ዋዜማ- የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶር)፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ ከደረሰባቸው ከባድ የመኪና አደጋ ጋራ በተያያዘ ላለፉት 6 ቀኖች በኢትዮ-ጠቢብ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል (አይሲዩ) የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ዋዜማ ስምታለች። ምንጮቻችን ሚኒስትሩ በወቅቱ በአልኮል መጠጥ ተጽዕኖ ስር ሳይሆኑ እንዳልቀሩ መታመኑን ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ አደጋው የደረሰባቸው፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሰኞ አጥቢያ ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ወደ ቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ፣ ራሳቸው ሲያሽከረክሩት የነበረው መኪና በካርል አደባባይ ከቆመ ኤክስካቫተር ጋራ በመላተሙ እንደኾነ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል።።
በግጭቱ፣ ሚኒስትሩ ካሳሁን በእጃቸው፣ በእግራቸው እና በደረት አጥንቶቻቸው ላይ ከባድ ጉዳት እንዳገኛቸው ተመልክቷል።
ሚኒስትሩን ከአደጋው ሥፍራ ወደ ሆስፒታሉ ያደረሷቸው ሰዎች፣ በግጭቱ ከተጎዳው ተሽከርካሪያቸው ውስጥ ሲያወጧቸውም ሆነ የተሻለ ሕክምና ያገኙባቸዋል ወዳሏቸው የተለያዩ ሆስፒታሎች ሲያዘዋውሯቸው፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን መኾናቸውን ባይገነዘቡም በአልኮል መጠጥ ተጽዕኖ ውስጥ እንደነበሩ ግን ማወቃቸውን ምንጮቻችን ተረድተዋል።
የመኪና አደጋውን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች አካላት እንዳይሰሙት ለመደበቅና ለተሻለ ህክምና ከአገር ወጥተው እንዲታከሙ ታስቦ እንደነበር የመረጃው ምንጮች አውስተዋል። ይሁንና ከነዳጅ ጉዳይ ጋራ ለተያያዘ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈለጓቸው ወቅት ስለ አደጋው በመስማታቸው ምክትላቸውን አደም ፋራህን ልከው አስጠይቀዋቸዋል ተብሏል። ከዚህ በኋላ እንደታሰበው ለህክምና ወደሌላ አገር ይላኩ እንደሆነ ለማረጋገጥ አልቻልንም ። [ዋዜማ]