራቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን ውሳኔ መሳለፉን ተከትሎ፣ በወላጆች በኩል ቅሬታና ውዥንብር ተፈጥሯል፡፡

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራት የውሳኔ ደብዳቤውን በፊርማቸው ያረጋገጡትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወንድሙ ኡመርን ያነጋገረች ሲሆን፣ ውሳኔው በደብዳቤው ላይ እንደተገለጸው ሁሉንም ሳይሆን ክልል አቀፍ መመዘኛ ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎችን የሚመለከት ነው ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ክልል አቀፍ ፈተና መስጠት ስለጀመረ ክልል አቀፍ መመዘኛ ፈተና ሳይወስዱ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የተዛወሩ፣ የ7ኛ ክፍል ተመዝጋቢዎችን በከተማው መመዘኛ ሳይመዘኑ መቀበል ፍትሐዊ አለመሆኑን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡ 

በወላጆች በኩል በውሳኔው ግልጽነት እና ተገቢነት ላይ የተነሳው ጥያቄን አመራሩ ኦረንቴሽን ተስጥቶች በአገባቡ እንዳስፈጽም ትዕዛዝ መሰጠቱን ምክትል ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከተማሩበት ክልል የማለፊያ ማረጋገጫ ያቀረቡ ተማሪዎች በትምህርት መጀመሪያ ወቅት ለፈተና ማስቀመጥ ላይ የተነሳው ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩ ችግር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከፍተቱ የተፈጠረው በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው የ2015 የትምህርት ዘመን የተጀመረውን የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ መመዘኛ ፈተና ሁሉም ክልሎች ባለመጀመራቸው መሆኑን፣ የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አመለወርቅ ህዝቅኤል ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ]